Get Mystery Box with random crypto!

' ኤሴቅ ' ክፍል ~፪፻፳፫~ ( 223) በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888 'እና ደሐብ ስለ ዶስ | ቅን ልቦች

" ኤሴቅ "
ክፍል ~፪፻፳፫~ ( 223)
በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888
"እና ደሐብ ስለ ዶስቶቭስኪ ልንገርሽማ በእርግጠኝነት ስለ እሱ ታውቂያለሽ። በጣም የሚገርምና በአለም ላይ የሚታወቅ ከያኒና ደራሲ ነው። በዛ ላይ የምትወጃት ሀገር የሩሲያ ፍሬ ነው"አለና ወሬ በማስቀየር የታሮስን ሀሳብ እንድትረሳው አደረጎ ታሮስን ከእግር እስከራሱ እየገላመጠ። ታሮስ ጥፋት እንደሰራ የገባው ኪሩቤል ሲገላምጠው ነበር። "አዎ በደንብ አውቀዋለሁ እንጅ የሩሲያው ሼክስፔር የስነፅሁፍ ራስ አይደል። የፅሁፎቹን ይዘት ሁሌም ሳነብ በጣም እገረማለሁ። በተለይ "notes frome the underground "የሚለው መፅሐፉ ይበልጥብኛል"ብላ ስለ መፅሐፉ አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጠች። "አዎ ልክ ነሽ እኔም እንደ ዳዊት ሁሌ ነው የምደጋግመው ሲያልቅብኝ እናደዳለሁ"አለና ኪሩቤል እዛው የመፅሐፍ ሙድ ውስጥ እንዳለች የሌላኛውን አስገራሚ የስነፅሁፍ ሰውና ተዋናይ ኮሜዲ ቻርለስ ቻፕሊንን ቃኘት አደረገላት። "ቻርሊ በጣም ቀልደኛ ነገር ግን በዛው ልክ ደግሞ ቁምነገረኛ ነው"ብሎ ሀሳቧን እንድትሰጥ በር ከፈተላት። "በተለይ ኪሩ እሱ ሰውዬ አልፎ አልፎ የሚፅፋቸው ግጥሞች በጣም ነው የሚገዙኝና የምወዳቸው አሁን ለምሳሌ "the mask"በሚል አርዕስት የፃፋት ግጥም ግሩም እኮ ነች።#The_Mask የምትለዋ
First I say,
“How do you do?"
And lift my hat
and wink at you
.
But you mustn't
clap too loud
I'm so modest
in a crowd."ብላ ደሐብ በቃሏ አነበበቻት። ኪሩቤል በዚህ ጊዜ ፈገግ አለና በነገርሽ ላይ ይቺን ግጥም እኔው በራሴ አገላለፅ ወደ አማርኛ ቀይሪያታለሁ"አለ "እና አታነብልኝም?"አለች። "ሳትጠይቂኝ ነበር የማነብልሽ ማስታወሻዬ ጋ ነው። ስልኬ ላይ አላሰፈርኳትም። ዝም ብዬ ቢሮ በሆነ ሀሳብ ውስጥ ሆኜ ግጥሟን እያነበብኳት ከሰውየው ባህሪም ጋር በተወሰነ መልኩ በማናፀር ነው የተረጎምኳት""ዋው ደስ ይላል"አልችና ወደ ቤርሳቤህ ዞር ብላ "የኔ ቆንጆ በጣም አምሮብሻል ኪሩቤል አፈር አይንካሽ እያለ ነው መሰል የሚንከባከብሽ?"