2022-01-16 13:11:37
ሶፋ ወይስ አልጋ? - አስፈላጊው ነገር ላይ የማተኮር ምስጢር
(“ትኩረት” ከተሰኘው የዶ/ር ኢዮብ ማሞ መጽሐፍ የተወሰደ)
አንድ ሰው በሚኖርበት ማሕበረሰብ አካባቢ አንድን ጥናት ማድረግ ፈለገ፡፡ ከጥናቱ ሊያገኝ የፈለገው እውነታ ይህንን ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል ትኩረታቸው ከላይ ለሰዎች የሚታየውን ብቻ ቀባ ቀባ ማድረግ የሆነና ለታይታ ብቻ የሚኖሩ ሰዎችን የሕይወት ሁኔታ ማወቅ ፈለገ፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ለታይታ ብቻ ሳይሆን በትክክለኛውና በሕይወት ላይ ለውጥ በሚያመጣው ነገር ላይ የሚያተኩሩ ሰዎችን ሁኔታ መገንዘብ ተመኘ፡፡
ይህንን ሁኔታ በቀላሉ ለማወቅ የሚችልበትን ዘይቤ ሲፈልግ አንድ ነገር ብልጭ አለለት፡፡ በየሰፈሩ እየተዘዋወረ ፈቃድን ባገኘበት ቤት ሁሉ እየገባ አንድን ጥያቄ መጠየቅ ጀመረ፡፡ ጥያቄው አጭርና ግልጽ ነበር፡- “በቤትዎት ካለው ሶፋ እና አልጋ በዋጋ የትኛው ይበልጣል? እነዚህንስ እቃዎች ሲገዙ ብዙ ትኩረት የሰጡበት የትኛውን ነው? ብዙ ዋጋ ላወጡበት እቃስ ያንን ያህል ዋጋ እንዲያወጡ ያነሳሳዎት ምንድን ነው?” የሚል ነበር፡፡
እነዚህን ሶስት ጥያቄዎች ከጠየቀ በኋላ የሰዎቹን የአኗኗር ሁኔታ በቀስታ ያጤን ነበር፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ ቤቶችን በመጎብኘት ይህንን መጠይቅ ለማቅረብና መረጃ ለመሰብሰብ ወደ አንድ አመት ፈጅቶበታል፡፡ በመጨረሻ ያገኘው መልስ ሲጨመቅ አስገራሚ ስእል አመላከተው፡፡
በዚህ ጥናታዊ መጠይቅ ላይ ከተሳተፉት ሰዎች አብዛኛዎቹ ለገዙት አልጋ ካወጡት ዋጋ ይልቅ በብዙ እጥፍ የከፈሉት ለሶፋቸው ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ግዢውን ሲፈጽሙ ብዙ አማራጭ ለማግኘት ጊዜን የወሰዱትና ብዙ ሰው ያማከሩበት እቃ ሶፎው ነበር፡፡ አልጋ ለመግዛት ካወጡት ገንዘብና ለምርጫ ካሳለፉት ጊዜ ይልቅ በሶፋ ላይ የበለጠ ገንዘብና ጊዜ የማውጣታቸውን ምክንያት ሲጠየቁ የሰጡት መልስ ሲጨመቅ፣ “ሰዎች ሲገቡ የሚያዩት ሶፋውን ስለሆነ ነው፣ አልጋውንማ ማን ያየዋል?” የሚል ነበር፡፡
ግኝቱ ይህ ነው፡- አንድ ሰው በቀን ውስጥ በአማካኝ ሰባት ወይም ስምንት ሰዓታትን በአልጋው ላይ ያሳልፋል፡፡ በቀን በሶፋው ላይ ተቀምጦ የሚያሳልፈው ጊዜ ግን በአማካኝ ከሶስትና ከአራት ሰዓት በላይ አይሆንም፡፡ ስምንት ሰዓታት ሰውነቱን ጥሎበት የሚያሳልፈው ይህ አልጋ የተሰኘው ነገር በአካላዊ ጤንነቱ ላይ ይህ ነው የማይባል ስፍራ አለው፡፡ በተጨማሪም ከማይመች አልጋ የሚመጣ የእንቅልፍ ማጣት ችግር ለቀን ተግባር ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑም እሙን ነው፡፡
አስፈላጊ ከሆኑት በሕልውናችንና በስኬታማነታችን ላይ ዘላቂ ተጽእኖ ከሚያመጡት የሕይወታችን ጉዳዮች ላይ ትኩረታችንን ማንሳት ብዙ አሉታዊ ተጽእኖዎች አሉት፡፡ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ከታይታ ወደማያልፉ ነገሮች እንድንዞርና ብዙ ውድ ነገሮቻችንን እንድናባክን አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ለምሳሌ ጊዜአችንን፣ ገንዘባችንንና ሃሳባችን በተለያዩ ጊዜአዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የመበታተን የሕይወት ዘይቤ ውስጥ እንገባለን፡፡ ትኩረቱን ከጊዜአዊውና ለታይታ ከሆነው ነገር ላይ በማንሳት ወደ አስፈላጊውና ወደ ዘላቂው ነገር ያዞረ ሰው ለጊዜው ሰዎች አይተው የሚያደንቁለት ነገር ባይኖረውም እንኳ ለነገ እንደሚሰራ ያውቀዋል፡፡
ለታይታ መኖር የዘመናችን ችግር ነው፡፡ እኛ በፍጹም ተጠቅመንባቸው የማናውቃቸው እንግዳ ሲመጣ ብቻ የሚወጡት ምቹና ደስ የሚያሰኙ እቃዎቻችን ብዙ ናቸው፡፡ በእነዚህ እቃዎቻችን ላይ የፈሰሰው ገንዘብ የእኛን የኑሮ ጥራት ለማሻሻል መሆን ሲገባው አልፎ አልፎ ብቅ ብሎ ለሚሄድ እንግዳ መደሰቻና “ይህና ያኛው እቃ እኮ አለን” የሚለውን መልእክት በድምጽ-አልባ ንግግር ለማስጮህ ካልሆነ በስተቀር ምን ትርጉም አለው? የማንመገበው እህል ሰው እንዲያየው ደጅ ቢሰጣ ምን ዋጋ አለው? የቤቴን መሰረታዊ ነገር ሳላሟላ በየካፌው ለሰው ብከፍል ትርፉ ምንድን ነው?
በሰው ለመታየት ከመጣጣሬ በፊት በመጀመሪያ የግል ኑሮዬንና የቤተሰቤን ሁኔታ በሚገባ ለማየት መጣጣር ይኖብኛል፡፡ ውጫችንን አይቶ ያደነቀን አይን ለውስጣችን ጤንነት ምንም አይነት መዋጮ አያደርግልንም፡፡ የሶፋችንን ማማር የተመለከተ ሰው ያሳየን መገረም የሚያስገርም እንቅልፍ ትቶልን አይሄድም፡፡ የውጭ ገጽታና ውበት እጅግ መልካምና የራሱ የሆነ ጥቅም ያለው የመሆኑ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ በመጀመሪያ ሊቀድም የሚገባው የአስፈላጊውና የመሰረታዊው የኑሮአችን ሁኔታ መስተካከሉ ነው፡፡
@kene_tobeya
2.0K views ⓐⓜⓐⓝ, 10:11