Get Mystery Box with random crypto!

' ኤሴቅ ' ክፍል ~፪፻፳፰~ ( 228) በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888 ሐምራዊ ገና በውል ከ | ቅን ልቦች

" ኤሴቅ "
ክፍል ~፪፻፳፰~ ( 228)
በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888
ሐምራዊ ገና በውል ከእንቅልፏ ሳትነቃ አይኖቿን በስሱ እንደገለጠች "ፍቅሬ ደወሉልኝ እኮ"አለ ቀዳማዊ "እነማን ናቸው እነሱ"ብላ ተገላብጣ ተኛች። "እነ መምህር ደረጄ ናቸዋ!" "መምህር ደረጄ ማነው?"ሐምራዊ አይኖቿን ከድና ከንፈሯን እያሸራመጠች ጠየቀችው። ሳቅ ብሎ ቀዳማዊ በዚህን ጊዜ ነበር ሐምራዊ በትክክል እንዳልነቃች ያወቀው።"አይይ ዝም ብዬ እለፈልፋለሁ አይደል"አለና የስፖርት ቱታውን ለብሶ የቤቱ ጊቢ ውስጥ ቀለል ያለ ስፖርት ይሰራ ጀመር።
***
የሌሊቱ ጨለማ በርኖሱን ከምድር አላነሳ ብሎት፣ አይኖቹ እንቅልፍ በአጠገባቸው ሳያልፍ ከቤቱ ጣራ ጋር እየተነጋገሩ ነው ያነጉት። ከአንድ ጊዜም ሁለት ጊዜ እየወጣ የሰማዩን ምስራቃዊ ክፍል ገላ ይመለከታል። ፅሐይ በስታው እንድትወጣ እየተመኘ የሰማይን ሽንቁር ገላ ከመቅፅበት ለመመልከት እየቋመጠ ቢቆይም ሰማዩ ግን በከዋክብቶቹ ደምቆ የፅሐይን መውጫ ስአት ያዘገየው ጀመር። ቢጨንቀው የክፍሉ በረንዳ ጋር ሆኖ ሰማዩ ላይ እንደ ዛር ቆሎ የተበተኑትን ከዋክብቶችን ይመለከትም ይቆጥርም ጀመር። ታሮስ የኮከቦችኖ ብዛት ለማወቅ አይደለም የመቁጠር ግቡ.. ምን አልባት አስር ኮከቦችን ሲቆጥር አስር የሌሊት ደቂቃዎች ቢያልፉልኝ ብሎ እንጅ። ሆዱ በፍርሀት ኮረኮንች እንደበዛበት መንገደኛ የሕዝብ አውቶብስ እየተንገጫገጨ ያስቸግረዋል። ልቡ ልትወጣ ቀዳዳ የምትፈልግ ይመስል በሁሉም የሰውነት ክፍሉ ትመታለች።
ፍቅር ውስጥ ስንሆን እያንዳንዷ ነገር ትነካናለች። ሆደ ቡቡ እንሆናለን። ፍቅራችንን ብቻ እያሰብን እንኖራለን።የአንድ ደቂቃ ርዝማኔ ያስለፈልፈናል ያፈላስፈናል።ለሁሉም ነገር እንቸኩላለን በፈጥነት እንዲሆንልንም እንመኛለን! ነገ ያጓጓናል። ሁሉም ነገር በበጎ ምልከታ ብቻ ይታየናል።
