Get Mystery Box with random crypto!

መንፈሳዊ ጉባኤ: Henok: #ጷግሜን_ለምን_እንጾማለን? #ጷግሜን_ለምን_እንጠመቃለን? #በመጠ | "ቃለ እግዚአብሔር "

መንፈሳዊ ጉባኤ:
Henok:
#ጷግሜን_ለምን_እንጾማለን?

#ጷግሜን_ለምን_እንጠመቃለን?

#በመጠመቃችን_የምናገኘው_ጥቅም_ምንድን_ነው?

#ጷግሜን_መጠመቅ_መተት_እና_ድግምትን_ይሽራል፡፡

#ጷግሜ_ሦስት_ርኅወተ_ሰማይ_ነው_ሰባቱ_ሰማያት_ይከፈታሉ ጸሎታችን በሙሉ ያርጋል፡፡

/ዩ ትዩብ ላይ የለቀኩትን ትምህርት በጽሑፍ ቃል በቃል አቅርቤላችኃለሁ/

የወለላይቱ እመቤት ልጆች እንደሚታወቀው ወርኃ ጳግሜ፤ ኢትዮጲያን ብቸኛዋ ባለ አሥራ ሦስት ወራት ሀገር ያደርገች ልዩ ወር ናት፡፡ ታዲያ ይህችህ በሦስቱ ወንጌላውያን አምስት ፣ በዘመነ ዮሐንስ በአራት ዓመት ስድስት ቀን የምትሆነው ጳግሜ፣ ብዙ ምስጢር እና ልዩ ጥቅም የላት ወር ናት፡፡

#ጳግሜን_ለምን_እንጾማለን?

የጳግሜ ወር በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት የዓለም ፍጻሜ መታሰብያ ወር ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ ጳግሜ የዓመታት መሸጋገሪያ፤ ጨለማው የክረምት ወቅት፤ ወደ ማብቂያው እና የሚያልፍበት፤ እንደ ሆነ ሁሉ፤

ዳግም ምጽዓትም ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ፤ ከጊዜያው ወደ ዘላለማዊ መሻጋገሪያ በመሆኑ ጳግሜ የእለተ ምጻት ምሳሌ የሆነችው፡፡ በዚህም ምክንያት የኦርቶዶክስ አማኞች የጳግሜን ወር በሱባኤ በጾም በጸሎት ያሳልፋሉ፡፡ በገዳም ያሉ አባቶች ጳግሜን በዝግ ሱባኤ ያሳልፋሉ፡፡

በእግርጥ ጳግሜ ከሰባቱ አጽዋማት ውስጥ ባትካተትም፤ ጳግሜን በግዴታ ሳይሆን በውዴታ ብንጾም የበረታን ሱባኤ ብንይዝባት፣ የቻልን በታቅቦ ብናሳልፋት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡

አንደኛ በፈቃዳችን በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በሱባኤ ብናሳልፍ ጸጋና በረከት ያሰጠናል፡፡ ሁለተኛው ጳግሜ የአዲስ ዓመት መቀበያ የዋዜማ ቀናት በመሆኗ፤ አዲሱን ዓመት በጾም፣ በጸሎት በሱባኤ ብንቀበል አዲሱ ዓመት የበረከት፣ የረድኤት ይሆንልናል፡፡

አዲሱን ዓመት በተለይም በዋዜማው በመዝናናት፣ በመጨፈር፣ በመጠጣት እና በመዘሞት ከምንቀበል፤ በጸሎት ብንቀበል አዲሱ ዓመት የበረከት ዓመት፣ ያሰብነው ያቀድነው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚሳካበት ይሆናል፡፡

