Get Mystery Box with random crypto!

ፍልሰታ × | መቼም ቢሆን የልጅነት ዘመኔን ከሚያስታውሱኝ የቤተክርስቲያን ወቅቶች መካከል የፍል | ከ

ፍልሰታ
×

|

መቼም ቢሆን የልጅነት ዘመኔን ከሚያስታውሱኝ የቤተክርስቲያን ወቅቶች መካከል የፍልሰታ የፆም ወቅት አንዱ ነው። በዚሕ የፆም ወቅት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳደደ ነጠላ አጣፍቼ ወደ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ለማስቀደስ የሄድኩት።

ሕንፃ ቤተክርስቲያኑን ከራሴ ቁመት ጋር አነፃጽሬ የተገረምኩት። ትልቀቱ ግዝፈቱ የገረመኝ። የቤተክርስቲያኑ ግንብ ላይ ያሉት ጠጠሮች ። የቆሙት አስራ ሁለቱ የቤተክርስቲያን ምሰሶዎች….. ብቻ ሁሉንም ማወቅ የቻልኩት በዛን የልጅነቴ ጊዜዬ ነው ፡፡

ነጠላዬን አላስተካከልኩም

"ወዴት ነው የምትሄደው? "

" ስንት ሰዓት ነው የምትመጣው? " አልተባልኩም። ብቻ ነጠላዬን አጣፍቼ ወደ ቤተክርስቲያን ራሴን ችዬ ከሰፈሬ ልጆች ጋር የሄድኩት በፍልሰታ የፆም ወቅት ነው፡፡

ቤተክርስቲያኑ እንደኔ ያሉትን ብዙ ሕፃናት የማስተናገድ አቅም ነበረው። ብዙ ነን። በጣም ብዙ።

አንዱ ዣንጥላ ይዞ ይሯሯጣል ….

አንዳንዱ ሹሌ ይጫወታል…..

ሌላው ምንጣፍ ይጎትታል….. በዘረጋነው ምንጣፍ ላይ ተርታውን ዓውደ ምሕረቱ ላይ እንተኛ ነበር፡፡ (ካደኩ በኋላ ነው እንዲያ የምንተኛው የአተኛኘት ዓይነት አስመራ ድርድር መባሉን ያወኩት)። የደብሩ ዲያቆናት ከመቅደሱ ወደ ቤተልሔም ለአገልግሎት ሲፋጠኑ ….ውር ውር ሲሉ የልጅነት አዕምሮዬ ላይ ተከትቦ ቀርቷል። መቅደስ ውስጥ የጉልላቱን ርቀት እያየሁ ይደንቀኝ ነበር። መንግስተ ሰማያት ማለት ያ ይመስለኝ ነበር ። ያኔ ነው የመቅደሱ ፍቅር የጣለኝ፡፡

ካሕናቱ ፍሕሙን በጧፍ ሲያቀጣጥሉ ። የዕጣኑ መዓዛ በንፋስ እተገፋ ያለንበት ድረስ መጥቶ ሲያውደን። የቤተክርስቲያኑ ጠባቂ ንቦች አንዳንድ ጊዜ ለመደበቅ የማይመች ቦታ ሲነድፉን በእብጠቱ ጓደኞቻችን እየሳቁ ያስኮርፉን ነበረ ። ከንፈራችን አፍንጫችን ቅንድባችን የተነደፈ ዕለት የሚኖረው እብጠት እኛኑ ራሱ ያስገርመን ነበረ። ደሞ በ
ሌላ ጊዜ እንዳይነድፉን በነጠላችን ስንሸፋፈን ትዝ ይለኛል፡፡

በቃ ደስ የሚል ትዝታ አለ አይደለ ….ፍልሰታ ለእኔ እንደዛ

የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች ሁላችንንም ሰብስበው አዳራሽ ውስጥ ቁርባን እስኪጀመር ድረስ አስገብተው የሚነግሩን መፅሃፍ ቅዱሳዊ ታሪኮች። መሳጭ የሆኑት የእነ አብርሃም ታሪክ አጣፍጠው የሚነግሩን የተረት አባቶች ። ያኔ አዳራሹ መቀመጫ ወንበር አልነበረውምና ምንጣፍ ተነጥፎልን ነበር የምንቀመጠው። ብዙዎቻችን ለመቀመጥ እንጋፋለን ።

