Get Mystery Box with random crypto!

በቃ እንዲሕ ያለውን የነጠረ ቃል ሳስታውስ ነው ፍልሰታ ማለት ለእኔ ምን ማለት እንደሆነች የምረዳው | ከ

በቃ እንዲሕ ያለውን የነጠረ ቃል ሳስታውስ ነው ፍልሰታ ማለት ለእኔ ምን ማለት እንደሆነች የምረዳው….. ከዛፎቹ …..ከመጠለያው …..ከአስቀዳሹ…… ከፅናው….. ከዲያቆኑ….. ከካሕኑ ከልብሰ ተክሕኖው ….. ከሚሯሯጡት ሕፃናት ….. ከሁላ ሁሉ በላይ የድንግል ማርያም ምስጋና የፍልሰታ ጾም ውበት ነው፡፡


የቁርባን ስዓት (ድርገት) ሲደርስ ከሰንበት ትምሕርተ ቤት አዳራሽ በሰልፍ ስንወጣ…. በተወሰነ ርቀት ሰልፋችንን ጠብቀን እንድንጓዝ የሚደርጉን የመዘምራን ዩኒፎርም የለበሱት ትዝ ይሉኛል። ቆርበን ስወጣ በወንዶች እና በሴቶች በር የተቆራረሰ ዳቦ ለምለም እንጀራ ይዘው ለሁሉም ቆራቢ የሚሰጡት እናቶች ዛሬ ድረስ ትዝታዬ ናቸው ። አንዳንድ ጊዜ በልጅነት ዘመን ሳንቆርብ እንደቆረብን መስለን አፋችንን በነጠላ ሸፍነን ዳቦ እንቀበል ነበር። በሴቶች በር ተቀብለን ከሆነ በወንዶች በር ለመቀበል የምንሰጠው ምክንያት ገራሚ ነበረ

"ጫማዬ በዛኛው በር ነው"

"እናቴ በዛ እየጠበቀችኝ ነው"

ከቆረብን በኋላ ካሕኑ የሚያነቡት ንባብ

ይህንን የማርያምን የምስጋና ቃል እንደሰማችሁ የሕፃናትን ይልቁንም አጥንትን የሚያለመልመውን የመላእክት ምስጋና እንደዚሁ ያሰማችሁ። የእሳት ድንኳኖች ወደ ተተከሉበት የካሕናት አለቆች ወደ አሉበት ያግባችሁ ። አንድ ኦርቶዶክሳዊ ይሄንን መርሳት መቼም አይሆንለትም። መቼም ቢሆን አይረሳም ። በልጅነት ልቦናችን ላይ የታተመ የተቀረፀ የትላንትናችን የትዝታ ማህደር ነው።

አድንኑ አርዕስቲክሙ ሲባል የልጅነት ልቦናችን እና እግራችን ወደ ቤት ለመሮጥ ይዘጋጃል። ሥርዓተ ቅዳሴው ማለቁን እንረዳለን። ዳዊት ድፍዳ ፀበል ይዞ ከቤተ መቅደስ ከወጣ ።

በቃ ቅዳሴው አልቋል ማለት ነው ጃንጥላዎች ከታጠፉ ምንጣፎች ከተሰበሰቡ ነጠላዎች በሰስ ፌስታል ውስጥ ከተከተቱ. በቃ ቅዳሴው አልቋል ማለት ነው። ዛሬም ቢሆን ከዓመታት በኋላ ዳዊት ድፍዳ ለአንዳንድ ምዕመናን ጸበል መስጠቱን አላቆመም ። አድንኑ ሲባል ሁሉም ነጠላውን ያጥፋል።

"በስላም ግቡ ወደ ቤታችሁ ግቡ" ከተባለ በኋላ ድምፅ ማጉያውን ተቀብለው የሚዘምሩትመ ዘማሪዎች ትላንትም ነበሩ….. ዛሬም አሉ ።

ትላንትና ከቅዳሴው መጠናቀቅ በኋላ በአባ ክፍለዮሐንስ (የከተማው እንጦንስ) ቤት ገብተን እግር ስመን የፍልሰታን በረከት እንቀበል ነበር። ባቄላና ንፍሮ አንዳንዴም አነባበሮ እንቀበላለን ። ንቦቹ እንዳይነድፉን ፊታችንነ በነጠላ እንሸፍናለን። ጋሽ አድማሱም ጋር እንሄድ ነበረ። ትዝታችን እዚህ ጋር ነው የተሰበረው። አባ ክፍሌ እና ጋሽ አድማሱ በአካለ ሥጋ ከእኛ ጋር የሉም።

በፍልሰታ ፆም የማይገኙት የየት ሰፈር ልጆች ናቸው?