ቅድም እንዳልኩት የገዳም አባቶቻችን የጳግሜን ወር፤ መንፈሳዊ ጥቅም ስለሚያውቁ፤ በፈቃዳቸው በታላቅ ሱባኤ ሆነው ስለ ሀገር፣ ስለ መጪው አዲስ ዓመት መልካምነት ፈጣሪን ይማጸኑበታል፡፡ እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን እና፣ እነሱ የሄዱበትን መንገድ ተከትለን፤ እንደ እነሱ ልንጠቀም ያስፈልጋልና፤ ወርኃ ጳግሜን በጾም በጸሎት እና በሱባኤ ብናሳልፍ እንጠቀማለን፡፡

በተለይ በአሁኑ ጊዜ እኛም፣ ሀገራችንም ቅድስት ቤተ-ክርስትያናችንም የገጠመን ፈተና፣ እጅጉን ከባድ ነውና እግዚአብሔር እንዲታረቀን፣ ገጸ ምህረቱን እንዲመልስልን፣ ወረርሽኙን እንዲያጠፋልን፣ ለቅድስት ቤተ-ክርስትያናችንና ለሀገራችን ጽኑ ሰላም እና አንድነት እንዲሰጥልን ወርኃ ጳግሜን እንደ በፊቱ በመብላት በመጠጣት ሳይሆን በጾም በጸሎት ብናሳልፍ ጥቅሙ ለእኛው ነው፡፡

#ጳግሜን_ለምን_እንጠመቃለን?

#በመጠመቃችን_ምን_ጥቅም_እናገኛለን?

እንደሚታወቀው ብዙዎቻችን ወርኃ ጳግሜን እንጠመቃለን፡፡ ጳግሜን የምንጠመቅበት ዋናው ምክንያት ከሊቀ መልአኩ ከቅዱስ ሩፋኤል ጋር የተያያዘ ነው፡፡

በዚህ በጳግሜ ወር በዓለም ላይ ያሉ ውቅያኖሶች፣ ባህሮች፣ ወንዞች፣ ኩሬዎች ጸበሎች በአጠቃላይ ውሃዎች ሰማይ ተከፍቶ፣ በመላክእት የሚባረኩበት ስለሆነ፤ ጳግሜን የቻልን ጸበል ቦታ ሄደን፣ ወይም በአከባቢያችን ጸበል ካለ እዛም ሄደን፤ መሄድ ባይመቸን፣ ቤታችን ውስጥ ባለው ውኃ ብንጠመቅ እንባረክበታለን፣ ከበሽታችንም እንድንበታለን፡፡

በጳግሜ ጸበል፣ እንኳን የሰው በሽታ፤ በሽታ ያለው እህል፣ በሽታው ይለቀዋል፡፡ ገበሬው ከጳግሜ ወዲያ ነው የሚጠፋውንና የማይጠፋውን እህል የሚለየው፤ በተለይ ዘንጋዳ ጳግሜ ላይ ነው በደንብ የሚያስታውቀው፡፡

በአባባልም ‹‹ዘንጋዳ እና ቡዳ ከመስከረም ወዲያ›› ነው የሚያስታውቀው ይባላል፡፡ የሚገርመው አባቶቻችን ጳግሜ ሦስት ሌሊት ስድስት ሰዓት በተለይ ፏፏቴ ያለው ወንዝ፤ ውሃው ሲቆም ያዩታል፡፡

ቀድሞ አባቶቻን ይህንን ተአምር ለማየት ጳግሜ ሦስት ሌሊት በተለይ ፏፏቴ ያለበት፣ ትልቅ ወንዝ ዳር ሄደው ያድሩ ነበር፡፡ ውሃው ቀጥ ብሎ ሲቆም ሰማይ ሲከፈት ያዩ ነበር፡፡ ጳግሜን በተለይም ጳግሜ ሦስት፣ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በአሉ ስለሆነ፤

በዚህ ቀን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ውሆችን የሚባርክበት፤ እና ለሰው ልጆች በፈጣሪው ጸጋ፤ ድህነት እና ፈውስ የሚያሰጥበት ቀን ስለሆነ ብንጠመቅ ከበሽታችን እንድናለን፡፡

በመጸሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ ወንጌል በምዕራ 5 ቁጥር 4 ላይ ‹‹አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ፣ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኃላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸውም ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር›› ይላል፡፡

የጌታ መልአክ ‹‹ውኃውን ያናውጥ ነበር›› የተባለው፤ ከሰማይ ወርዶ ውኃውን ይባርከው ነበር ለማለት ነው፡፡ ውኃውም የሚናወጠው የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ሲባርከውና እና በመጠመቂያው፣ ለፈውስ ደጅ የሚጠኑት፣ ህሙማን ውሃው በመልአኩ መባረኩን የሚያውቁት ውኃው ሲናወጥ ነው፡፡

ዛሬም እንደ ቀድሞ ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል፤ በዓለም ላይ ያሉትን ውሃዎች ሁሉ ስለሚባርካቸው፤ ብንጠመቅባቸው እንፈወሳለን፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቅዱሳን መላእክትም ውኃውን ይባርኩታል፡፡

ጳግሜ ሦስት ይህ ብቻ አይደለም ሊቀ መልአኩ ያስለመደን ነገር አለ፡፡ ይህም ሁል ጊዜ ጳግሜ ሦስት ሌሊት፣ ጠዋት፣ ከሰዓት አልያም ማምሻ ላይ ይዘንባል፡፡ ይህ ከሰማይ የሆነ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ጸበል ነው፡፡

በልጅነታችን ጳግሜ ሦስትን ‹‹ሩፋኤል አሳድገኝ›› እያልን እንጠመቃለን፡፡ ጳግሜ ሦስት በዘነበው ውኃ መጠመቅ ትልቅ መታደል እና ፈውስ ነው፡፡ በደዌ ይሰቃይ የነበረው ኢዮብም በዚህ ሳምንት ነው ተጠምቆ ነው የዳነው፡፡

የሚገርማችሁ በዚህ በከተማ ብዙም ስለማይታወቅ ነው እንጂ፤ በገጠር እና በክፍለ ሀገር የቅዱስ ሩፋኤል እለት የዘነው ዝናብ በእቃ ይቀዳና ይቀመጣል፡፡ በተቀዳው ጸበል ቦሃቃው ይረጭበታል፣ በውሃው እህሉ ይቦካበታል፣ ቤቱ ደጁ ይረጭበታል፡፡

ይህም የሚሆነው የቅዱስ ሩፋኤል እለት የዘነበው ውኃ የሰላቢ መንፈስን ስለሚያርቅ ነው፡፡ የሰላቢ መንፈስ ከቤታችን የእህል በረከት የሚያሳጣ፣ ለአንድ ወር ያሰብነውን ለሳምንት የማያዳርስ፣ ለዓመት ያልነው በሦስት ወር እንዲያልቅ የሚያደርግ፤ ክፉ መንፈስ ስላለ ይህን ያርቅልናል፣ በጸበሉ በረከት እህል አስቤዛውን ያበረክትልናል፡፡

እንደምታውቁት ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት ሦስተኛው ነው፡፡ በመጀመሪያዋ እለተ ፍጥረት እግዚአብሔር መቶ ነገደ መላእክት ፈጥሮ በአሥር ከተማ ሲያኖራቸው

ቅዱስ ሩፋኤል ራማ ላይ ነው ከነ ሠራዊቱ ያረፈው ወይም የከተመው፡፡ በራማም መናብርት ተብለው ለሚጠሩት አሥሩ ነገድ አለቃ ወይም መሪ ሆኖ በእግዚአብሔር ተሹሟል፡፡ በኃላም መጋብያን በሚባሉ በሃያ ሦስቱ ነገድ ላይ ተሹሟል፡፡

ስለዚህ ጳግሜ ሦስት የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል በዓለ ሲመት ወይም የሹመት በዓሉ ነው፡፡

ይህንንም እራሱ ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በመጽሐፈ ጦቢት ምዕራፍ 12 ቁጥር 15 ላይ ‹‹ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ›› በማለት ተናግሯል፡፡