***
"ፍቅር በምሽት ውስጥ በጨለማ ውስጥ ለተቀመጠ ሰው የሚታይ የተስፋ ጭላንጭል ብርሃን ነው። ብዙዎች ስላፈቀሩ ብቻ ነገን መኖር ይጓጓሉ። መፈቃቀር የሁለት ጥንዶች የልብ ቋንቋ አንድነት ምስጢር ሲሆን! ማፍቀር ደግሞ የተፈጥሮ እውነትና የልብ ቅፅበታዊ ድርጊት የሚፈጥረው ደስ የሚል ስሜት ነው። አሁን በፍቅር ከትላንቱ የተሻለ ዛሬን ከዛሬ የተሻለን ነገ መኖር ያስችላል። በፍቅር ውስጥ ሙሉነት አለ።"አለ ኪሩቤል የታሮስን የሰርግ ሱፍ ገዝተው ሻይ ቡና እያሉ ተቀምጠው ሳለ። "ከሚገርምህ አንተ ብቻ አይደለህም ከምታፈቅራት ሴት ውጪ ሌላ አለምን ማየት የማትፈልገው። ሁሉም የራሱ የፍቅር ጠባሳ አለው። ተመልከት ይሄ ሁሉ ተጓዥ መንገደኛ የራሱ የሆነ ሕመም ቁስል የፍቅር ችግር ይኖርበታል። አንተ ከጤፍ እህል ብዛት ነጥረህ ወጥተህ የምታፈቅራትን ሴት ልታገባ ነው። በዚህ ልትደሰት እንጅ ልታዝን አይገባም። በምንም ታዕምር አንተን ቀዳማዊን ለመርሳት ብቻ የምታገባህ መስሎህ ከተሰማህ ችግሩ የአንተ እንጅ የእሷ አይደለም!! አምናለሁ ቀዳማዊን ትወደዋለች ግን ያለፈ ታሪክ ነው። አሁን ሁለታችሁም ሌላ አለም የራሳችሁን ድንቅ የፍቅር ፕላኔት ልትፈጥሩ ነው። ከዚህ በላይ ደግሞ ደስታ የለም"ብሎ ትከሻውን መታ መታ አደረገው። ታሮስ በጥሞና ሲያዳምጠው ከቆዬ በኋላ "አመሰግናለሁ ኪሩዬ ከዚህ በላይ ምን ልልህ እንደምችል አላውቅም። ሁሌም ከጎኔ ሆነህ የሚበጀኝን ሀሳብ ትሰጠኛለህ። ብቻየን እንዳልሆን አድርገኸኛልና አመሰግናለሁ!!!" በእኔና ባንተ መሀል ያለምስጋና የሚሰበር ድልድይ የለም። እኔና አንተ በመነጋገር እና የግል ችግሮቻችን ላይ በጋራ እልባት መስጠት እንጅ መመሰጋገን የለብንም። ካልሆነማ ምኑን ጓደኛሞች ሆነነው?"ብሎ በጥያቄ መልስ ሀሳቡን ገለፀለት።
**
"ሁሌም ካፋችን ጠፍተህ አታውቅም! በተለይ ደሬ እንደው የት ሀገር ሆኖ ይሆን እያለ ያብሰለስል ነበር"አለች ትሕትና "አውቃለሁ እትዮ መቼም ከውስጣችሁ እንደማልወጣ። በዛ situation (ሁኔታ) ውስጥ ሆኜ ራሱ ሁሌም ነበር የማስበው። በእውነት እናንተን ለማግኘት ያላደረኩት ጥረት አልነበረም። አሁን ራሱ በቃ ግራ ግብት ሲለኝ ነው ባለቤቴ በቴሌቭዥን ና በሬዲዮ እናፈላልጋቸው ስትለኝ ሀሳቧን የተቀበልኩት" "በጣም ጥሩ ነው። ማግባትህነም በዛው ቃለመጠይቅ ስታደርግ ሰማን። በጣም ነው ደስ ያለን ልጄ እንኳን ደስ አለህ!"አለች ትሕትና ፍፁም ትሕትና በተሞላው አነጋገር!!! "አመሰግናለሁ እትዬ ቀደም ብለን ብንገናኝ ኖሮ የደስታዬ ተካፋይ ትሆኑ ነበር። ግን እግዚአብሔር አልፈቀደም" "አዎ ሁሉም ነገር የሚሆነው እሱ ሲፈቅድ ብቻ ነው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ብዙ የምንካፈላቸው የደስታ ጊዚያቶች አሉን"አለች