የሁሉም ሰፈር ልጆች ይገኛሉ፡፡

ስለምንቆርብ ነው ገላችንን በደንብ የምንታጠበው ። ስለቆረብን ነው ኳስ እንዳንጫወት የተከለከልነው። ስለቆረብን ነው ከቤት እንዳንወጣ የተደረግነው ። ወላጆቻችን ከወትሮ በተለየ እቤት ውስጥ የተንከባከቡን ስለቆረብን ነው ።

በክረምት የሚሰጠው የሰንበት ትምህርት ቤቱ ኮርስ ነው ። ከፍልስታ ፆም መግባት ጋር ልዩ ድባብ ነበራቸው። ዛሬም አላቸው…. የምድብ አስልጣኞች የሚያፅፉን ፅሑፍ ሁሉም በፍልሰታ ወቅት ልጅነቴ ብዬ በምጠራው ሀዲድ ላይ የተሳፈሩ የሃይማኖት ቤት ትዝታ ናቸው፡፡

ማታ ሲመሽ

ሰዓታት ዘሌሊት ከመቆሙ በፊት ወደ መቅደስ ግቡ የሚለው ደወል እስኪደወል ድረስ የአዳራሹ ወንበር ገጥመን እንተኛ ነበር። ዲያቆናት ውዳሴ ማርያም ዜማ ያደርሳሉ ። ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ደወል ሲደወል የቤተመቅደሱ መብራት ሲበራ ሁሉም ከተኛበት ተነስቶ ተናጽቶ ወደ ቤተመቅደስ ይገባል። ፀሎቱን ሳያደርስ ማንም ከማንም ጋር አያወራም….. የሰዓታቱ ቦታ አራት ማዕዘን ቅርፅ አለው…… የአበባ ምንጣፍ ይነጠፍበታል…… አሳዳሪው ካሕን ካባቸውን ለብሰው በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሕዱ አምላክ አሜን ብለው ይጀምራሉ፡፡ በግራና በቀኝ ካሕናት ፣ መነኮሳት ፣ መሪጌታዎች ፣ ቀሳውስቶች ፣ ቀኝ ጌታዎች ፣ ግራ ጌታዎች ፣ ዲያቆናት ፣ መፀሐፈ ሰዓታት ይዘው የሚከታተሉት ብቻ ብዙውን ነገር ያየሁት በልጅነት አዕምሮዬ በዛች ውብ ቤተ መቅደስ ነው፡፡

አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሰዳዴሆሙ ለአጋንንት እምየማንነ ወእምፀጋምነ እምዛቲ መካን ይርሃቁ እምኔነ ለእለ ይፀብዕዎ ለነፍስነ ይባላል…… አባ ልብሰወርቅ ሰዓታት ቋሚውን ቆንጆ ሽቶ ሲቀቡ።

ኃይል ባለው ድምፅ እንባ በሞላው ፀሎት ሁሉም ሰዓታት አድራሾች የእመቤታችን ስዕለ አድህኖ እየተመለከቱ ንዒ ኀቤየ ኦ ድንግል ምስለ ኢሳያስ ሲሉ…….. ተረኛው ሲቀበል….. ዲያቆኑ ምስባክ ሲሰብክ….. ካሕኑ ወንጌል ሲያነቡ ያ ሁሉ የልጅነት ልቦናዬ ላይ የታተሙ ፊደሎች ናቸው ….. ዲያቆናቱ ኩሎሙን ሲቀሽሩት…… አባ ኃይለስላሴ ነዓ ነዓ ነዓ ጊዮርጊስ እንዘ ትፄአን በፈረስ ሲባል እንዴት ነበር መቋሚያውን የሚዘምሙት….. ትባርኮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር ነዓ ጊዮርጊስ ሰማዕተ ኢየሱስ ክርስቶስ ወነዓ ፍቁር ዘልዳ ንጉስ ዘሐረፀከ ዱዲያኖስ ወወገረከ ደብረ ይድራስ። አባ ኃይለስላሴ በአካለ ሥጋ ከእኛ ጋር አይደሉም ። በረከታቸው ይደርብን።

ደሞ ሊነጋጋ ሲል…… አባ ልብሰወርቅ ተዓምሪሃ ለእግዕዝትነ ማርያም ሲሉ….. ተዓምረ ቂርቆስ ……ተዓምረ ኢየሱስ ተከታትለው ሲነበቡ….. ዕሴብሕ ፀጋኪ ሲባል…….እንዴት ደስ ይላል….. የደብሩ የመጽሐፍ መምሕር የኔታ ብርሃኑ ውዳሴ ማርያም አንድምታውን ሲተረጉሙት፡፡

"አዕምሮውን ልቦናውን ሳይብን አሳድሪብን " ሲሉ፡፡

እንዴት መሰላችሁ የሚናፍቀው። የፍልሰታ ፆም ብዙ ነገር ነው።

ነሐሴ 16 ታቦተ ሕጉ ሕዝቡን እየባረከ ዑደት ሲያደርግ። የሰንበት ትምሕርት ቤት ተማሪዎች "ሞትሽ በጥር ነሐሴ መቃብር ሲሉ" እነዚህና መሰል ትዝታዎች ዛሬን ብቻ ነገም አብሮን ይኖራል።

የፍልሰታን ፆም እንኳን ደኽና መጣሽ እንበላት፡፡

ፆሙን የበረከት ፆም ያድርግልን!