Get Mystery Box with random crypto!

' ኤሴቅ ' ክፍል ~፪፻፳፮~ ( 226) በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888 ደሐብ ከታሮስ ጋር በ | ቅን ልቦች

" ኤሴቅ "
ክፍል ~፪፻፳፮~ ( 226)
በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888
ደሐብ ከታሮስ ጋር በሰከነ መንፈስ ስለ ሁሉም ነገር በግልፅ ካወሩ በኋላ ለሰርጋቸው ቤተሰቦቻቸው እንዲዘጋጁ ለመናገር ተስማሙ። "እኔ አንተን የማገባህ ቀዳማዊን ለመርሻነት አይደለም። የማገባህ ቆሜ እንዳልቀር ፈርቼ አይደለም። የማገባህ እናትና አባቴ ማግባት ይኖርብሻል ብለው ስላስገደዱኝ አይደለም። የማገባህ የእኔን እውነተኛ ፍቅር በአንተ ልብ ውስጥ ስላገኘሁት ነው። ፍቅር በሰጡት ልክ መስጠት እንዳልሆነ አሳይተኸኛል። አንተ ስትሰጠኝ የነበረው በሰጠውህ ልክ አልነበረም። እንደው በተቃራኒው ነው። በራኩህ ቁጥር እየቀረብክ በጠላውህ ጊዜም እየወደድክ ዝም ባልኩህ ጊዜም እያወራህ ፍቅርህን አሳይተኸኛል።ለእኔ የሚያስፈልገኝ እሱ ነው። አንተ የእኔ እውነተኛ አፍቃሪ ነህ። እሱን ደግሞ ድርጊቶችህ ሁኔታዎችህ ነግረውኛል። ስለዚህ አንተ የልጆቼም አባት የእኔም ባልና ጠባቂ መሆን ስለምትችል ከአንተ ጋር በፍቅር ኑሮ መመስረት እፈልጋለሁ"አለች ደሐብ የታሮስን የግራ እጅ መዳፍን እያሻሸች። ታሮስ ስቦ ወደ እቅፉ አስጠጋትና "በቅርቡ የራሳችንን ቤተሰብ እንመሰርታለን"አለና ግንባሯን ሳማት። ደሐብ ልስልስ ኩርምት ብላ ዝናብ መትቷት ከብርድ ለማምለጥ ዋሻ ውስጥ እንደ ተሸጎጠች ፍየል ደረቱ ውስጥ ሰርስር አድርጋ ተሸጎጠች።
በደሐብ መወላወል ምክንያት የተቆረጠው ቀን ከአንድ ጊዜም ሁለቴ ስለተቀየረ የታሮስ ቤተሰቦች ትንሽ ቅር ተሰኝተው ነበር። "ልጃችንን እንዳትጎዳብን እንጅ ብለው እስከመጨነቅም ደርሰው ነበር። በዚህም ምክንያት ሽማግሌዎቹን ደግመው በመላክ ያለውን እውነት እንዲያጣሩ ቢልኩም አጥጋቢ መልስ አላገኙም ነበር። ታዲያ አሁን በድጋሚ ያለውን ነገር ሲነግራቸው እንደማቅማማት ቢሉም ደግሞ የእሱን ደስታ ማክበር ስለነበረባቸው ተቀበሉትና ለመጨረሻ ጊዜ ሽማግሌ ልከው ቀኑ ተቆረጠ። ይህም ቀን ከሁለት ወር የማይበልጥ ርዝማኔ ያለው ነበር።
