Get Mystery Box with random crypto!

ሸረሪት በሳይንስ እና በኢስላም እይታ ወንዱ ሸረሪት የዘር ፈሳሹን ወደ እንስቷ ሸረሪት ካስተላ | ISLAM IS UNIVERSITY

ሸረሪት በሳይንስ እና በኢስላም እይታ

ንዱ ሸረሪት የዘር ፈሳሹን ወደ እንስቷ ሸረሪት ካስተላለፈ በኃላ አብዛኃኛውን ጊዜ እጣ ፈንታው ምን እንደሆነ ያውቃሉ? ከእንስቷ ሸረሪት <እሰይ አበጀህ> የሚል የሙገሳ ቃል ሳይሆን የሚጎርፍለት ግድያ ነው የሚጠብቀው። ትገድለዋለች። ትበላዋለች። ሲያሻትም ሬሳውን ከቤቱ ውጭ አሸንቀጥራ ትጥለዋለች። ያ የዘር ፈሳሽ ግን አይመክንም። ልጆች ይፈጠራሉ።

ልጆቹ ካደጉ በኃላ በአባታቸው ላይ የተፈፀመውን ድርጊት ማን ሹክ እንዳላቸው በማናውቀው መንገድ ብቀላ ቢጤ ይጀምራሉ። የአባታቸውን ገዳይ ይበቀላሉ። እናታቸውን አፈር ድሜ ያበሏታል። ይገድሏታል። በአባታቸው የደረሰውን እጣ በእርሷም ላይ ይደግሙታል። ሬሳዋን ከቤቱ ውጭ አምዘግዝገው ይጥሉታል።

ከቤቶች ሁሉ በአስቀያሚነቱ ወደር የማይገኝለት ቤት ይህ ነው - የሸረሪት ቤት። ከቤቶች ሁሉ ደካማው ቤት።

የቁርዓን ተዝቆ የማያልቅ ሚስጢር ከብዙ አቅጣጫ የሚፈተሸ ነው። ቆፋሪ ይቀፍራል እንጂ የጥበቡን ስር ማክተሚያ መቼም አያገኘውም - ማክተሚያም የለው። ነገር ግን በቁፋሮው ሂደት የአቅሙን ያክል ዘርፈ ብዙ ጥበቦችን ያገኛል። በዚያም ይረካል። እስኪ ቁርዓን ከላይ ያየነውን ክፉ ቤት እንዴት አድርጎ በአንዲት አንቀፅ እንደሚገልፀው አብረን እንመልከት ፡-

مَثَلُ الَّذِينَ اتَّخَذُوا مِن دُونِ اللَّهِ أَوْلِيَاء كَمَثَلِ الْعَنكَبُوتِ اتَّخَذَتْ بَيْتاً وَإِنَّ أَوْهَنَ الْبُيُوتِ لَبَيْتُ الْعَنكَبُوتِ لَوْ كَانُوا يَعْلَمُونَ

<እነዚያ ከአላህ ሌላ ረዳቶችን የያዙት (ለራሷ) ቤት በሰራች ሸረሪት ይመሰላሉ። ከቤቶች ሁሉ ደካማው የሸረሪት ቤት ነው። (የአማልክቶቻቸውን ድክመት) የሚያውቁ ቢሆኑ ኖሮ (ባላመለኳቸው) ነበር።>

የሸረሪት ቤት ምን ያክል ደካማ እንደሆነ በግልፅ ሊታይ የሚችል ከመሆኑ አኳያ ሰዎች ይህንን ማወቃቸው አይደንቅም። ተጨባጭ የሆነም እውነታ ነውና። ሚስጢራዊ ደካማነቱን ግን ያወቁት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። ከላይ የሰፈረው አንቀፅ ማሳረጊያውም እንዲህ ይላል لَوْ كَانُوا يَعْلَمُونَ - "የሚያውቁ ቢሆኑ ኖሮ"

