Get Mystery Box with random crypto!

' ኤሴቅ ' ክፍል ~፪፻፳፱~ ( 229) በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888 **** 'ልጆች በሕይ | ቅን ልቦች

" ኤሴቅ "
ክፍል ~፪፻፳፱~ ( 229)
በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888
****
"ልጆች በሕይወታችሁ ልክ እንደ ንስር ከፍ ብላችሁ መብረር ከፈለጋችሁ በወጀብ የሚናጥ የንፋስ ሀይልን መቋቋም አለባችሁ። ዛሬ ከትምህርታችን በተለዬ መልኩ ስለ ሕይወት እነግራችኋለሁ። መቼም ከዚህ በፊት ሌሎች መምህራኖችም ነግረዋችሁ ይሆናል ስለ ቅዱስ ያሬድ ታሬክ ትሏ ሰባት ጊዜ ወድቃ በስምንተኛው ግንዱን ስትወጣ በተማረው መሠረት አሁን ሀይማኖታዊ የዝማሬ ዜማዎችን ደርሰውልናል። አለም ላይ ገናና እና ትልቅ አሻራ የሚያስቀምጡ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች እንደ ወርቅ ተፈትነው ከመሞት አምልጠው ወድቀው ተነስተው ነው ለጥሩ ደረጃ የሚበቁት። መቼም ይሄን ያለነገር አላነሳሁላችሁም።አሁን የምነግራችሁ ታሪክ እውነተኛ ነው። እኔም የማቀው ነው"አለና መምህር ደረጄ የቀዳማዊን ታሪክ አንድ በአንድ ነገራቸው። ተማሪዎች በተመስጦ አንገታቸውን ጠንዘል አድርገው ያድምጡታል። ከመሀል አንዳንድ ተማሪዎች ቀዳማዊ የደረሰበትን በእህቶቹ የደረሰበትን ስቃይ በእናቱ የተደረገበትን ግፍ ሲናገር ያለቅሱ ነበር። "በመጨረሻ ያ ሁሉ አልፎ አሁን በአለም ላይ በስራው አንቱታን ካተረፈና እውቅናን ከተቸረ ሎሳንጄለስ ኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ በዋና መሀንዲስነት እየሰራ በሺህ የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር እየተከፈለው በደስታና በስኬት እየኖረ ነው" "መምህር በቅርቡ በቴሌቪዥን ቀርቦ መምህር ደረጄን አገናኙኝ ያለው ነው?" ብሎ አንዱ ተማሪ ንግግሩን አቋረጠው። "አዎ በትክክል አይተኸዋል። እሱ ነው ቀዳማዊ ማለት። ልጁ እንደስሙ ቀዳማዊ ነው። አሻራዎቹ በሙሉ በስኬት የተሞሉ በገዛ ቤተሰቦቹ እኖደ እሳት የተፈተነ ልጅ ነው። እኔን ያፈላለገኝ በወቅቱ ምንም አድርጌለት ሳይሆን ግን በሀሳብ እደግፈው ስለነበር ነው። የተወሰኑ ቀናትም ከእኛ ጋር ሆኖ ለመማር ሞክሮ ነበር ያው እንደነገርኳችሁ እናቱ የማስተማር