Get Mystery Box with random crypto!

' ኤሴቅ ' ክፍል ~፪፻፴፩~ ( 231) በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888 ይሄ ስራ በትክክል | ቅን ልቦች

" ኤሴቅ "
ክፍል ~፪፻፴፩~ ( 231)
በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888
ይሄ ስራ በትክክል ተሰርቶ ለዚህ ደረጃ እንዲበቃ ጠዋትና ማታ ከእንቅልፍ ስአታቸው በመቀነስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በአንድ አይነት ሀሳብ በመቀናጀት ተናበው ሲሰሩ ለነበሩ መሀንዲሶችና ግንበኞች የቀን ሰራተኞች ከፍ ያለ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ። እንዲሁም ይህን ትልቅ ፕሮጀክት ለማሰራት ሙሉ ገንዘቡንና ሀሳቡን ያወጣው ኢንጂነር ቀዳማዊ ታረቀኝ በእኔና በማህበረሰቡ ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ። " ስራው በጣም የተለፋበትና የተደከመበት ስለመሆኑ የወጣበት ገንዘብና ጊዜ ብቻም ሳይሆን ስራው ራሱ ይመሰክራልና አቶ አቤል በእውነት ጥሩ ስራ ነው ለዚህ ትልቅ ምስጋና ሊቸረው ይገባልና ሞራል ስጡልኝ" በማለት መድረክ መሪው አቤልን ወደ ቦታው በጭብጨባ እንዲሸኙት አደረገ። "ግን እኮ እሱ የምንም ነገር እውቀት የለውም። እንዴት ይሄን ያህል ፕሮጀክት ሊያሰራ ይችላል?"አለ አንድ ወጣት ከስብሰባው መሀል ለሌላኛው ጓደኛው። "አዎ ግን እሱ እኮ ተቆጣጣሪ ነው። የስራውን ሂደት የሚከታተለው ግን ቀዳማዊ ነበር። ዋና መሀንዲሶች ነበሩ። እነሱ ናቸው ስራውን በደንብ ሲሰሩ የነበረው። ያው መልካሙ ከአሻንጉሊት ያልተናነሰ ስራ ነው ያለው"አለ "የሚገርም እኮ ነው ግን ቀዳማዊ እንደዚህ ይሆናል ብሎ የገመተ ማን ይኖራል?" "ምን ታደርገዋለህ? ፈጣሪ እድለኛ አድርጎ ሲፈጥርህ እኮ እጣህ እንዲህ በሀብት ላይ ሀብት በዝና ላይ ዝና መጨመር ነው"። መድረክ መሪው በመቀጠል በርካታ መልዕክቶችን ካስተላለፈ በኋላ የወረዳውን የስራ ሀላፊዎችንና ቀዳማዊን ወደ መድረክ በመጥራት የምርቃት ስነስርአቱ ተጀመረ።ሶስት ልጆች በእምነ በረድ የተፃፈውን ፅሁፍ አምጥተው ዳርና ዳር ከተሰራ ባላ አጋድመው ተከሉት። በትልቅ ወረቀት ተሸፍኖ ስለነበር ቀዳማዊ እንዲቀደው ተደረገ። ሰው ውስጡ ላይ ያለውን ፅሁፍ ለማየት በጣም ጓጉቷል። ቀዳማዊ በእርጋታ አዟዙሮ ከተመለከተ በኋላ በዳርና በዳር ወረቀቱን ቀዶ ፅሁፉን ለሕዝቡ ክፍት አደረገው "ደጃዝማች ታረቀኝ የሺዋስ መታሰቢያ ትምህርት ቤት"የሚል ፅሁፍ እምነበረዱ ላይ ተቀርጿል።
" ይህ ትምህርት ቤት በአባቴ ስም ያደረኩት። አባቴን እኔ ከማውቀው በላይ የዚህ ቀበሌ ነዋሪ በደንብ ያውቁታል። እኔ ልጁ ነኝ በቃ ስለ አባቴ እናንተ በነገራችሁኝ መሰረት ነው። የእናንተ አስታራቂ አስተማሪ እንደሆነ ብዙዎቻችሁ ነግራችሁኛል። ይህን ደግሞ በሚገባ ይዣለሁ። አንዳንድ ጊዜ ልጆች በወላጆቻቸው መጥፎ ሀጢያት እንደሚሰቃዩት ሁሉ እኔ ደግሞ በአባቴ ደግነት ምክንያት አንገቴን ቀና አድርጌ በእናንተ ፊት ቆሜያለሁ ሄጃለሁም። ከብዙ አመት በኋላ ስመጣ የአባቴን ደግነትና የአባቴን መልክ እኔ ፊት ላይ ለመስራት የጣራችሁትን ጥረት ያደረጋችሁትን ሙከራ በሚገባ አውቃለሁ። ስለዚህ ይህ ትምህርት በአባቴ ስም ተሰይሞ በአባቴ ግብር መልክ ትምትናን እውነተኛነትን ግብረገብነትን ፍቅርን መቻቻልን ልጆቻችሁ እንድንማር ተከፍቷል። የአባቶቻችንን መልካም ስራ ለማስቀጠል ደግሞ በትምህርት የታገዝን መሆን እንዳለብን ስላመንኩ ነው ትምህርት ቤቱን ለማሰራት የወሰንኩት። አባቴ ለእኔ ካደረገልኝ በላይ ለእናንተ ያደረገው ይበልጣልና ይሄው ይህ ትምህርት ቤትም በእኔ በልጁ ለእናንተ የተሰጠ ስጦታ ሆኗል። ልጆቻችሁን አስተምሩ። አለም በምሁራን እየተጥለቀለቀች የፈጠራ ባለሞያዎች እንደ ጉንዳን የሚፈለፈሉባት ሆናለች።