አለች ፈገግ ብላ "አዎ በደንብ ነዋ። ይሄው መሬቱን በእግሯ ከረገጠችው ቆይታለች። በስንት ጊዜ በቃ በእግሬ መሄድ እፈልጋለሁ መራመድ ናፍቆኛል ባለችው መሠረት ነው ዛሬ በእግሯ ያመጣኋት"አለ ኪሩቤል እየሳቀ "ኧረ ባክህ ወሬኛ አልቀረብህም። ከሚገርምሽ ስራውን ብነግርሽ ታፍሪበት ነበር። የሚያቅፈኝ እኮ የሆነ ነገር ሲያምረው ነው። ልክ ክፉ ላስ ወይ ቤት የሄድን እንደሁ እግራችን ቤቱን እንደረገጠ እቅፍ አድርጎ ቀጥታ ወደ አልጋ ነው የሚወስደኝ"አለች። "ይሄም ጥሩ ነገር ነው። እሱ ስለሆነ ነው ያደረገው ሌላ ቢሆን ማን ያደርገዋል?"አለችና ደሐብ በፈገግታ ኩም አድርጋ አቀፈቻት። ታሮስ ባደረገው ነገር እንደ መሸማቀቅ ብሎ በዝምታ ይመለከታቸዋል "የኔ ፍቅር ምነው ዝም አልክ?"አለች ደሐብ የታሮስን ፂም እየነካካች። "እ ምንም እንዲሁ እናንተ ወሪያችሁን እስክትጨርሱ እየጠበኩና የማነሳውን ሀሳብ እያሰብኩ ስለሆነ ነው"በማለት ቆጠብ ብሎ ተናገረ። "ዝም ስትል ይጨንቀኛል። ፈታ በል በደንብ ተጫወት እሺ ጌታዬ"አለችና ጉንጩን ሳም አደረገችው። ኪሩቤልና ቤርሳቤህ ተያዩ።
**
"እንዲህ ያለም የለ። በጣም ነው የምናመሰግነው እትዬ። ይሄን ያህል ቀን ተስማምቶን ነው የቆየን እግዚሐር ይስጥልን"አለ ሙሉቀን ጎንበስ ብሎ። ሙሉሰው በነ ሙሉቀን ስርአትና የቃላት ጥንቃቄ እየተገረመ "እናንተ ቤተሰቦቻችን ናችሁ እኛም እንደዛው። ቀዳማዊ አስተሳስሮናል። ስለዚህ በክፉም በደጉም አብረን ነን። እኛም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መጥተን እንጠይቃችኋለን"አለ ሙሉሰው። ሔዋን ሻንጣ ሙሉ ልብስና አንዳንድ የሚያስፈልጉ ነገሮችን አዘገጃጅታ "ልጃችሁን ሳሙልኝ። ወላጆቻችሁንሞ ሰላም በሉልን"አሉና ተሳስመው መኪና ውስጥ አስገቧቸው። "በቃ አይዟችሁ እንዴ በቅርቡ መሄዳችን አይቀርም የሆነች ነገር የምንጎበኛት ነገር አለች"አለ ቀዳማዊ እነ ሙሉቀንንና ሔዋንን በየተራ እየተመለከተ" በሉ እሺ በሰላም ግቡ ፈጣሪ ከእናንተ ጋር ይሁን"አለና ሙሉሰው እጁን አውለበለበላቸው። ሔዋንም መልካም ምኞቷን ገልፃላቸው ተሸኛኙ። ቀዳማዊ እና ሐምራዊ እነ ሙሉቀንን እያጫወቱ ኤርፖርት አደረሷቸው።"ወንድሜ በዚህ የደስታ ቀኔ አብረኸኝ ስለሆንክ በጣም ደስ ብሎኛል።"አለና ቀዳማዊ አቀፈው። "እኔም ወንድሜ በጣም ተደስቻለሁ። ሰርግህ በጣም ግሩም ነበር። እነ ጋሽ ሙሉሰው ጥሩ አድርገው ነው የዳሩህ የነሱ ውለታ አለብህ ቀዳም በርግጥ አንተ ያደረጉልህን የምትረሳ አይደለህም። ግን ተንከባከባቸው በነዚህ ጥቂት ቀናቶች ምን አይነት ሰዎች እንደሆኑ አስተውለናል። እና አምላክ የልብህን አይቶ ወደር የማይገኝላቸው እናትና አባት ሰጥቶሀል"። "አንቺም እህቴ እንግዲህ ተዛምደናል። ቶሎ ወልዳችሁ ደግሞ ደስታችንን እጥፍ እናድርገው።"ብሎ ሐምራዊንም አቅፎ ሳማት። በናፍቆት ተለያዩ።