ይህ አንቀፅ የትኛው ምዕራፍ ውስጥ እንዳለ ያውቃሉ?
ሱረቱል አንከቡት ይሰኛል። የሸረሪት ምዕራፍ ማለት ነው። የምዕራፏ አብይ ርዕስ እምነትና ለእምነት ሲባል የሚከፈል መስዋዕትነት ፥ ለእምነት ሲባል የሚደርስ ፈተና ነው። ይህንኑ በማጉላት ትወጠናለች። እምነት በቃል ብቻ የሚባል ሳይሆን ፥ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ አማኞችም እውነተኛነታቸው በእሳት (በመከራ ፥ በገንዘብ) እንደሚፈተን ትገልፃለች። ከምዕራፉ የመጀመሪያ አንቀፅ እስከ ፍፃሜው ማለት ይቻላል የሚያትተው ስለ <ፈተናዎች> ነው።
ምዕራፉ በዚህች ነፍሳት ስያሜውን አግኝቷል።

ፈተናዎችን እና ሸረሪትን ምን አገናኛቸው የሚል አንዳች ጥያቄ አእምሮዎ ካጫረ እንዲህ እንላለን ፡-
የፈተና መልኩ እና ቅርፁ የሸረሪት ድርን ይመስላል። ፈተና የነገሰበት ክልል ውስብስብ ነው። የፈተና ቀጠና ጥልፍልፍ ነው። ክፉውን ከበጎው ለመለየት አዳጋች ነው። የተቆላለፈ መስክ ነው። መውጫ ቀዳዳው በውል አይታወቅም። ጠልፎ ይጥላል። አይነቱ ብዙ ነው። እጅግ በጣም ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ ይፈታተናል። ነገር ግን ያ ጥልፍልፉ የድር መከራ በአላህ ኃይል ብቻ ይበጣጠሳል። በእርሱ እገዛ ይንኮታኮታል።

በሌላ መልኩ ከላይ የሰፈረው አንቀፅ በዚህ ዩኒቨርስ ውስጥ ያሉ ኃይላትን ትክክለኛ ባህሪና ማንነት የገለፀ ምሳሌ ነው። ሰዎች ብዙ ጊዜ ይህን እውነታ ይዘነጉታል። በመሆኑም አመለካከታቸው ሲዛባ ፥ እይታቸው ሲበከል ፥ መዞር ወደሌለባቸው ኃይል ሲዞሩ ፥ መመካት በሌለባቸው አካል ሲመኩና ሊማፀኑት የማይገባውን ፍጡር ሲማፀኑ ይስተዋላል። እውነተኛ ኃይል የአላህ ኃይል ብቻ ነው። ከርሱ ውጭ ያሉ ኃይላት ጉልበታቸው እንደ ሸረሪት ድር ደካማ ነው። በነርሱ የተመካም ደካማ ቤት እንደያዘ ሸረሪት ይመሰላል። የተጠለለችበት ቤት ጉልበት ከርሷ ቢደክም እንጂ አይጠነክርም።
ሰዎች ይህን እውነት ይዘነጋሉ። ገንዘብ ፥ ስልጣን ወይም እውቀት ምድር ላይ ያሻቸውን ለማድረግ የሚያስችሏቸው ኃይሎች እንደሆኑ ያስባሉ። ለእነርሱ ያድራሉ። ይፈሯቸዋል። ያከብሯቸዋል። የእነርሱን ትሩፋት ለመማግኘት ፥ እነርሱን ላለማጣት ይጓጓሉ። ለነኝህ ኃይላት በማጎብደድ እውነተኛውን ኃይል (አላህን) ይዘነጋሉ። የእነኝህ ኃይላት ጉልበት ከሸረሪት ድር የጠነከረ እንዳልሆነ አይረዱም። ከአላህ ኃይል ውጭ ሌላ ኃይል የለም። ከአላህ ጥበቃ ውጭ ሌላ ጥበቃ የለም።

ሙስሊም ላልሆኑት ጥያቄ አለኝ! ታድያ ይህንን ሁሉ ጥልቅ ዕውቀት ያልተማረ፣ መፃፍና ማንበብ የማይችል ነብይ እንዴት ሊያውቅ ይችላል?

እንጠይቅ፣ እንመርምር።