Get Mystery Box with random crypto!

እውነት ነው የምላችሁ አንብብ እና የሰላም እንቅልፍ ተኙው አስታዋሽ አምላኬ ሆይ የሥነልቦ | ከ

እውነት ነው የምላችሁ አንብብ እና የሰላም እንቅልፍ ተኙው

አስታዋሽ አምላኬ ሆይ

የሥነልቦና ባለሞያ Bini Girmachew  እንደፃፈው

      በተደነቀ ዝምታ  የምትኖር አስታዋሽ ፈጣሪ ሆይ አመሰግንሃለሁ፡፡ አንተ በዝምታህ ውስጥ መልስ አለህና አከብርሃለሁ፡፡

እንደማይሰማ ዝም ብትልም፣ እንደማይሰጥ ብትዘገይም፣ እንደማይገደው ብታልፍም ዓላማ አለህና ተመስገን፡፡ የቀኑን ምልክት በማየት አለባበሴን ባስተካክልም፣ የዘመኑ ምልክት ግን ሳይገባኝ በአንደበቴ ጠፍቻለሁና አድነኝ፡፡ ዓለም ስትንጫጫ ዝም ማለትን አስተምረኝ፡፡
    
     እውነት ስናገር ሰዎች ይከፋቸዋል፣ ሐሰት ስናገር ፍቅርህ ያዝንብኛል፡፡ እባክህ የአንተ ወገንተኛ አድርገኝ፡፡ ያንተ ወገን በሁለት ወገን እንደተሳለው ቃልህ ለማንም አይመችም፡፡

መተማመን በጠፋበትና ቋንቋ  በተደባለቀበት ዘመን የልቤና የአንደበቴ ጠባቂ ሁን፡፡ በሰነፎች ዘመን ጠቢብ አድርገኝ፡፡

ውዴ ሆይ፡ የሚያልፍ ዘመን የማያልፍ ንግግር እንዳያናግረኝ እባክህ ተቆጣጠረኝ፡፡

     ሰዎች እንደ እኔ ካላሰቡ ከሚሉ ግትሮች ጠብቀኝ፣ እኔም ሰዎች እንደ እኔ ካላሰቡ በሚል የሕይወት ጠንቅ ውስጥ እንዳልገባ ያዘኝ፡፡

ሥጋዬን አላምነውምና መንፈስህ ይምራኝ፡፡ የገዛ ፍቅሬ እንጂ ሌሎችን መጥላት ከማንም ጋር እንዳያፋቅረኝ ተጠንቀቅልኝ፡፡ ያምራል ብዬ ከተናገርኩት ይከፋል ብዬ የተውኩት እንደሚሻል አሳየኝ፡፡

ዘላለም የሚጸናው የአሁኑ ሳይሆን ያንተ ሥርዓት መሆኑን ግለጥልኝ፡፡ ለስሜቴ የሚስማማኝን እየመረጥኩ ቃልህን እንዳልታዘዝ እማጸንሃለሁ፡፡

     ተስፋህ ተስፋ ያደረኳቸውን ነገሮች ሁሉ ይውረሰው፡፡ ሰዎች እንዲያምኑኝና ፍትሐዊ ነው እንዲሉኝ የማደርገውን ጥረት ከእኔ አርቀው፡፡

አንተ ትበቃኛለህና ልቤን በጥላህ አኑረው፡፡ በማስፈልግበት ሰዓት እንዳልተኛ እርዳኝ፡፡ ሰው ሁሉ የመፍራት ሥልጣኑን ተጠቅሞ ሲፈራ እኔን በዓለት ላይ አቁመኝ፡፡

ሰዎች ሲያዘምሙ ሳይ ነቢይ እንዳልሆን ጠብ ቀኝ፡፡ ካንተም ይልቅ ቸር እንዳልሆንኩ አስረ ዳኝ፡፡ እገሌ በደለ እንጂ እኔ በደልኩ የማይልን አገርና ትውልድ ፈውስ፡፡ የመካሰስ ወራትን በይቅር  ነፋስ ለውጥ፡፡

