Get Mystery Box with random crypto!

የስሙንም ትርጉም ስንመለከት ‹‹ሩፋ›› ማለት ሐኪም ማለት ነው፡፡ ኤል ማለት እግዚአብሔር ማለት ነ | "ቃለ እግዚአብሔር "

የስሙንም ትርጉም ስንመለከት ‹‹ሩፋ›› ማለት ሐኪም ማለት ነው፡፡ ኤል ማለት እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሩፋኤል ማለት የእግዚአብሔር ሐኪም ማለትነው፡፡ ሌላው መልአከ ሰላም ወጥዒና ወይም የሰላም እና የጤና መልአክ ይባላል፡፡

የሰው ልጆችን ከተያዙበት ከተለያዩ በሽታውች በጸሎቱ፣ በአማልጅነቱ እንዲፈውስ ስልጣን እና ጸጋ የተሰጠው ታላቅ መልአክ ነው፡፡
ሩፋኤል ማለት የእግዚአብሔር ሐኪም ማለት መሆኑን ነብየ

እግዚአብሔር ቅዱስ ሄኖክ በመጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 10 ቁጥር 13 ላይ ‹‹በበሽታ ሁሉ ላይ፣ በሰው ልጆችም ቁስል ላይ፤ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው›› እንዲሁም እዛው መጽሐፈ ሄኖክ ምዕራፍ 6 ቁጥር 3 ላይ

‹‹በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መልእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው›› በማለት እግዚአብሔር ለቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የወጣውን፤ ቁስል እና ደዌ፤ ይፈውስ ዘንድ ስልጣን እንደሰጠው፣ ሐኪም እንዳደረገው ነግሮናል፡፡

እንዲሁም ፈታሄ ማሕፀን ይባላል፡፡ እንኳን በምጥ የተያዙትን ሴቶች፣ እናቶች፤ ቀርቶ እንስሳት እንኳን ምጥ ሲፀናባቸው፣ ስሙን ከጠሩት ይፈታቸዋል፡፡ ይህ መልአክ በተለይ ለሴቶች እጅጉን ረዳታቸው ነው፡፡ ከፀነሱበት ጊዜ አንስቶ እስኪወልዱ አይለያቸውም፡፡

በተለይ በእርግዝናቸው ጊዜ ስሙን እየጠሩ፣ መልኩን እየጸለዩ፣ ጸበሉን እየጠጡ እየተዳበሱ፣ ከተማጸኑት ጭንቀታቸውን ያቀላል፣ በሰላም ያዋልዳቸዋል፡፡

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይሁንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፤ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችንን ስለ ቅዱስ ሩፋኤል እንዲያሳውቃቸው፣ ክብሩን እንዲገልጽላቸው ጠየቁት፡፡ ጌታም ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅዱስ ሩፋኤልን እንደሚመጡ አዘዛቸው፡፡ እነሱም መጡ፡፡

ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ስለ ራሳቸው ከተናገሩ በኃላ ጌታም ቅዱስ ሩፋኤልን ‹‹ክብርህን ንገራው›› አለው፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም ለጌታ ሰግዶ ለሐዋርያት ብዙ ምስጢር ነገራቸው፡፡

በተለይም ስሙን ለሚጠሩ፣ መታሰብያውን ለሚያደርጉ፣ በጸሎቱ ለሚማጸኑ፣ እንደማይለያቸው፣ እንደሚረዳቸው፣ ክብር እንደሚያሰጣቸው ለሐዋርያት ነግሯቸው ወደ ሰማያት አርጓል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም በወቅቱ ወንጌልን ሲያስተምሩ፣ ስለ ቅዱስ ሩፋኤል ክብር እና በእሱ የሚገኘውን መልአካዊ እርዳታ፣ ለምዕመናኑ በደንብ አስተምረዋል፡፡

ቅዱስ ሩፋኤል ልቦናን ደስ የሚያሰኝ፤ ባለ መድኃኒት ፈዋሽ፤ የጸሎት መዝገብ መክፈቻ የተሰጠው፤ በዙፋን ላይ በክብር የሚቀመጡ መላእክት መሪ፤ የሰውንም ይሁን እንስሳን ማሕፀን የሚፈታ፤ አዋላጅ፣ ምጥን የሚያቀል፣ ታላቅ መልአክ ነውና እንጠቀምበት፡፡

