Get Mystery Box with random crypto!

ምን ላድርግ ? አባ ፓምቦ አባ እንጦንስን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- “ምን ላድርግ ?” ሽማግሌውም | ከ

ምን ላድርግ ?

አባ ፓምቦ አባ እንጦንስን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- “ምን ላድርግ ?” ሽማግሌውም እንዲህ አለው ፡- “በራስህ ጽድቅ አትተማመን ፣ ስላለፈው ድርጊትህ አትቆጭ ፣ ምላስህንና ሆድህን ተቆጣጠር ።”

ብዙ ዘርተው ጥቂት ማጨድ ያቃታቸው ፣ ፍቅር ሰጥተው ስድብ የተመለሰላቸው ፣ ለማስደሰት ሞክረው ሰዎች የተከፉባቸው ፣ የቤታቸውን ጣራ በጠገኑ ቊጥር ያፈሰሰባቸው ፣ መልካም ለመሆን ሞክረው አስመሳይ የሚል ስም የተሰጣቸው ፣ ሲያጠፉም ሲያለሙም ምስጋና የተነፈጋቸው ፣… “ምን ላድርግ ?” በማለት ግራ የመጋባት ጥያቄ ያቀርባሉ ። አባ ፓምቦ ግን “ምን ላድርግ ?” ያለው ለእግዚአብሔር ለመኖር ፣ ለወደደው አምላክ የተመረጠውን ለማድረግ አስቦ ሲሆን ፣ ጥያቄ ግራ የመጋባት ሳይሆን ቀኙን የመምረጥ ነው።

ሁለት የደነዙ ቢላዎች እንኳ ሲሳሳሉ ምላጭ ይሆናሉ ። ሁለት የበረቱ አባቶችማ እርስ በርሳቸው ሲመካከሩ ይኸው ለትውልድ የምክር ብርሃን ይፈነጥቃሉ ። ድንጋይና ድንጋይ ፣ እንጨትና እንጨት እንኳ ሲፋጭ እሳት ይወጣቸዋል ። የተቀደሱ አባቶችማ ሲጠያየቁ ረቂቅ የሆነው መንፈሳዊ ኑሮና መንፈሳዊ ውጊያ ፍንትው ብሎ ይብራራል ። አባ ፓምቦ አባት ቢሆንም ከአባ እንጦንስ ለመመከር ዝቅ ያለ ነበር ። ለመሞላት ዝቅ ማለት ያስፈልጋል ። ከወራጁ ከፍ ያለ ማድጋ አይሞላም ። ዝቅ ያለና ባዶ ሁኖ የቀረበ ማሰሮ ግን ይሞላል ። በዚህ ጨለማ ባጠላበት ዓለም ላይ የቅዱሳን አባቶች ምክር የሚመራ ኮከብ ነው ። ኮከቡም የሚያደርሰው ክርስቶስ ጋ ነው ። ክርስቶስ ጋ የደረሰም ይሰግዳል ፤ ያለውን ሁሉ ይሰጣል ።

ከመደበኛ የትምህርት መርሐ ግብር ለየት ያለው ጥያቄና መልስ ያለው መማማር ነው ። ጥያቄና መልስ መምህርና አስተማሪውን የሚያሳትፍ ትልቅ የትምህርት መርሐ ግብር ነው ። መምህሩ በውስጡ የተደበቀውን እውቀት የሚያወጣው በጥያቄ ነው ። የመምህሩ መደበኛ ትምህርት ለተማሪዎቼ “ይህ ያስፈልጋቸዋል” ብሎ ያቀረበው ማዕድ ሲሆን ጥያቄ ግን ተማሪው “ይህ ያስፈልገኛል” ብሎ ያማረው ምግብ ነው ። ጥያቄ የተማሪ የነጻነት ሜዳ ነው ። የማይረሱ ትምህርቶች በጥያቄና መልስ የሚሰጡ ናቸው ። አስተማሪው ተማሪውን የሚያውቅበት ፣ የራሱን እውቀትና ምን ያህል ማስተማሩን የሚለካበት ሚዛን ጥያቄ ነው ። ጥያቄ አስተማሪ ይበልጥ እንዲያነብ ያደርገዋል ። የሚጠይቅ ተማሪ ሲጠይቅ አላውቅም እያለ ነውና ጥያቄ ትሑት ያደርጋል ። በርግጥ ለፈተና የሚጠይቁ ያልታደሉ ወገኖች አሉ ። ጥያቄ ተማሪና አስተማሪን ያቀራርባል ። የምናመልከው አምላክ ጥያቄን የሚፈራ አምላክ አይደለም ።