አቅም ከሌላት በሚል ሀሳብ። እና ያቺን እንደ ትልቅ እገዛ ቆጥሯት ነው እኔን ለምስጋና ያፈላለገኝ። ስለዚህ እናንተም በየራሳችሁ እስካሁን ምን አይነት ሕይወት እንደገጠማችሁ እና እንዳልገጠማችሁ አላውቅም። ግን የምነግራችሁ ነገር ያሻውን በሕይወታችሁ መከራ ቢበዛ ተስፋ ቆርጣችሁ የሰይጣን መጫወቻ እንዳትሆኑ። የሕልማችሁ ተራራ ጫፍ ላይ እስክትደርሱ መታገል መፍጨርጨር አለባችሁ።" አለ መምህር ደረጄ እንባው በአይኑ እየሞላ። በዚህ ጊዜ ነበር የእሱ ክፍለ ጊዜ አልቆ የሌላኛው መምህር ክፍለጊዜ ደርሶ ሌላኛው መምህር በሩን ያንኳኳው። "በሉ የዛሬውን ክፍለጊዚያችን በሌላ ጊዜ እናካክሰዋለን መልካም ትምህርት ይሁንላችሁ "ብሎ ትቷቸው ወጣ። መምህር ደረጄ ለተማሪዎቹ ስለቀዳማዊ በመናገሩ ኩራት ተሰማው። ከቀዳማዊ የሕይወት ታሪክ ተምረው ራሳቸውን ለተለያዩ ስኬትች እንደሚበቁ አመነ። በሌላ በኩል ደግሞ ቀዳማዊ ያን ሁሉ ፈተና ተቋቁሞ ለዚህ ለሌሎች ሕይወት ማስተማሪያ በመሆኑ ፍፁም ደስታ ተሰማው።
***
ከአንድ አመት በኋላ
ራስ አምባ የገጠር ቀበሌ ከወትሮው ልዩ ሆና አሸብርቃለች። ኮረኮንች መንገዷ ሁሉ ተስተካክሏል። መልካሙ በቀዳማዊ የተጣለበትን ኃላፊነት ስለመወጣቱ ስራው ምስክር ሊሆነው ይሄው ሁሉንም ነገር አጠናቆ የእንግዶቱን መምጣት ብቻ ይጠባበቃል። በርካታ ገንዘብና ጉልበት የወጣበት ፕሮጀክት ስራው ተጠናቆ ለጎብኝዎቾና ለተጠቃሚዎች ክፍት ሊሆን በእንግዶች ተመርቆ በይፋ መከፈት ብቻ ይቀራል።ቀዳማዊ፣ሐምራዊ ወይዘሮ ሔዋንና አቶ ሙሉሰው ወይዘሮ ፊደላዊትና አቶ ሱራፌል ሐመረ ኖኅ የአየር ማረፊያ ወርደው በተዘጋጀላቸው መኪና ወደ ራስ አምባ ቀበሌ ያመሩ ጀመር። ቀዳማዊ ፈገግ ብሎ "ይችን ትመስላለች እንግዲህ የተወለድኩባት አካባቢ"አለ ለሁላቸውም እያሳዬ። መልካሙ (አቤል) ሳቅ አለና "ያው ተወለድክባት እንጅ ብዙም አታውቃትም"አለ "አይ ወንድሜ ከዛ በላይ እንዴት ልወቃት ለአስራ ሁለት አመት ነው ለአስራ ሶስት አመት ኖሬባታለሁ "አለና "ያው ኑሮ ከተባለ"አለ በለሆሳስ ማናቸውም ሳይሰሙት "አይ በጣም ገጠር ነች። እኔ እኖደውም አንተ ያጋነንክ መስሎኝ ነበር። በጣም ገጠር ነች ስትለን"አለች ሔዋን። " "አዎ እትዬ በጣም እንጅ አሁን ነው እንጅ መብራት ምናምን የተገጠመላት በእኛ ጊዜ መብራት አናውቅም። ስናጠና ራሱ በኩራዝ ነበር"አለ ቀዳማዊ። ሐምራዊ ትንሽ ደከም ብሏት ቀዳማዊን ተንተርሳ የሚያወሩትን በጥሞና ታዳምጥ ስለነበር " የትም ይሁን የትም ዋናው ራስን ለትልቅ ደረጃ ማብቃቱ ነው ትልቁ ቁምነገር"አለች የቀዳማዊን ስኬት በመተማመን ፊደላዊት የልጇን ሀሳብ በመደገፍ "ልክ ነሽ ሐምራ ግን ተመችቶሻል?"