Get Mystery Box with random crypto!

ሰዎች ባዩት ነገር እየተደነቁ ልባቸውን ለእግዚአብሔር ይከፍቱ ነበር። ጆሮአቸውን ለወንጌል ይከፍቱ | "ቃለ እግዚአብሔር "

ሰዎች ባዩት ነገር እየተደነቁ ልባቸውን ለእግዚአብሔር ይከፍቱ ነበር። ጆሮአቸውን ለወንጌል ይከፍቱ ነበር። ብዙዎች ጌታችንን አምነው ነበር። ብዙዎች ወደ እግዚአብሔር መንግስት ይጨመሩ ነበር። ሐዋርያትም በተአምራቱ የተከፈተውን የሰዎችን ልብ ተጠቅመው፣ ወዲያው ወንጌልን ይዘሩ ነበር። እግዚአብሔር በብዙ ድንቅና ተአምራት ቃሉን በመካከላቸው ያጸና ነበር። ዛሬም ምናልባት እግዚአብሔር በእጃችን ድንቅና ተአምራቶችን ያደርግ ይሆናል። እነዚህ ተአምራቶች ግን ለራሳችን የሰዎችን ትኩረት መሰብሰቢያዎች እንዳናረግ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ይልቁንም ትንሽም ሆነ ትልቅ እግዚአብሔር በእኛ ተጠቅሞ የሰራው ነገር ካለና የሰዎችን ትኩረት እግዚአብሔር ከሰጠን፣ ቶሎ ብለን ስለ ተአምራት አድራጊው መናገር፥ እኛን ስለወደደበት ፍቅር የሰው ልጆችን ሁሉ ከኃጢያት በሽታ ለማዳን መሰቀል መሞቱን፣ ሞትና አገንንታዊ አሰራርን ድል አድርጎ መነሳቱን ለሰዎች መመስከር ይኖርብናል። የእግዚአብሔር የልቡ ትርታ ሰዎች ከጨጉዋራ በሽታ መፈወሳቸው አይደለም። ስለ ምድራዊ ፈውሶቻችን ግድ የሚለው አምላክ ቢሆንም፣ ዋናና ትልቁ አላማው ግን ሰዎችን ከኃጢያት በሽታና ዘላለማቸውን ከሚያሳልፉበት ከዘላለም ጨለማ አውጥቶ ወደ ዘላለም መንግስቱ ማስገባት ነው።

