2022-07-12 19:49:54
ዋስትና የተጠርጣሪን የኋላ ታሪክ እስክናውቅ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይፈቀድልን፣
ተከሳሹ ደጋጋሚ ወንጀለኛ ስለሆነ ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም በሚል የምትከራከሩ ዐ/ህግ እና መርማሪ ፖሊሶች እንዲሁም ይህን በምክንየትነት የምትቀበሉ ዳኞች ተከታዩን ግንዛቤ እንድትወስዱ "የተጠቃለሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ የህግ ትርጉሞች ከቅፅ1-23" መፅሃፍ መሀል ይህን የሰበር መዝገብ እንደ ማሳያ እነሆ።
የሰ/መ/ቁ.132055፡-በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 67 (ለ) ስር የተደነገገው የዋስትና መብት ገደብ በተከሳሹ ያለፈ የወንጀል ታሪክ ላይ የሚመሠረት አይደለም፡፡
ይልቁንም የድንጋጌው ዓላማ በእጅ ላይ ያለውን የክሱ ሂደት ሊያደናቅፍ ይችላል ተብሎ በሚገመትበት ጊዜ በዋስ የመለቀቅ መብቱን ለመገደብ ነው፡፡ የወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 67 (ለ) ከንዑስ ቁጥር (ሀ) እና (ሐ) ጋር በአንድነት ሊነበብ ይገባል፡፡
ህጉ የተከሳሹን በዋስ የመለቀቅ መብት እየገደበ ያለው በዋስትና ወረቀት ላይ የሰፈሩትን ግዴታዎች አይፈጽምም ተብሎ ሲገመት ወይም ምስክሮችን ሊያባብል ወይም ሊያስፈራራ ይችላል ወይም ማስረጃዎችን ሊያጠፋ ይችላል ተብሎ ሲገመት ነው፡፡
የቁጥር 67 (ለ) ድንጋጌም ከንዑስ ቁጥሮች (ሀ) እና (ለ) ጋር በጣምራ ሲነበብ “ሌላ ወንጀል ሊሠራ ይችላል ተብሎ ሲገመት” የሚለው ድንጋጌ ከተያዘው ክስና ከተጀመረው የፍርድ ሂደት ጋር በተያያዘ ጠባብ የህግ ትርጉም በተጣጣመ መልኩ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡
ፍ/ቤቶቹ የተከሳሽችን ያለፈ የቅጣት ውሳኔ አሁን ከተከሰሰበት ጉዳይ ጋር በማያያዝ በዋስ ቢለቀቅ ተመሳሳይ ወንጀል ሊፈጽም ይችላል የሚል ግምት በመውሰድ የዋስትና ጥያቄውን አለመቀበል አግባብ አይደለም፡፡
በተጨማሪም በሌላ በኩል የወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 138 (1) ህጉ በግልጽ ካልተደነገገ በቀር ተከሳሹ በፍርድ ዳኝነት በግልጽ እስካልታወቀ ድረስ የቀድሞ ጥፋተኝነቱ አይገለጽም ሲል ደንግጓል፡፡
ድንጋጌው የተከሳሽን ንጹህ ሆኖ የመገመት ህገ-መንግሥታዊ መብት የሚያመለክት ሲሆን በተጨማሪም ዳኞች የወንጀል ጉዳይ በሚመረምሩበት ጊዜ በተከሳሹ የጥፋተኝነት ሪከሪድ ጫና አድሮባቸው የተሳሳተ ውሳኔ እንዳይሰጡ ለማድረግ የሰፈረ ነው፡፡
በመሆኑም የተጠርጣሪዉ የቀድሞ የጥፋተኝነት መዝገብ በጊዜ ቀጠሮ ጊዜ ሲቀርብ ፍ/ቤቶች ከላይ በተጠቀሰው የህግ ድንጋጌ መሠረት እንዳልቀረበ በመቁጠር ሊወሰን ይገባል እንጂ ህጉን በመጣስ በተጠርጣሪዉ የቀድሞ የጥፋተኝነት መዝገብ ላይ በመመሥረት ማከራከር እና መወሰን መሠረታዊ የህግ ስህተት ነዉ፡፡
በአጠቃላይ የአንድ ተከሳሽ ያለፈ የቅጣት ውሳኔን አሁን ከተከሰሰበት ጉዳይ ጋር በማያያዝ በዋስ ቢለቀቅ ተመሳሳይ ወንጀል ሊፈጽም ይችላል የሚል ግምት በመውሰድ የዋስትና ጥያቄን አለመቀበል አግባብነት የለዉም፡፡እንዲሁም በህግ በግልጽ ካልተደነገገ በቀር አንድ ተከሳሽ በፍርድ ዳኝነት በግልጽ እስካልታወቀ ድረስ የቀድሞ ጥፋተኝነቱ ሊገለጽ አይገባም፡፡ቅጽ/23
via #henoktaye law office
#አለ_ህግ #Alehig
@lawsocieties @AleHig
https://t.me/lawsocieties
https://t.me/AleHig
2.2K viewsEntrust ETC, edited 16:49