ስለዚህ የቅዱስ ሩፋኤል ቀን የዘነበውን ዝናብ በዕቃ ቀድታችሁ አስቀምጡ፡፡ ያንንም ጸበል ቤታችሁን፣ ደጃችሁን፣ እንዲሁም የሥራ ቦታችሁን እርጩበት፣ እየቆጠባችሁ እህል ስታቦኩ አብኩበት ጠጡት ተጠመቁበት፡፡ ብዙ በረከት እና ፈውስ ታገኙበታላችሁ፡፡

እህል እና ገንዘብ የሚሰልብባችሁን የሰላቢ መንፈስ ያርቅላችኃል፡፡
ውጭ ሀገር ያላችው እህት ወንድሞቼ ጸበል መጠመቅ ስለማይመቻችሁ፤ ውኃ አቅርባችሁ፣ ያስለመዳችሁትን ጸሎት ውሃው ላይ ጸልያችሁ ‹‹አምላከ ቅዱስ ሩፋኤል›› ባርክልኝ ብላችሁ ቤት ውስጥ ተጠመቁ ጠጡት፡፡

ጳግሜን መጠመቅ ከጥንት አባቶቻችን ጀምሮ የነበረ እና በየአመቱ ጳግሜን መጠመቅ የሚናፈቅ ጊዜ ስለሆነ ተጠቀሙበት፡፡ በዚሁ አጋጣሚ እኛም እንጦጦ ማርያም ጳግሜን የጸበል አገልግሎት ስለምንሰጥ መጥታችሁ መጠመቅ ትችላላችሁ፡፡

#ጳግሜ_ሦስት_ርኅወተ_ሰማይ_ነው_ሰባቱ_ሰማያትይከፈታሉ_ጸሎታችን_በሙሉ_ያርጋል፡፡

ጳግሜ ሦስት ርህወተ ሰማይ ይባላል፡፡ ርኅወተ ሰማይ ማለት የሰማይ መከፈት ማለት ነው፡፡ ይህም የሰማይ መስኮቶች ወይም ደጆች የሚከፈቱበት እለት ነው፡፡ ርኅወተ ሰማይ ወይም የሰማይ መከፈት ሲባል፤ በሰማይ መከፈት እና መዘጋት ኖሮበት ሳይሆን፤

ቅዱሳን መላእክት የሰውን ልጆች ጸሎት፣ ልመና፣ ያለ ከልካይ፤ ወደ እግዚብሔር የሚያሳርጉበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ እንዲሁም ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል የዓመቱን የጸሎት መዝገበ የሚከፍትበት ቀን ስለሆነ ነው ርኅወተ ሰማይ የተባለው፡፡

በእርግጥ በንስሐ ሆኖ ለሚጸልይ ሰው ለእርሱ ሁሌም የሰማይ ደጅ የተከፈተ ነው፡፡ ከዓመት ተለይታ ጳግሜ ሦስት የሰማይ መስኮቶች፤ ወይም ደጆች በሙሉ ተከፍተው፣ የምዕመናን ጸሎት በተለየ ሁኔታ የሚያርግበት ጊዜ እንደ ሆነ ሊቃውንተ ቤተ-ክርስትያንም ይነግሩናል፡፡

ስለዚህ በዚህም ቀን ማለትም ጳግሜ ሦስት ያስለመድናቸውን ጸሎቶች፤ አንዳንዶቻችንም ያቋረጥናቸውን ጸሎቶች፤ በርትተን ብንጸል ቅድመ እግዚብሔር ይደርሳል፡፡

በዚህችም ቀን የጸለይነውን ጸሎቶች፤ ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል እና ቅዱሳን መላእክት ቅድመ እግዚብአብሔር ያሳርጉልናል፡፡ በዚህችም እለት የእግዚአብሔር ምህረት እና ቸርነት ለሰው ልጆች የሚወርድበት ታላቅ እለት ነው፡፡

አባቶቻችን እንደሚነግሩን ከሆነ፤ ጳግሜ ሦስት ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ጀምሮ፤ ያስለመዱትንና ሌሎችንም ጸሎቶች ሲጸልዩ ያድራሉ፡፡ ስለዚህ እኛም እንደ እነሱ ማድረግ ባንችል፤ የበረታን ሌሊት ስድስት ሰዓት፤ የቻልን ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ተነስተን ጸሎት ልንጸልይ ይገባናል፡፡

#ጳግሜን_መጠመቅ_መተት_እና_ድግምትን_ይሽራል!