*
"ወንድሜ ሲልህ አንጀቴን አላወሰው። ውይ አነጋገሩ እንዴት አንጀቴን እንዳላወሰው"አለች ሐምራዊ እነ ሙሉቀንን ሸኝተው ሲመለሱ።ቀዳማዊ ፈገግ ብሎ "አዎ ከልቡ ነው እንደዛ የሚለኝ። ምድር ላይ ከእሱ በላይ የሚወደኝ ያለ እስካይመስለኝ ድረስ ነው የሚገርመኝ። በእኔ ጉዳይ በጣም ስስ ነው። እኔን ሲነኩኝ አይወድም። ከልጅነቴ ጀምሮ በጣም ነው የሚሳሳልኝ። ከሚገርምሽ እሱ ከትምህርት ይቀርና እኔ እንድማር የኔን ግልገሎች ይጠብቅልኝ ነበር። እናቴ ያው ከትምህርት ቤት የምታስቀረኝ ጊዜ ስለሚበዛ እሱ እኔ እጠብቅለታለሁ ብሎ ከትምህርት ቤት እስክመለስ በደንብ ይጠብቅልኛል። ምን አልባትም ምሳ ላይበላ ይችላል ብሎ ስለሚያስብ እሱ ቤቱ በልቶ ከእንደገና እናቱን በአገልግል ያስቋጥራትና እንበላለን። ብቻ የቱን አንስቼ የቱን ልተውልሽ የእናት ልጅ እንደዛ ማድረጉን እጠራጠራለሁ። ሁሌም የሚለኝ አንተ የተማርህ ምሁር ነው የምትሆን እኔ እጣፈንታዬ ገበሬነት እንደሆነ አውቀዋለሁ።ስለዚህ አንተ ተማር ጎበዝ መምህር ትሆናለህ ነው የሚለኝ። ያው በዛን ጊዜ በእኛ እይታ ትልቅ ስራ መምህርነት ነው የሚመስለን። ከእኛ የተሻለ ከተሜዎች ስለሆኑ እንደነሱ መኖር ነው የምንፈልገው። ትልቁ ራዕያችን እንደ ጋሼ እንትና ጎበዝ አስተማሪ መሆን ነው።ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ወታደር መሆን። እና ታዲያ የኔን ጎበዝ ተማሪ መሆንን ይኮራበታል። ወንድሜ እኮ አንደኛ አንደኛ ነው የሚወጣው የሚሸለመው ደፍተር እኮ ብዙ ነው። እያለ በእኔ ይኮራል። በኤረኞቹ ፊት ደረቱን ነፍቶ ይቆማል ይጀበንባቸዋል። ብቻ ምን አለፋሽ እኔ እዚህ ለመድረሴ ትልቁን ሚና የተጫወተው እሱ ነው። ለመጥፋት ባሰብኩ ጊዜ እንኳ ራሱ እናቱ ያስቀመጠችበት የብር ቅል ገብቶ ብር ሰርቆ ነው መሳፈሪያ የሰጠኝ። ከዛ በኋላ በዛች ብር ፈጣሪ እረድቶኝ አዲስአበባ ገብቼ ለዚህ በቃሁ ማለት ነው።እንግዲህ ከብዙ በጥቂቱ ይሄን ይመስላል ፍቅሬ"አለ ቀዳማዊ እንባ ያቀረሩ አይኖቹን በፈገግታ ለመሸፈን ፈገግ እያለ። "የኔ ጌታ እንኳን መጣህልኝ። ለእኔም ባለውለታዬ ነው። አንተን ከዛ ባያስወጣህ ኖሮ ይሄኔ ምን እሆን ነበር?"አለች ሐምራዊ

@amba88
@ken_leboch