****
የድንጉዛዋ እመቤት የፍቅር መለይካዋ የምድር ገነቷ አርባ ምንጭ የፍቅሯን ሞሰብ ለመክፈት ለመጡ ሁሉ በደስታ ከፍታ ማዕዷን በበረከት የምታቋድስ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ለመጣ እንግዳዋ ቤቷን ክፍታ አድርጋ እጆቿን ዘርግታ ከምድር እስከ አርያም በሚልቅ ባልተበረዘና ከልብ በመነጨ ንፁህ ፈገግታዋ "ሀሹ ሳሮ ይዴታ"ብላ ተቀብላለች። ዛሬም ፍልቅልቋን ሐምራዊና ገራገሩን ቀዳማዊ ከማይነጥፈው ማድጋዋ ፍቅሯን በአንደበቷ ሞልታ ተቀብላቸዋለች አርባምንጭ እንደደረሱ ቀጥታ አዲስአበባ ሆነው ከያዙት ሆቴል አረፉ። በሁለት ሀይቆች ተከባ የፅሀይን መዳረሻ ከሰማይ አርቃ ለምድር ያቀረበችው ሞቃታማዋ አርባምንጭ በብዙ የተፈጥሮ መስህቦች የተሰበዘች ሰበዝ ሆና ሙቀቷን እስከ ማስረሳት ታደርሳለች
በጥቅጥቅ ደኖቹ መሀል ከፈለቁት ምንጮች ስር እንደ አሳ ሁሪት እየተስለከለኩ ይዋኛሉ። የዛፉቹ ኮሽታና ቅጠሎቹ ከዛፉ ሲወርዱ የሚያሰሙት የለሆሳስ ድምፅ ከጫካ ወቹ የወፎች ጫጫታ ተዳሞሮ ነፍስን የገነት በር እያደረሰ ይመልሳል። ሊያስጎበኟቸው የመጡ ሁለት የሰማይ ስባሪ የሚያህሉ ወጥማሻ ባለ ፈርጣማ ክንዶች ዙሪያ ገባውን እያማተሩ ከምንጮቹ ዳር ካለ አንድ ዛፍ ስር ተቀምጠዋል። ሙሽሮቹ ምንጩ ውስጥ እንደ ህፃን ልጅ እየተደፋፈቁ እስኪበቃቸው ከዋኙ በኋላ ራሳቸውን አደራርቀው ልብሳቸውን ለባብሰው ወደ ሌላ የሚጎብኝ ስፍራ ጉዟቸውን ጀመሩ። በያገኙበት ስፍራ ሁሉ ፎቷቸውን እየተነሱ የእግዜር ድድልድይን የነጭሳር ብሔራዊ ፓርንክን የአዞ እርባታን በየተራ ሁሉንም አንድ በአንድ ሲጎበኙ ቆይተው ተመለሱ። አስጎብኝተው ለጠበቋቸው ሰዎች ከጉርሻ ጋር ጨምረው አመስገነዋቸው ተለያዩ። የአርባምንጭ ቆይታቸውን አጠናቀው ሐዋሳ ደግሞ ድንቅ ጊዚያትን አሳልፈው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።

**
ታሮስና ደሐብም ለመጋባት ሽር ጉድ እያሉ ነው። አቶ እዮሲያስ ሰርጉን የተለዬ ለማድረግና ከማንም የተሻለ ሰርግ እንዲሆን እየጣረ ነው። በርካታ የሚያውቁት ሰዎችና የስራ ሸሪኮቹ ብዙ አውራጅ ይዘው ቀርበዋል። በርካታ ሰንጋ ለእርድ ቀርቧል። አቶ እዮሲያስ ደደሐብ በምንም ታዕምር ያነሰች፣ የተጣለች፣ የተገፋች፣ እንዳይመስላት በበርካታ መንገዶች ሊሸፋፍን ይጥራል። የጥሪ ካርድ ለሁሉም ተብትኗል ከሚታወቁ ሰዎች ካልተጠሩት መካከል አቶ ሙሉሰው አንዱ ነው። ይህን ያወቀው ሙሉሰው ሳቅ አለና "ከሚገርምሽ እኔ ቢጠራኝም አልሄድም ነበር"አለ " እንዴት ጠርተኸው ሳይመጣ የቀረ ሰው ለልጁ ሰርግ ይጠራኛል ብለህ ታስባለህ"አለች ሔዋን "ኧረ በእውነት መጥራትስ ይጠራኛል ብዬ ገምቼ ነበር። ግን ይሄን ያህል ይወርዳል ብዬ አላሰብኩም ነበር!"አለ ሙሉሰው
