Get Mystery Box with random crypto!

19ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ፡፡ 'ሙስናን መታገል በተግባር | Injibara University

19ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ፡፡

"ሙስናን መታገል በተግባር" በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ለ18ኛ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጋርዳቸወው ወርቁ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው በዘንድሮው ዓመት የህዝቡን ሮሮ እና ጥያቄ መሰረት በማድረግ ከጸረ ሙስና ኮሚሽን ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በተግባር የታገዘ ንቅናቄ እየተካሄደ መሆኑን አንስተዋል። እንደ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ነባራዊ ሁኔታ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የሥራ ክፍሎችን በመለየትና ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት ያለውን ክፍተት ለመሙላት በተግባር የታገዘ እንቅስቃሴ ከሁሉም ሠራተኛ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

የዕለቱን የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የፀረ-ሙስናና ሥነ- ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደሳለው ጌታሁን የፀረ ሙስና ቀን በየዓመቱ ኅዳር ወር እንደሚከበር ጠቅሰው የሁሉም ሀገራት ከፍተኛ ተግዳሮት የሆነው ሙስና እጅግ በረቀቀ መንገድ የሚፈፀም ወንጀል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ነቅቶ በመታገል የበኩሉን ሀገራዊ ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመነሻ ጽሑፉም የሙስና ምንነት፣ የሙስና ወንጀል ልዩ ባህሪያት፣ የፀረ-ሙስና ትግል በኢትዮጵያ አስቻይ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችና የባለድርሻ አካላት ሚና የሚሉ አርዕስቶች የተዳሰሱ ሲሆን የሥራ ክፍሉ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በበዓሉ አከባበር የሥነ-ጽሑፍ ዝግጅቶች እንዲሁም የዕለቱን በዓል የተመለከቱ የጥያቄና መልስ ውድድር በተማሪዎች የተካሄደ ሲሆን ለአሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ኅዳር 23/2015 ዓ.ም