     በአገራችን ሁሉም ሊቅ ነውና የሚማር መንፈስን ስጠኝ፡፡ የሰዎች ርእስ ያልሆኑትን የተረሱትን አንተ አስታውስ፡፡

ኃያላን ሲጣሉ እኛ እንዳንደቅ አውጣን፡፡ በደግ ቀን ያልጸለዩት በክፉ ቀን አይረዳምና በጸሎት አትጋኝ፡፡

አስቤ እንድናገር ሊቃውንት ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን አንተ በእኔ ቦታ ብትሆን ለሰውዬው የምትናገረውን እንድናገር እርዳኝ፡፡

የጥያቄዎች ሁሉ መልስ «አምላኬ በእኔ ቦታ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር?» የሚለው መሆኑን አብራልኝ፡፡

ጣዕም ባለው ስምህ ለዘላለሙ አሜን።

የማይሾሙህ ንጉሤ

     ከከበሩት በላይ ከብረህ የምትኖር የማይ ሾሙህ ንጉሤ፣ የማያበድሩህ ብልጥግናዬ ሆይ አመሰግንሃለሁ፡፡ ዓመታት ዘመናት ብዙ ወዳጆቼን ሲለውጡ እኔም በብዙዎች ስለወጥ አንተ ግን ያው አንተ ነህና አመሰግንሃለሁ፡፡

ልብስ የሸፈነውን ጓዳዬን፣ ጥርስ የሸፈነውን ልቤን ላንተ እገልጣለሁ፡፡ ልትረዳኝ አቅምና ፈቃድ ላለህ ላንተ መሸነፌን አወራለሁ፡፡ አንተ እንደ ሰው አልፎ ሂያጅ አይደለህምና እመካብሃለሁ፡፡

     ሰው ሁሉ ራሱንና አካባቢውን በሚያ ዳምጥበት ዘመን ቃሌ አይሰማምና እባክህ አንተ ስማኝ፡፡

ፍቅርና መልካምነት የራቀኝ የትዝታ ሰው ሆኛለሁና ዘመኔን እንደ ቀድሞው አድስ፡፡ ሰው በተሰለቻቸበት ዘመን የማይጠገብ ፍቅር ስጠኝ፡፡ ክፉን በክፉ ሳልመልስ በመልካም ማሸነፍን አድለኝ፡፡

     በፀፀት የትላንትናውን፣ በንዴት የዛሬን ከመመልከት በእምነት የወደፊቱን እንዳይ እባክህ እርዳኝ፡፡ በማየው ተወስኛለሁና የተስፋ አገሬን አጉላልኝ፡፡

ሰው በሰው ሆኖ ሲጠቃቀም እኔ ግን ካንተ በቀር የምጠራው የለምና ድረስልኝ፡፡ ሰዎችን በፍጹም ልቤ እንድወዳቸው እርዳኝ፡፡ ሰዎችም እኔን በመውደድ እንዳይፈተኑ አግዛቸው፡፡ ቃላት ቆርጣሚ አማርኛ ሰንጣቂ ከመሆን እውነት ቀማሽ አድርገኝ፡፡ ሰዎች ቋንቋን ያዳምጣሉ፣ አንተ ግን አሳቤን ተረዳልኝ፡፡

ሁሉም ወደ ራሱ አሳብ ሲያዘነብል እኔን ግን በአሳብህ ማርከኝ፡፡ ባልንጀርነትና ትዳር ባቢሎን ሲሆን ለእኔ ግን ቋንቋዬ ሁንልኝ፡፡ የሰው አንደበት ያቆስላል፣ የሚያዩት የሚሰሙት አያስደስትምና ለእኔስ ወደ አንተ መቅረብ ይሻለኛል፡፡

     ንጹሕ ምንጭ እንደሚደፈርስ የብዙ በጎ ሰዎች አእምሮ ደፍርሷልና እባክህ አድነኝ፡፡

ከልብ የሚያመልኩህ ሳይበላሹብህ ውሰዳቸው፡፡ የሃይማኖት ቃላችንን ማንም ሊሰማው ጠልቷልና ደግ ዘመን አምጣልን፡፡ ራሴን በቃልህ እንጂ በደከመው ወንድሜ እንዳልመዝን እርዳኝ፡፡ በሚያስጠጋው ስምህ ለዘላለሙ አሜን።
በምስጋና ተውበህ