ስለዚህ ወላጆች ልጆቻችሁን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ አታቅማሙ ልጅችም ወደ ትምህርት ቤት ላለመሄድ ማሰብ የለባችሁም። እናንተ ስትማሩ ቤተሰባችሁን አካባቢያችሁን ታስተምራላችሁ። እናንተም ተምራችሁ ራሳችሁንም ኑሯችሁንም ትለውጣላችሁ። እና በመጨረሻ አንድ ነገር ብዬ ልውረድ። እኔን ከማሳደግና ከማስተማር ጀምሮ ትልቅ መስዋዕትነት ለከፈሉት ለአቶ ሙሉሰውና ለወይዘሮ ሔዋን ምስጋናየን በእናንተ ፊት ልገልፅላቸው እወዳለሁ። እነሱ ባይኖሩ እኔ እዚህ ደረጃ የመድረሴ እውነት አጠራጣሪ ነበር። እግዚአብሔር አባቴን ወስዶ እናትም አባትም ሰጥትኛልና ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን። እንዲሁም ባለቤቴ ሐምራዊ ሱራፌል። ስራዎቼ ላይ የራሷንም ሀሳብ በመጨመር በማበረታታት ትደግፈኝ ነበር። ይህ ትምህርት ቤት እስኪጠናቀቅም ሙያዊ እርዳታ ከማድረግ ጀምሮ ብዙ ነገሮችን ከአጠገቤ ሆና ከውናልኛለችና አመስግኑልኝ። በመጨረሻ እዚህ ትምህርት ቤት ላይ ጉልበታችሁንና ጊዜያችሁን ለሰጣችሁ የዚህ ቀበሌ ወጣቶችና ጎልማሶች በጣም ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ። አቶ አቤልን የማመሰግንበት ቃል ስላጠረኝ ምንም ልለው አልችልም። ይሄን ፕሮጀክት ከጥንስሱ ጀምሮ እየተከታተለ ለዚህ አብቅቶታልና እባካችሁ አመስግኑልኝ"በማለት ምክር ሀሳቡንም ምስጋናውንም በማቅረብ ንግግሩን ጨርሶ ማይኩን ለመድረክ መሪው ሰጠ። "ኢንጂነር ቀዳማዊ በዚች ትንሽ የገጠር ቀበሌ ተፈጥሮ። የአባቱን ደግ ልብ በመውረስ እሱም የአባቱን ፈለግ በመከተል የዘላለም ቅርስ ተክሎልናል። ከእኛ የሚጠበቀው በእንክብካቤ መያዝና የተሰጠንን ስጦታ ተቀብለን መማር ነው። እንግዲህ ሁላችንም ከቀዳማዊ ሕይወት በመማር ራሳችንን ለትልቅ ደረጃ ማብቃት ይኖርብናል ማለት ነው። ስለሆነም ኢንጂነር ቀዳማዊን ልናመሰግነው ይገባል። ይህን የመሰለ ትምህርት ቤት ሰርት ስለሰጠን"ብሎ ቀዳማዊን በጭብጨባ ወደ ቦታው እንዲመለስ አድርጎ ንግግሩን ቀጠለ። "የኔ ፍቅር ጥሩ ንግግር ነበር ያደረከው"አለች ሐምራዊ "በእውነት?" "አዎ እያንዳንዷን ነገር በጥንቃቄ ለቅመህ ነው ያነሳኸው!"አለች ሐምራዊ ጉንጩን ሳም እያደረገች። "አመሰግናለሁ እናት!"
"በእርግጠኝነት ወይዘሮ አትጠገብ ይሄን ጉድ ስትሰማ በንዴትና በጭንቀት ትሞታለች"አለ አንደኛው ባላገር "እንዴት አትሞት ይሄን ሁሉ መአት ሲወርድባት"አለ ሌላኛው። "ቄሶች ጥሩ ስራ ለራስ ነው። ዋጋው ለእራስ እንጅ ለእግዜርም ለሌላኛው ሰውም አይደል። ደግ መሆን መጀመሪያ የሚጠቅመው ለራስ ነው። መጥፎነትም ሚጎዳው ራስን ነው። ብለው የሚያስተምሩን እኮ ለዚህ ነው። ወይዘሮ አትጠገብም ሴት ልጆቿን መርጣ ነው ይህን ልጅ ገና በህፃንኑቱ ምንም በማያውቀው ሀጢያት ከፋይ እንዲሆን የፈረዱበት ስለዚህ ብትሞትም ምንም አይደል። የእንጀራ እናት እራሱ እንደ እሷ ክፉ አይደለም። አይሆንም። ግን ይሄው በትልቅ ቁና ስራዋ ተሰፍሮላታል። ያመነቻቸው ሴት ልጆቿ ቁም ስቅሏን እያበሏት ነው።የምረቃ ስነስርዓቱ በልዩ ልዩ ግብዣ ደምቋል። ለትምህርት ቤቱ ማስመረቂያ ተብሎ ሁለት ሰንጋ በሬ ታርዷል። በርካታ ሰዎች ደግሞ ፍየል በግ አቅርበዋል። ልዩ የሆነ መሰናዶ ነበር። ትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ የተሰራው ሰፊ ዳስ የምርቃት ዝግጅቱን ለመታደም መጡ ሰዎች ተሞልቷል። ድግሱ ለጉድ ነበር። መለስተኛ ሰርግ ነበር የሚመስለው። ሁሊም የየራሱን ወግ በጎንዮሽ እያወሩ ይጠጣሉ ይጫወታሉ ቢራም ወንይንም ጠጅም ጠላም ሁሉም በአይነት ነበር።

@amba88
@ken_leboch