አባ ፓምቦ፡- “ምን ላድርግ ?” ብሎ ጠየቀ ። ይህ ጥያቄ የእውቀት ጥያቄ ሳይሆን የመለወጥና ክርስትናን ተጨባጭ የማድረግ ጥማት ነው ። ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ሲያስተምር በትምህርቱ የተነካው ሕዝብ፡- “ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት፡- ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው።” የሐዋ. 2፡37 ። ምን ላድርግ ? ማለት ልብ ሲነካ የሚቀርብ ጥያቄ ነው ። አንድ ሰው የክርስቶስ ፍቅር በልቡ ውስጥ ሲጠልቅ ምን ላድርግ ? ይላል ።

አባ እንጦንስ ካስተላለፈው ምክር አንዱ፡- “በራስህ ጽድቅ አትተማመን” የሚል ነው ። “ምን ላድርግ ?” ለሚል ጥያቄ ስላለፈው አድራጎትህ አትተማመን የሚል መልስ መስጠቱ የሚገርም ነው ። ለቀጣይ አድራጎት ለተጠየቀ ጥያቄ መልስ ተደርጎ የተሰጠው ያለፈው በጎነትህ ላይ አትተማመን የሚል ነው ። የቅዱሳን አባቶች ሁሉ የሠመረ ጎዳና በራሳቸው በጎነት ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ መደገፋቸው ነው ። ነቢዩ ዳዊት፡- “ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም” ብሏል ። መዝ. 15 ፡ 2 ። በራስ ጽድቅ መተማመን ባለፈው ያንን አልፌዋለሁ ብሎ አሁን ግን አልወድቅም በሚል ስሜት መዘናጋትም ነው ። በራስ ጽድቅ መተማመን ማለት ሌሎች ላይ መፍረድና እኔ እሻላለሁ ብሎ ማሰብ ነው ።

አባ እንጦንስ ሁለተኛው ምክሩ፡- “ስላለፈው ድርጊትህ አትቆጭ” የሚል ነው። ባለፈው ድርጊትና በተናዘዙበት ስህተት መቆጨት ራስን እየመረዙ መኖር ነው ። “እንዴት እኔ ይህን አደርጋለሁ ?” ማለትም መመጻደቅ ነው ። ሌሎች የሚሠሩትን ስህተት ካልሠራን እግዚአብሔር ስለረዳን እንጂ የማይሠራ ሥጋ ስለተሸከምን አይደለም ። “ባለፈ ክረምት ቤት አይሠራም” እንደሚባል ባለፈው ዘመን መቆጨት ያለውን ዘመን ማቃጠል ነው ። እግዚአብሔር ይቅርታ እንዳደረገልን ካመንን ከኅሊናችን ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልገንም ። “የአንድ ግብ መድረሻ ለሌላ መነሻ ነው” ይባላል ። ንስሐም የኃጢአት መጨረሻ የጽድቅ መነሻ ነው ። ስለ ክፉ አድራጎት መጸጸት በራሱ በጎነት ነው ። እየተጸጸቱ መኖር ግን በእግዚአብሔር አለማመን ነው ። የሚመለስ ሰው እንጂ የማይበድል ሰው አይደለንም ።

“ምላስህንና ሆድህን ተቆጣጠር” ሦስተኛው ታላቅ ምክር ነው ። ምላስ ባለቤቱን አስሮ የማስቀመጥ አቅም አለው ። ሕይወትና ሞትም በአንደበት ላይ ነው ። የምንጓዘው ወደ ተናገርነው ነው ። ስለዚህ ምላስን መቆጣጠር ይገባል ። ሆድን መቆጣጠርም ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ጤንነት ወሳኝ ነው ። ተገኘ ተብሎ መብላት ፣ እንደ ዔሳው ለምግብ ጎምዥቶ ብኵርናን መሸጥ አይገባም ። ፍላጎት ገደብ ከሌለው በምድር በሰማይ ከርታታና የማይረካ ሰው ያደርገናል ። መቆጣጠር በጥንቃቄ መኖርን የሚያመለክት ነው ። ጠቢቡ፡- “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል ፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል” ይላል ። ምሳሌ 2፡11 ።

ጌታ ሆይ ፣ በአንደበቴ ሳይሆን በልቤ የታዘብኩት እንኳ ፈተና ሁኖ ይመጣብኛል ። አለሁ ስል ይበልጥ አልኖርም ። ስምል ፣ ስገዘት የበለጠ እወድቃለሁ ። አምላኬ ትላንት የዛሬውን ሕይወቴን እንዲያውክ ፈቅጄለታለሁ ። በአንደበቴ ላይም ገና ባለሥልጣን አልሆንሁም ። እባክህን ጌጠኛውን የጽድቅ መጎናጸፊያ አልብሰኝ ።

በዘላለማዊ ክብርህ አሜን ።

ለተጨማሪ ትምህርቶች Add ማድረግ ይቻላል

https://t.me/KeAbawandebet