Get Mystery Box with random crypto!

' ኤሴቅ ' ክፍል ~፪፻፴፪~ ( 232) በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888 'የሐመረ ኖህ ወረዳ | ቅን ልቦች

" ኤሴቅ "
ክፍል ~፪፻፴፪~ ( 232)
በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888
"የሐመረ ኖህ ወረዳ አስተዳዳሪ ና ልዑካቸው እየተዟዟሩ ትምህርት ቤቱን ከጎበኙ በኋላ ወደ ተዘጋጀላቸው የክብር ወንበር ሄደው ተቀመጡ። "ጥሩ አድርጎ ነው ያሰራው። በሚገባ የተደከመበት ስራ ለመሆኑ ህንፃው ይናገራል"አለ የሐመረ ኖኅ ከተማ ከንቲባ። "በትክክል ከእኛ የሚጠበቀው ጥሩ ጥሩ መምህራኖችን መቅጠር ነው። በሚቀጥለው አመት መጀመሪያ ተማሪዎች ትምህርት ተመዝገበው እንዲማሩ ይደረጋል። ማንኛውም ከሰባት አመት እድሜ ከፍ ያለ ልጅ ካለ በግዴታም ቢሆን ገብተው መማር አለባቸው። ይሄን ስራ ደግሞ እናንተ መስራት አለባችሁ"አለና የወረዳው አስተዳዳሪ ወደ ቀበሌው ሊቀመንበር ዞረ። "በትክክል እንጅ እኛ እየዞርን ቤተሰቦቻቸውን በማስፈራራት ትምህርት እንዲጀመሩ አሰናደርጋለን"በማለት መለሰ።
*
የትምህርት ቤቱን መመረቅ ተከትሎና የነ ቀዳማዊን መምጣት ተመልክቶ ጥሩ ድግስ ተደግሷል። ዘመድ አዝማድና ጎረቤትም ተጠርቷል። ከወይዘሮ አትጠገብ ልጆች በስተቀር ሁላቸውም መጥተዋል። ሙሉቀን ጨዋታውም ምኑም እንዲደራ ከአንድ ቀን በፊት ለሊቀ መኳስ መልዕክተኛ ልኮበት ነበር። "እንደምን አለህ ሊቀመኳስ ተቻልህ እና ቶሎ ከደረስክ ነገ ጠዋት ታልሆነልህ ደግሞ ወደ ማታ አካባቢ እንድትደርስ። የደጃዝማች ታረቀኝ ልይ ቀዳማዊ መጥቷልና እንዳትቀር አደራ "የሚል መልዕክት ነበር የሰፈረበት ደብዳቤው ላይ።
"ውሸት በፍርቃ ግንድ
ሲታጠን እንድታይ ጧት እንዳታረፍጂ
ታይቷል አምሮ ከብሮ
በደጃዝማች እውነት ጊዜ ሆይ ስገጂ"ሊቀመኳስ እንጉርጉሮውን ጀመረ። "እየው እየው ይሄ መናጢ ጨዋታዋን ጀመራት። አጀብ ነው እንዴት ነው ወጓን የሚፈጥራት"አለ አንድ ሽማግሌ በፈገግታ የዳሱ ኮርና ላይ ተቀምጦ ጠጁን እየጠጣ ከሌላኛው አጠገቡ ከተቀመጠ ጎረቤቱ ጋር እየተያያ። "አዎ በደንብ እንጅ ወጓንም እውነቷንም ወዋታዋንም ሽሙጧንም በደንብ ነው የሚችልባት"አለ ሌላኛው።
"አዝማሪ ያደረጉለትንና ያደረጉበትን አይረሳምና ዛሬ በአካል ባይኖርም ደጃዝማች ታረቀኝ የሁላችንም አባት ነው። ማንም የማይሰጠኝን ክብር ነበር እሱ የሚሰጠኝ። አዝማሪነቴ ጥበበኝነት እንደሆነና መዝናኛ እንደሆነ ነበር ሁሌም የሚነግረኝ"አለ ሊቀመኳስ ማሲንቆውን ለአፍታ አቁሞ። ሔዋንና ሙሉሰው ራሳቸውን በአግራሞት ነቀነቁ።