****
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የምሽት ሁለት ስአቱን ዜና ጨርሶ በርካታ ማስታወቂያዎችን እየተመለከቱ እያለ የሆነ ቃለመጠይቅ ሲመጣ ዮአኪን አሳለፈው "ተወው እንጅ መልሰው እስኪ ቃለመጠይቁ ምንድን ነው እናዳምጠው "አለች ትሕትና "እስኪ ወቅቱን ንገረን መቼ ነው?" ጋዜጠኛው ይጠይቃል "ልጅ ነበርኩ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነው ተቀይሮ ሌላ ቦታ የሄደው። በእኔ ምክንያት ነው ስራ የለቀቀው!!" አለ ቀዳማዊ "እስኪ ማስተላለፍ የምትፈልገውን መልዕክት ተናገር"ብሎ ጋዜጠኛው ለቀዳማዊ እድል ሰጠው። "መምህር ደረጄ ይባላል አስተማሪዬ ነበር ባለቤቱ ወይዘሮ ትሕትና ትባላለች። እኔ ቀዳማዊ ታረቀኝ እባላለሁ ይህን ቃለመጠይቅ ይምታዩ ሁሉ እነ መምህር ደረጄን አገኝ ዘንድ እርዱኝ! ከዚህ ቀጥሎ በሚገኘው ስልክ ብትደውሉ ታገኙናላችሁ"አለ ቀዳማዊ እንደ ሕንዶች ሰላምታ እጆቹን አገናኝቶ ወደ ግንባሩ አስጠጋ። እንግዲህ ይህን መልዕክት የምታዩ ሁሉ እንድትተባበሩት እኔ በአክብሮት እጠይቃለሁ። እኔና አንተ በዚሁ ጨዋታችንን እንቀጥልና "በቅርቡ ነው ትዳር የመሠረትከው ትዳር እንዴት ነው?" "ትዳር በጣም ጥሩ ነገር ነው። በተለይ ሁለት የሚፋቀሩ ሰዎች ትዳር ሲመሰርቱ ጎጆ ሲቀልሱ ይበልጡን ከወትሮው በበለጠ ይፋቀራሉ ይግባባሉ።ስለዚህ በእኔ እይታ ትዳር የላላ የፍቅር ገመድን የሚያጠብቅ ሲባጎ ነው ማለት ነው። እኔና ሐምራ አሁን ገና ትዳርን እየጀመርን ነው። የሁለታችንም የትዳር ሞዴሎች አሉን እነሱን እያየን ስለሆነ እኛም ሞዴሎች የማንሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም።" ጥሩ አሜሪካን ሀገር የምትሰራበት የኮንስትራክሽን ድርጅትም እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርንጫፍ ከፍቷል። የዚህ ቅርንጫፍ ዋና ስራ አስኪያጅና ዋና መሀንዲስ አንተ እንደሆንህ መረጃው አለኝ እና ምን ለመስራት አቅደሀል?" "ያው ሀገራችን በርካታ የምህንድስና ወለድ ድጋፎች እንደሚያስፈልጓት እሙን ነው። አሁንም መንገዶች ሆስፒታሎች ትምህርት ቤቶች የህዝብ መኖሪያቤቶች ያስፈልጋታል ከጠቀስኩልህ ውጭም ጊዜን የሚቆጥቡ ድልድዮችና ግድቦች ያስፈልጓታል። እና ሀገራችን በሚያስፈልጋት ሁሉ እኔም እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚጠበቅብኝን የምወጣ ይሆናል ማለት ነው" .....

@amba88
@ken_leboch