ታዲያ እግዚአብሔር ለዘላለም የሚሰጠው ቦታ እጅግ በጣም ትልቅ እንደሆነ ከተረዳን፣ ስኬት ከእግዚአብሔር እይታ አንጻር ምንድነው? ስኬት ከዘላለም አንጻር ሲታይ ወይንም፣ 70 እና 80 አመታቶችን አልፎ ማየት በሚችለው መነጽራችን ስናየው ምንድነው? እግዚአብሔር አንድን ሰው የተሳካ ህይወት ነበረው የሚለው ያ ሰው በምድር ላይ በተሰጠው ጥቂት ዘመናቶች ምን አይነት ህይወት ሲኖር ነው? ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ እንግዲህ፣ ከእኔ ተማሩ ያለው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ከኖረባቸው ስኬታማ አመታቶች በላይ ሌላ ሊያስተምረን የሚችል ነገር የለም። ቅዱሳን አባቶቻችንም በተሰጣቸው በጣም አጭር አመታቶች እያንዳንዱን የተሰጧቸውን ጊዜያቶች በትክክል በመጠቀም ስኬታማ ሆነው ያለፉና እኛም አሁን እየኖርን ላለነው ህይወት ትልቁ ምሳሌዎቻችን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ቅዱሳን አባቶቻችን በምድር ላይ የኖሩባቸው አመታቶች ናቸው። አባቶቻችን በኖሩባቸው ጥቂት አመታቶች ውስጥ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ አምልኮት የነበራቸውና በትክክል የሄዱ፣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያውቁ ማድረግ ላለባቸው ነገሮች በሙሉ ትክክለኛውን ጊዜ እያወቁ በትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛውን ነገር የሚያደርጉ ሁልጊዜ ተልኮ እንዳላቸው የማይረሱ፣ የቀንና የለሊት ሀሳብና ምኞታቸው የእግዚአብሔር የአባታቸውን ፈቃድ መፈጸምና ማገልገል ነው። ጌታችንም ፍጹም አምላክ ብቻ ሳይሆን፣ ልክ እንደ እኔና እንደ እናንተ ፈታኝ የሆነውን ስጋ ለብሶ በምድር ላይ የተመላለሰ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ታዲያ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን መጨረሻ ላይ፣ የሰጠኸኝን ስራ ፈጽሜ አከበርኩህ በማለት በነበረበት ዘመን መስራት ያለበትን ሁሉ ሰርቶ ጨርሶ ስኬታማ የሆነ ሰው ንግግርን ሲናገር እንሰማዋለን። ከዚህ ንግግሩ፣ ሊሰራ የተሰጠው ስራ እንደነበረ ወይንም እንደመጣ መረዳት እንችላለን። ታዲያ ቃሉን ስታነቡ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሰራ ባሰበው የምድር ቆይታው ውስጥ አንድ እየደጋገመ የሚናገረውና ሁልጊዜ ትኩረት የሚሰጥበት አንድ ነገር ነበር።
የእግዚአብሔር ፈቃድ። ፈቃዴን ለማድረግ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው የመጣሁት ይላል። አካባቢው ላይ ያሉ ሰዎችን ፈቃድም አያደርግም። ጊዜያዊ ጥቅም ሊያስገኙለት የሚችሉትን ጥሩ ጥሩ እድሎችና አጋጣሚዎችም አይጠቀምባቸውም። ሰዎች ተሰብስበው እናንግስህ ሲሉትም አልፈልግም እያለ ጥሎዋቸው ይሄዳል። የእሱ ልብ ያለው ከፍታም ዝቅታም ጋር አይደለም። ልቡ ያለው የተላከበትን ወይንም ወደ ምድር የመጣበትን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መኖርና ማገልገል ላይ ብቻ ነው። ከተላከበት አጀንዳ ትንሽ ፈቀቅ የሚያረገው አጋጣሚም፣ እድልም፣ ከፍታም ዝቅታም አልነበረም። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ የልቡ ምኞት ደግሞ የላከውን የአባቱን ፈቃድ መፈጸም እንደነበረ፣ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለው ብሎ ልኮናል። የላከን ደግሞ የእሱን ሀሳብና ፈቃድ እንድንኖርና እንድናገለግል ነው። እሱ የኖረውን ህይወት እንድንኖር ነው። በዚህ በተላክንበት ህይወት ውስጥ፣ የመጀመሪያው ሀላፊነታችን እንደ ተላከ ሰው ማሰብ መጀመር ነው። የሆነ ነገር ለመስራትና ለማገልገል የተላኩ ሰዎች ነን። በየቀኑ የምንሰራውና የምናደርገው ደግሞ የላከንን ሀሳብና ፈቃድ ነው። ከላከን ጋር በጸሎትና ቃሉን በማንበብ ያነበብነውን ደግሞ ለመኖር በመሞከር ውስጥ የጠበቀ አንድነት አለን። በዚህ አንድነታችን ውስጥ የሚሰጡንን ምሪቶች በመቀበል በየቀኑ እንኖራቸዋለን። የየቀኑ ኑሮአችን በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ የተጠበቀ ነው። የምናገለግለውም፥ አገልግሉ ተብለን የተላክንበትን መልእክት ብቻ ነው። በዚህ ውስጥ እግዚአብሄር እኛን ያውቀናል። ዋናውና ትልቁ የህይወት ስኬታችን ይሄ ብቻ ነው። የልቡን ሀሳብ መኖርና ማገልገል። ሳይፈጥረን በፊት ስለ እኛ የጻፈውን በየቀኑ መኖር። ልክ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን ዋጋ የምንከፍልበትን ህይወትና አገልግሎት ለእግዚአብሔር እንደ መስዋእት ማቅረብ። ፈቃዳችንን በሙሉ ለፍቃዱ ማስገዛት። ለዘላለም የእርሱ ባሪያዎች በመሆን ውስጥ ያለውን ዘላለማዊ ክብር ማግኘት። እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ዝቅ ብሎ፣ በዘላለም ውስጥ ከፍ ማለት። ከምናልፍበት የምድር ውጣ ውረድ፣ ስቃይና መከራ ጋር የማይወዳደረው ዘላለማዊ ክብር ውስጥ መግባት። በመድኃኒታችን ውስጥ ያገኘነውን ልጅነት ጠብቆ የእግዚአብሔርን የመንግስቱ ተካፋዮች መሆን፣ በዘላለም እረፍት ውስጥ ለዘላለም መኖር። ይሄ ነው የእኛ ግብ። ይሄ ነው የእኛ ስኬት። 2014ዓ ም እንዴት አለፈ ምን አሳካን? ስኬታችንስ በምን ይመዘን? መጪውን ዓመት ስኬት ብለን ማቀድ ያለብን ምድራዊ ነገሮችን በማሳካት ሳይሆን በዋነኝነት ስለዘለዓለማዊ ህይወታችን በማሰብ፣ የላከንን፣ የፈጠረንን አምላክ ፈቃድ መፈፀም ላይ ትኩረት እናድርግ።

ቀሲስ ሳሙኤል አያልነህ

@KaleEgziabeher