ሕይወት በብዙ መልክ ሆና በስኬት ካባ ተከናንባ በሌላ የድል ምዕራፍ ሕይወቷን ሀ ብላ ትቀጥላለች። ቀዳማዊ በሊቀመኳስ የግጥም ስንኞች ትላንቱን እንደ ገብስ እህል በሀሳብ መንሽ እየበረበረ በልጅነት ዛላ የረሳውንም እያስታወሰ ያስታወሰውንም እያጣጠመ አመሸ። ሊቀመኳስም ክፉዎችን በስንኙ እየጎሸመ መልካሞችን እያሞገሰ ከበርካታ የብር ሽልማቶች ጋር አመሸ። በሕይወቱ ተሸልሞ የማያቀውን የብር መጠን በአንዲት ጀንበር አጋብሶ አመሸ።
***
"እባካችሁ ልጆቼ አንድ ነገር ብቻ ልለምናችሁ ልጄን ለመጨረሻ ጊዜ ልዬው ጥሩልኝ። ቢያንስ ለነፍሴ ጥሩ ስንቅ ይሆናታል። እንደዚሁ መሄድ አልፈልግም "አለች ወይዘሮ አትጠጠብ ዙሪያውን የከበቧትን ልጆች እየተማፀነች። ግራ ተጋብተው ተያዩ "ይቺ ሴትዮ ምንድን ነው የምትለው?"አለችና አድና በንዴት ተነስታ ወደ ስርጡ(ጓዳ) ገባች። "በቃ እህቶቼ እየደከመች ነው ቀዳማዊን እናስጠራላት።ምንም ቢሆን የእኛ ፍላጎት ከእናታችን አይበልጥም"አለች ርብቃ። በርብቃ ሀሳብ ተስማምተው ለቀዳማዊ መልዕክት ተላከ። ሙሉቀን ዙሪያ ገባውን ጋራና ሸንተረሩን ከምሽቱ አናሳ የጨረቃ መጠን ጋር እያስተያየ ውጪ ላይ ተቀምጦ የርብቃ ልጅ እያለከለከ መጣ "ጋሻዬ ሙሉቀን!"አለ "አቤት ምን ሆነህ ነው የምታለከልከው? እየሮጥኩ ስለመጣሁ ነዋ!" "ምን ሆነህ ነው እየሮጥክ የመጣኸው?"ሙሉቀን እየደነገጠ ጠየቀው። "አያቴ ደክማለይ እና ቀዳማዊን መገናኘት ትፈልጋለች። አጎቴን እንዲመጣ ጥሩ ብላ ነው። እንድጠራው ተልኬ ነው።"አለ ሙሉቀን በፍጥነት ወደ ቀዳማዊ ጋር ሄደና በሹክሹክታ በጆሮው ሁሉንም ነገረው።"እሺ አንድ ጊዜ ጠብቀኝ ላስተኛት"አለ ጭኑ ላይ የተኛችውን ሐምራዊ እየተመለከተ። ሐምራዊን ደገፍ አቀፍ አድርጎ መኝታቸው ጋር ካስተኛት በኋላ ከሙሉቀን ጋር ህፃኑን ተከትለው ሄዱ።
ቀዳማዊ እንደደረሰ ሁላቸውም በፀጥታ ተዋጡ። ዙሪያ ገባውን አማተረ። ያ ምድጃ አሁንም አለ። በብርድ ተመትቶ ለመሞቅ የሚቀመጥበት የምድጃው ጠርዝም መልኩን አልቀየረም። የመከራ ስቃይ በልቶ የሚተኛባት ደመደም የምትመስለዋ መደብም ያለምንም ልዩነት አለች። ቀዳማዊ አይኖቹ እንባ አርግዘው ሁሉንም ተመለከተና ዝቅ ሲል ሌላኛው መደብ ላይ ወይዘሮ አትጠገብ ተኝታለች። ሙሉቀን ቀዳማዊን ደገፍ አድርጎ ወደ ወይዘሮ አትጠገብ አስጠጋው። ርብቃ የእናቷን ወገብና አንገት ደገፍ አድርጋ "ይሄው መጥቷል"ብላ በአጠጯ ወደ ቀዳማዊ ጠቆመቻት። አይኖቿን እያርገበገበች ቀዳማዊን ለማየት ጥረት አደረገች ነገር ግን አይኖቿ ብዥታ ውስጥ ስለነበሩ ቀዳማዊን በትክክል ለመመልከት አልቻለችምና አይኖቿ ወደነበረበት ተከድነው ሰውነቷ እየቀዘቀዘ ሄደ። ወይዘሮ አትጠገብ ለዘላለም ይቺን ምድር ተሰናብተዋት ሄዱ። ርብቃ ዋይታዋን አቀለጠችው። ሌሎቹ እህቶቿም ተከትለዋት እሪ አሉ። ፊታቸውን እየነጩ ደረታቸውኝ መድቃት ጀመሩ።