ትሕትና "እውነት ነው እሱስ ገና መች ጀመርነው። እኖደው እዚህም ብትገኙልኝ ብዬ ነው እንጅ። የት ነው የምትኖሩት አሁን?"" ኮምቦልቻ ነን ወደዚህ መጥተናል!" በጣም ጥሩ በቃ መጥቼ እጠይቃችኋለሁ!! እስከዛው ግን እንደዋወላለን"አለ ቀዳማዊ ተባብለው ጨዋታቸውን ጨርሰው ሲዞር ሐምራዊ ከጀርባው ቀስ ብላ እየተራመደች ልታስደነግጠው ስትል አያት። "ኤጭ ሳታስበው ላቅፍህ ነበር ቀረብህ" "አይ አይቀርብኝም እርግቤ"አለና ግራ እጇን ሳብ አድርጎ ስሞ ጭኑ ላይ አስቀመጣት።"አሁን ስታወራ እየሰማውህ ነበር። በእንቅልፍ ልቤ ቢሆንም ቅድምም ሰምቼሀለሁ። በጣም ነው ደስ ያለኝ የኔ ፍቅር! አሁን ሁሉንም አግኝተሀል አሳክተሀል!!! ስለዚህ ከዚህ በኋላ ትንሽ አትጨናነቅብኝ"አለችና አቅፋ ወደ አንገቷ ሸጎጠችው። አንገቷን ሳም አደረገና "በትክክል ሁሉንም አግኝቻለሁ ግን አንድ ነገር ብቻ ነው የቀረኝ። ግን ምን እንደቀረኝ እንዳትጠይቂኝ!"አለ ቀዳማዊ "እንዴ የኔ ፍቅር ካልፈለክማ ለምን እጠይቅሀለሁ። ነገር ግን ብትነግረኝ ደስ ይለኛል!"አለች ሐምራዊ እየተቅለሰለሰች "ፍቅር ሲሳካ እነግርሻለሁ"
***
"በጣም ልዩ ሁነሻል የኔ ወርቅ!!"አለች ትዮቢስታ ደሐብን ትኩር ብላ ስትመለከታት ከቆየች በኋላ። ደሐብ ፈገግ አለችና "አዬ እማዬ ልጅ ሁሌም ለእናትና አባቱ በጣም ቆንጆና ልዩ ነው። ግን የትንንንሾች ውበት ከቤተሰብ አይን አልፎ በሌሎች አይንም ያርፋል!" አለች ደሐብ በመስታውት ራሷን እየተመለከተች። "እኔ ልጄ ስለሆንሽ አይደለም ቆንጆ ነሽ ያልኩሽ ቆንጆ ስለሆንሽ ነው። ውበትሽንና ቁንጅናሽን ደግሞ ያየ ሁሉ የሚመሰክረው ነገር ነው" አለች ትዮቢስታ ከጀርባዋ በኩል ያለውን ቀሚሷን እያስተካከለችላት። ደሐብ ምንም አልመለሰችላትም። በዝምታ ውስጥ ሆና ራሷን ታስውብ ጀመር። ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ጓደኞቿ፣ ሚዜዎቿ እና ሜካፕ የሚሰሩት ልጆች አንድ ላይ መጡ። ወደ ደሐብ ክፍል ገቡና ሜካፕ ሰሪዎቹ ተከፋፈሏት። አንደኛዋ የእግር ጥፍሯን ሌላኛዋ የእጇን ጥፍር ሌላኛዋ ደግሞ ፊቷን ተከፋፍለው ያስውቧት ጀመር።
'የፉክክር ሰርግ አስመሰለው' ተብሎ እስኪታማ ድረስ እዮሲያስ ሰርጉን ከሰርግነት ደረጃ አስወጣው። በጣም ቅንጦት የተቀላቀለበት ድግስ ነበር። ሙሽራዋም ውዱን የሙሽራ ቬሎ ለብሳለች። እዮሲያስና ትዮቢስታ ለአንድ ልጃቸው ያላቸውን ጉልበትና ገንዘብ ሁሉ አውጥተው ሞሽረዋል።

@amba88
@ken_leboch