ሥርዓተ ቅዳሴ ሲጀመር ይሰማናል።

"አሐዱ አብ ቅዱስ ..." ሲባል ሁላችንም እንድንነሳ ይደረጋል። አቤት የነበረ ፍቅር። ቶሎ ለመነሳት ያለን እሽቅድድም። ለመነሳት አንዱን ስንደገፍ…. ሌላኛው እኛን ሲደገፈን…. የነበረው መልካምነት ደስ ይል ነበር። የሰንበት ትምህርት ቤቱ መድረክ ለልጅነታችን አዕምሮ ይገዝፍብን ነበር። እየተቀባበሉ የሚያቀርቡልን መነባንብ ….. የምድብ ማቴዎስ የሕጻናት ክፍል ተማሪዎች እየተቀባበሉ የሚዘምሩልን መዝሙር…. አዝማቹ ሲጠፋቸው ለማረም ስንሞክር የምነፈጥረው ረብሻና ጩኽት። አቤት እንዴት ደስ ይል ነበር። አዳራሽ በተራ ነበር የምንገባው…… ዛሬ ወንዶች ከገቡ ነገ ደግሞ ሴቶች ይገባሉ፡፡ በዛ ድራማና መነባንብ ተስበን ብዙዎቻችንን ሰንበት ትምህርት ቤት አባል ሆነን ቀርተናል።

ጥሬ የሚለቅሙት ነጫጭ እርግቦች አውደ ምህረቱ ላይ የተበተነላቸውን የድፎ ዳቦ ፍርፋሪ….. የእንጀራ ቁራሽ…. የጥሬ ብትን ሲመገቡ ቆመን እናያቸው ነበር።

ስንት ነበሩ ርግቦቹ?

አንድ ጨቅላ ሕጻን ልጅ እየሮጠ ወደ ተሰበሰቡት እርግቦች መሰስ ብሎ ሲሄድ እየተበታተኑ ወደ የአቅጣጫው ሲሄዱ። በየዛፎቹ ላይ ሲንጠላጠሉ። እናቶች ሕፃኑን ልጅ ይዘውት ሲሄዱ። የተበታተኑት እርግቦች መልሰው ሲሰበሰቡ። ከሕ
ንፃ ቤተክርስቲያኑ መስኮት ላይ ….. ከደውሉ ላይ…… ከዛፎች ላይ ….ድጋሚ ተሰብስበው ጥሬ ሲለቅሙ ያለው ድባብ መቼም የማይረሳ ትዝታ ነው፡፡

ሕፃንነት ነውና ጊቢው ዙርያ እንሮጣለን…. አንዱን ጓደኛችንን እናባራለን፡፡

በሌላ ቀን ደሞ

ካህናቶች ወደ ቤተልሔም ወርደው መሶበ ወርቅ ዲያቆኑ ተሸክሞ ሲመለስ የዲያቆኑን ቃጭል ተከትሎ የሚደወለው ትልቁ ደወል ። ሕዝበ ክርስቲያኑ መሬት ወድቆ ሲሳለም።

"እምነ በሃ ቅድስት ቤተክርስቲያን አረፋቲሃ "ሲሉ። ሁለቱ ድምፅ ማጉዎች ሲያስገመግሙ ሲያስተጋቡ ።

"ሃሌ ሉያ እመቦ ብዕሲ ምዕመናን ዘቦአ ቤተክርስቲያን " ሲባል እንረጋጋለን። ወላጆች ልጆቻቸው እንዳይቀሰፉ በማለት በእጆቻቸው ይጣራሉ፡፡

በፍልሰታ ፆም የማላየው የዣንጥላ አይነት የለም። ጥቁር ቢጫ አረንጓዴ ቀይ...