የወለላይቱ እመቤት ልጆች እንደምታውቁት ያለንበት ጊዜ አጋንንት ተፈቶ የተለቀቀበት፣ ሰው በክፋት ከአጋንንት ያልተናነሰበት አንዳንዴም የሚበልጥበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ በተለይ ብዙ ምዕመናን በመተት በድግምት እድላቸው ተወስዶ፣ ሕይወታቸው ባዶ እየተደረገ ነው፡፡

አጋንንት ጎታቾች እና መተት መታቶች ጳግሜን በሰው ላይ የሚመትቱትን መተት የሚያድሱበት ስለሆነ ጸበል በርትተን ብንጠመቅ እድሳታቸው ይሽራል፣ መተታቸውም ይከሽፋል፡፡ ስለዚህ በዚህ በወርኃ ጳግሜ በመተት እና በድግምት የምትሰቃዩ ወገኖቼ በርትታችሁ ጸበል ተጠመቁ ጠጡ፡፡

ምክንያቱም ዓመቱን ሙሉ በእድላችን ሲመተት ወደ እና ሕይወት ሲጎተት የነበረው አጋንንት ጳግሜን በርትተን ከተጠመቅን አጋንንቱ አዲሱን አመት አይሻገርም፡፡

በተመተተብን መተት እና በበላነው ድግምት ውስጣችን በተለይ ሆዳችን፣ እንዲሁም መላ አካላታችን ላይ ደዌ ሆኖ የተቀመጠው አጋንንት ይለቀናል፣ ውስጣችን ያለው የደዌ መተት ይሻራል፡፡
እንዲሁም በአውደ ዓመት መስከረም አንድ ቀን በቅዱስ ዮሐንስ ስም አስታከው ዛር አንጋሾች፤ ለዛር ደም የሚያፈሱበት፣ የሚገብሩበት ጊዜ ነው፡፡

አዲሱን አመት ደም በማፍሰስ፣ ለዛር በመገበር ስለሚቀበሉ ጸበል መጠመቁ ከእዚህ ችግር እናመልጣለን፡፡ በተለይ ቤተሰባችሁ በቅዱስ ዮሐንስ የሽፋን ስም ‹‹ለዓውደ ዓመት ነው፣ ለአድባር ነው፣ አዲስን ዓመት ለመቀበት ነው፣ የእናት አባታችን የአያቶቻችን አምላክ እንዳይጣላን ነው፣

በአዲሱ ዓመት ጠላታችን ደሙ እንዲፈስ ነው፣ ደም የምናፈሰው የእኛን ጦስ ይዞ እንዲሄድ ነው›› በማለት ገብስማ፣ ወሰራ፣ ባለ ነጠላ ዶሮ፤ ነጭ፣ ቀይ በግ እያሉ ያረዱትን እንዳትበሉ፡፡

አውቃችሁ በዮሐንስ ስም ለዛር የተገበረለትን ብትበሉ በደም የገባውን ዛር፤ በጸበል ለማስወጣት ትቸገራላችሁ፡፡ በቤታችሁ፣ በአከባቢያችሁ እንደዚህ አይነት ክፉ ልማድ ካለ ተቃወሙ፣ ለማስተው ሞክሩ፡፡ የእነሱ እዳ ነው ነገ ለእናንተ የሚተርፈው፡፡

በተረፈ ይህችን ወርኃ ጳግሜን እንደ አባቶቻችን እንድንጠቀምባት አምላከ ቅዱስ ሩፋኤል ይርዳን፡፡