አለች "አዎ እማዬ እኔም ልጄም የቀዳማዊን ሰውነት ተንተርሰን ምን እንሆን ብለሽ"አለች። ሐምራዊ ልትወልድ በቢዛ የወር እድሜ የቀራት ነፍሰጡር ነች። ቀዳማዊ አብራው እንዳትመጣ ብዙ ጠይቋት ነበር። ብቻህን አልልክህም ብላ እምቢ ስላለችውና በዚህ ትልቅ ቀንህ ከጎንህ መሆን እፈልጋለሁ ብላው ነው አብራው ለመምጣት የቆረጠችው። ወይዘሮ ፊደላዊትና አቶ ሱራፌልም በዚህ ልዩ ቀንህ አብረንህ ልንሆን ይገባል"ብለው ወዲህም ሐምራዊን ለመንከባከብ አብረው ለመምጣት የወሰኑት። ሔዋንና ሙሉሰውም ልጃችንን ብቻውን አንልከውም በማለትና ያሰራውን ስራ በአይን ለመመልከት እዚሁ ራስ አምባ ድረስ ለመምጣት የወሰኑት። ቀዳማዊ በሁላቸውም አብረውት ስለመጡ በጣም ደስ ብሎታል። ቀዳማዊ ሐምራዊን በፍቅር እየተመለከተ ከቆዬ በኋላ "ልጃችን እንዴት ነው"በማለት በቀኝ እጁ ሆዷን እየዳበሰ ጠየቃት። "ልጃችን በጣም ደህና ነው የኔ ፍቅር"አለችና አንገቱ ስር ሳም አደረገችው።
ከራስ አምባ ቀበሌ ደርሰው ከወረዱ በኋላ ቀጥታ ወደ ቀይ አፈር የገጠር ቀበሌ አመሩ። ሙሉቀን ከዳስሽ ጋር ሆነው ቀኑን ሙሉ ቤቱን ሲያስተካክሉና ሲያስውቡ እንዲሁም የእንግዶቹን ማረፊያ መደቦች በፍራሽ ሲያነጥፉ ነበር።ቤቱ በጭራሽ የገጠር ቤት አይመስልም ነበር። ቀዳማዊ የቤት ማሰሪያ ብሎ የሰጠውን ሀምሳ ሺህ ብር በጥሩ ሁኔታ በድንጋይና በጭቃ እንዲሁም በቆርቆሮ ጣሪያ ሰፊ ደርብ ቤት ሰርተዋል። ለአቶ ሱራፌልና ፊደላዊት አንድ የጠፍር አልጋ ላይ አዘጋጁላቸው። ለወይዘሮ ሔዋንና ለአቶ ሙሉሰውም እንደዚሁ የጠፍር አልጋ። ለእነ ሐምራዊና ቀዳማዊ ደግሞ ሰፊ መደብ ላይ ፍራሽ አንጥፈው አሳረፏቸው። ገና ከመግባታቸው ሙሉቀንና ዳሳሽ የተሰራውን የምግብ አይነት ካልበላችሁ ብለው ሲሞግቷቸው ቆዩ። ምንም እንኳ የቻሉትን ቢበሉም ነገር ግን ለነ ሙሉቀን መብላታቸው አልታያቸውም ነበርና በሞቴ አፈር ስሆን እያሉ ከእርጎውም ከስጋውም ከሁሉም እያቀረቡ ይለምኗቸው ጀመር። ሔዋንና ሙሉሰው ተገርመው ዝም ብለው ይመለከቷቸዋል። ፊደላዊትና ሱራፌል በደስታ እየበሉ እየተጨዋወቱ ነው። በመጨረሻ ጠግበው ማዕዱ ተነሳ። "እስኪ ዳሳሼ ወገሜት አሙቂላቸው እሱን ትንሽ ቢጠጡ "አለ ሙሉቀን።
@amba88
@ken_leboch