የማልመለከተው የሰው ዓይነት የለም አጭር ወፍራም ሽማግል ወጣት ቀጫጫውን ...ወዘተ

ያላየሁት መቀመጫ ዱካ በርጩማ ያላየሁት ምንጣፍ የለም። ከቤተክርሰቲያኑ ዋናው በር በስተግራ የመባዕ መሸጫውን….. ክርስትና ቤቱን ….. የሰንበት ትምህርት ቤቱ አዳራሽን ይዞ….. የደብሩ አስተዳደር ያለበትን…. የአባታችን የአባ ክፍለ ዮሐንስ ዘወልደማርም መኖሪያ ቤት በሙሉ መጠለያ ስምንትን ጨምሮ እስከ ቤተልሔሙ ድረስ[ከቤተልሄም በመለስ] ሴቶች ይቆማሉ።

ጥንታዊያን የተሰኙ ዲያቆናት መሪጌታዎች መነኮሳት ቀሳውስት የቤተልሔሙን አጸድ ይመርጣሉ። ወጣቶችም አይጠፉም ። መጠለያዎቹ ግጥም ብለው ይሞላሉ ። ደወሉም ላይ የሚወጣ አይጠፋም። በቤት መኪና …. በላዳ ታክሲ ጭምር መጥተው የሚያስቀድሱም አሉ። ብቻ ሁሉም እግሩ በመራውና ይመቸኛል ባለው ቦታ ለማስቀደስ ይቆማል ።

"ሥመር እግዚኦ ከመ ታድኅነነ " ሲባል ሁሉም ቀጥ ብሎ ይቆማል ። የቤተክርስቲያኑ በሮች በጥበቃዎቹ ይዘጋል። እጆች ይዘረጋሉ።

"አሐዱ" ሲባል ጥበቃው እየተራመደ ከሆነ ይቆማል። አንዳንዱ ያለቅሳል ሌላው በፍርሃትና በተመስጦ በጌታ ፊት ሲቆም። የሚነደው ፍሕም ላይ የገባው ዕጣን ያለከልካይ ብቻውን ሲንቦለቦል። የካህናቱ ዜማ እንደ ንፁሕ ምንጭ ውሃ ኩልል ሲፈስ። የእጣኑ መዓዛ ጅረት ሆኖ ቤተክርስቲያኑን ሲዞር ለተመለከተው የሰማይ ሥርዓት በምድር እንደተሰራ የሚያመላክት አንዳች ኃይል አለው ፡፡

ሕፃናት ጃንጥላዎቻቸውን ዘርግተው የቤተክርስቲያኑን ግንብ ተደግፈው ይቀመጣሉ፡፡ በጊቢው ውስጥ የተገኙት ምዕመናን "ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሃት" የሚለውን የዲያቆኑ ትዕዛዝ ተከትለው "ቅድሜከ እግዚኦ ንሰግድ" እያሉ በሕብረት ይሰግዳሉ።

ሁለት አንድ አይነት የሆኑ የካሕናት ዜማዎች ከቤተመቅደሱ አናት ላይ ይፈሳሉ። በልጅነቴ የሰማሁት ቅዳሴ ማርያም ዛሬምድረስ ይታወሰኛል። የእመብርሃን…. የወላዲተ አምላክ ቅዳሴ እኮ ነው ።

አኮቴተ ቊርባን ዘእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘደረሰ በመንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ ኤጲስ ቆጶስ ዘሀገረ ብህንሳ ። ሁላችንም ይህን የቅዳሴ አንቀጽ የሰማነው በልጅነታችን አእምሮ ነው። "

"...ጎሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ ወአነ አየድሕ ቅዳሴሃ ለማርያም አኮ በአብዝኆ አላ በአውሕዶ" የቀዳስያኑ ድምጽ ባለ ግርማ ሞገስ ነበር (አሁንም ነው ድረስ ነው) ። ፍሬ ቅዳሴውን እየተቀባበሉት ሲደግሙት። አንድ ቀን በግዕዝ። በሌላኛው ቀን ደሞ በአማርኛ ንባቡን ሲዘልቁት። ዛሬም በአዕምሮዬ ትዝታ ሆኖ ቀርቷል፡፡

"ድንግል ሆይ አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ እንደ ዕብራዊን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለም በንፅሕና በቅድስና በቤተመቅደስ ኖርሸ እንጂ….."

"ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥ የጠጣሽ አይደለሽም ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥ ነው እንጂ ….. "