     በክብር ደምቀህ፣ በምስጋና ተውበህ፣ በአእላፋት ተከበህ፣ በኪሩቤል ጀርባ ነግሠህ የምትኖር የማትወሰን፣ ለሁሉ ወሰን የሰጠኸው አምላኬ  ሆይ አመሰግንሃለሁ፡፡

ለዚህ ሁሉ ፍጥረተ ዓለም ምክንያቱ አንተ ነህ፣ አንተ ግን ምክንያት ሳትሻ ትኖራለህና አከብርሃለሁ፡፡

     እንደ ወደድኸኝ ልወድህ አልችልም፣ እንዴት እንደወደድከኝ እንኳ የፍቅርህን ልክ ማወቅ ተስኖኛልና እባክህ አግዘኝ፡፡

ባምነው መንግሥተ ሰማያት እገባለሁ፣ ብክደው ገሀነመ እሳት እወርዳለሁ ብዬ ሳይሆን ወዶኛል ሞቶልኛል ብዬ እንድከተልህ እርዳኝ፡፡

አቅሜን አላውቅምና በፍቅር አቅሜን አሳውቀኝ፡፡ በመሰበር መማር አይረሳም፣ እኔን ግን በመውደድህ አስተምረኝ፡፡

ሰው ሁሉ  ለመከራው አያቅድም፡፡ መከራ ግን በሰው ላይ ያቅዳልና ይሆናል ብዬ መጠበቅንም አስተምረኝ፡፡

የምወዳቸው ያለ ችግር እንዲሆኑ የማደርገውን ጥረት ከእኔ አርቀው፣ አይሳካምና፡፡ ለማንም ካንተ በላይ ደግ እንዳልሆንኩ አሳውቀኝ፡፡ የማልፍበትን የኑሮ ገጽ  ሁሉ «ይህም ሕይወት ነው» እንድል አሰልጥነኝ፡፡

ፀጥታ ረብሻ ሲሆን አጽናኝ፡፡ ማንም እንዳይደርስብኝ የከለልኩት የፀጥታ ሰዓቴን ለተጨነቁት ማዋልን አድለኝ፡፡

ራስን በማዳመጥ ሳይሆን ሌሎችን በመርዳት ያለውን ደስታ ግለጥልኝ፡፡

የማላደርገውን እንዳልናገር፣ የተናገርኩትን እንድፈጽም፣ ከሁሉ በላይ ተስፋ ሰጪ ሰው እንድሆን እለምንሃለሁ፡፡ ሰውን የሚያህል ፍጡር በማይፈጸም «እሽ» እንደ ዶሮ እንዳላባርር ማስተዋል ስጠኝ፡፡

«አይሆንም» በጊዜው ጥሩ መልስ መሆኑንም ግለጥልኝ፡፡

ጌታዬ ሆይ ምንም ባስቸግርህ ለፍላጎቴ አሳልፈህ አትስጠኝ፡፡ ከሚያፀፅት ሕሊና አድነኝ፡፡

ሥጋዬ የበላይ ሆኖብኛልና አንተ ግዛኝ፡፡ ላንተ ከመገዛት ውጪ ሌላ አሳብ የለኝም፡፡ ለመታዘዝ ግን ፍላጎት እንጂ አቅም የለኝምና ጸጋህንና የጸጋ ስጦታህን ላክልኝ፡፡

አውቄህ እንዳላወቀህ ከመሆን አድነኝ፡፡ ለዚህ የእንግድነት ኑሮ እንዳልረሳህ ከራሴ ጠብቀኝ፡፡ ምናልባት ነገ ብትመጣ ከነኃጢአቴ እንዳታገኘኝ ነጩን ሸማህን አልብሰኝ፡፡

ወደ ፍጡራን ብጠጋም ጽድቃቸው ለራሳቸውም አልበቃቸውም፣ አንተው በሚተርፈው ጽድቅህ አጽድቀኝ፡፡

በማይታበለው እውነትህ ለዘላለሙ አሜን፡፡


Bini Girmachew ( ሰው ሁን ከሰውም ሰው ሁን) 

YouTube ሰብስክራይብ ለማድረግ ይሄን ሊንክ

ይጠቀሙ!!

  
https://www.youtube.com/channel/UCawJZOERphyparnxlMZwa6w

@Bini_Girmachewbot @BiniGirmachew


የነገ ሰው ይበለን