"ምንድን ነው ወዲያ ማዶ ግድም ዋይታ አለሳ እልፍነሽ "አለ አባወራው "አይይ አትጠገብ አረፈች ማለት ነው። በጣም ተቸንፋ ነበር። ሰሞኑን አታልፍም እያለ ነበር ሰው። አየ ጉድ አዬ ጉድ በመጨረሻ ወደማይቀረው ሄደይ!"አለችና በሀዘን እንደመተከዝ ብላ ለነገሩ ለእሷ እንኮ ሞቱ ይሻላታል። በጣም እየተሰቃየች ነበር"አለችና እንደመተከዝ አለች።
ቀዳማዊ በለቅሷቸው ደንዝዞ ቆመ። ለማን እንደሚያለቅሱ ማን እንደሞተ ግራ የገባው ይመስላል። ፊቱ ላይ የእንባ ርዝራዥም ሆነ የሀዘን ጥላ አጥልቶ አልታየበትም። ሙሉቀን ይዞት ወጣና ወደ ቤት መለሰው። ቀዳማዊ አልተቃወመውም ምንም ነገርም ደግሞ አላለውም።
"ልጄ የምን ለቅሶ ነው?"አለች የሙሉቀን እናት ""ወይዘሮ አትጠገብ እኮ አረፈች"። እነ ሙሉሰውና ሔዋን በድንጋጤ ተያዩ። "ኧረ እግዚኦ ምን አይነት ማዕት ነው!"አለችና ብድግ ብላ ወጣች። "ምነው ምን ሆና ነበር?"አለች ሔዋን ሙሉቀንን "አይ ከታመመች እንኳ ቆይታለች። እርጅናውም ምኑም ተጨምሮባት አባበሰባት። ቀዳማዊን ለማየት አስጠርታው ነበር። ልክ ቤት ስንደርስ ጉልበትም ምንም አንሷት ነበርና ትንሽ ሳትቆይ ወዲያው አረፈች"አለ። ቀዳማዊ ሁለታቸውንም ሲያዳምጣቸው ከቆዬ በኋላ ወደ ቤት ውስጥ ገብቶ ሐምራዊን እቅፍ አድርጎ ትኝት አለ። ሙሉቀን ተከትሎት ሊገባ ሲል "ተወው ልጄ የፈቀደውን ያድርግ ሕመሙ ሲዘልቀው ተነስቶ ያለቅሳል። ያዝናል"አለች ሔዋን። ዋይታውና እሪታው እየጨመረ መላው መንደሩን አዳረሰው።
ብሰንት ልመናና ጉትጎታ ቀዳማዊ ቀብር ላይ እንዲገኝ ተደረገ። በተለይ ሐምራዊ ባልተወለደው ልጇ ሁሉ ለምናዋለች። ሔዋን የበርካታ ታቦቶችን ስም በመጥራት ለምናዋለች። በመጨረሻ በሁላቻውም ጥረት ቀብር ላይ ለመቆም ወሰነ። ማለፊያ ቀዳማዊን ስታየው እንደ አራስ ነበር አደረጋት። "አንተ ነህ እናቴን የገደልካት። አንተ ወደዚህ ባትመጣ ኖሮ አትሞትም ነበር። አንተ የተረገምክ ሕይወታችንን ስቃይ አደረከው"እያለች ደረቷን ትደቃበት የነበረውን ድንጋይ ይዛ ወደ ቀዳማዊ እየገሰገሰች ስትመጣ ለቀስተኞች ይዘው አስቀሯት። ድግጋውንም ከእጇ በቀስታ በመንጠቅ ወረወሩት። ቀዳማዊ በነ ሔዋን ታጅቦ ዝም ብሎ ስርአተ ቀብሩን አስፈፀመ።

@amba88
@ken_leboch