Get Mystery Box with random crypto!

አስተማሪና መሳጭ ታሪክ! ~ በሰዑዲ የሚኖር የመኒ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ታሪክ እንዲህ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

አስተማሪና መሳጭ ታሪክ!
~
በሰዑዲ የሚኖር የመኒ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ያጋጠመውን ታሪክ እንዲህ ይተርከዋል፡፡
ከፊሌ የዘካ ገንዘብ ሊያከፋፍል ፈልጎ ከሱ ጋር ወጣሁ፡፡ የድሃ መንደሮች ወዳሉባቸው ጠረፍ አካባቢ ሄድን፡፡ የዘካው ገንዘቦች በፖስታ የታሸጉ ነበሩ፡፡ እያንዳንዱ ፖስታ በውስጡ 5ሺ ሪያል ይዟል፡፡ ከአንዱ መንደር ወጥተን የጂዳ-ጂዛን መስመር ስንይዝ አንድ የ70 አመት አካባቢ ሽማግሌ አገኘን፡፡ ሽማግሌው ብርቱና ጤናማ ነው፡፡ ጎዳናውን ይዞ ይጓዛል፡፡
ወዳጄ፡ “ይሄ ደግሞ በዚህ ሰዓት በዚህ በረሃ ምን ይሰራል?” አለኝ፡፡
ሹፌሩ፡ “ህገ ወጥ የመኒ ነው” አለ፡፡
ካጠገቡ ደርሰን ቆምንና ሰላም አልነው፡፡
* “ከየት ነው ወንድም?”
- “ከየመን”
* “የት ነው የምትሄደው?”
- “የአላህን ቤት ናፍቄያለሁ።”
* “ህጋዊ ነህ?”
- “አይደለሁም”
* “ለምን ህጋዊ አልሆንክም?”
- “ለዋስትና 2ሺ ሪያል ማስያዝ ይጠበቅብኛል፡፡ እኔ ያለኝ 200 ብቻ ነው፡፡ በመቶዋ ተሳፈርኩባት፡፡ የቀረኝ መቶ ብቻ ነው” አለ፡፡
* “እሺ አጎቴ! በጉዞ ላይ ምን ያክል ሆነህ?” አለው ጓደኛየ፡፡
- “ስድስት ቀን!”
* “እየፆምክ አይደለም ኣ?”
- “አይ ፆመኛ ነኝ፡፡”
* “ጥሩ፡፡ አንተ ከ 5 በላይ የፍተሸ ኬላዎችን አልፈሃል፡፡ እንዴት ነበር የምታልፋቸው?”
- “ከሱ በስተቀር እውነተኛ አምላክ በሌለው አላህ እምላለሁ! የማልፈው በነሱው ዘንድ ነው፡፡ ግን አንድም ያናገረኝ የለም!”
* “ለስራ ነው አመጣጥህ?”
- “በጭራሽ ወላሂ! እኔ የአላህን ቤት ናፍቄ ነው የመጣሁት፡፡ ዑምራ ማድረግ ነው የምፈልገው፡፡ ወደ መካ ነው የምጓዘው፡፡”
* “በአስፋልት ላይ ስትጓዝ ተዘዋዋሪ ዘቦች /ፓትሮል/ አልያዙህም?”
- “ከግማሽ ሰዓት በፊት በ 50 ኪ. ሜ. ርቀት ላይ ይዘውኝ ነበር፡፡ እዚህ ከመድረሴ አንድ ኪ. ሜ. ቀደም ብሎ ድረስ እነሱ ናቸው ያመጡኝ፡፡ የት እንደምሄድ ሲጠይቁኝ በአላህ ምየ የአላህን ቤት እንደምፈልግ ስነግራቸው ለቀቁኝ።”
* “ሱብሓነላህ! ጭራሽ እስከዚህ ቦታ በፍጥነት እንዲያደርሱህ አላህ ፓትሮሎችን አመቻቸልህ” አልኩኝ በውስጤ፡፡
- ወዳጄ ሁለት ፖስታዎችን እየሰጠው “እነዚህን ያዝ፡፡ ዘካ ነው” አለው፡፡
* እየተቀበለ “ጀዛኩሙላህ ኸይር” አለ፡፡
በፖስታዎቹ ያለው ገንዘብ መጠኑ ምን ያክል እንደሆነ አያውቅም፡፡
* “የሰዑዲን ብር ታውቃለህ?” አልኩት፡፡
- “አዎ!” አለ፡፡
* “ጥሩ፡፡ ፖስታውን ክፈትና እንዳይጠፋብህ ገንዘቡን በቀበቶህ (በሒዛምህ) ውስጥ ደብቅ” አልኩት፡፡
ሲከፍተው 10 ሺህ ሪያል!!
- “ይህ ሁሉ ለኔ ነው?” አለ፡፡
* “አዎ ላንተ ነው” አልነው፡፡
ከመኪናው ላይ ወደቀ፡፡ ራሱን ሳተ፡፡ ከመኪናው ወርደን በላዩ ላይ ውሃ መርጨት ያዝን፡፡
- “ይህ ሁሉ ገንዘብ ለኔ ነው? ይህ ሁሉ ገንዘብ ለኔ ነው?” እያለ መጮህ ያዘ፡፡ ቁጭ ብሎ ማልቀስ ቀጠለ፡፡
* ባልደረባዬ፡ “ከኛ ጋር ትንሽ ወደ ፊት እንውሰደው” አለ፡፡
ከኛ ጋር መኪና ላይ ወጣ፡፡ ትንሽ ሲረጋጋ ጠየቅኩት፡
* “ምንድን ነው ይህ ሁሉ ለቅሶ?” አልኩት፡፡
- “እኔ የመን ውስጥ ከቤቴ ጎን ቦታ አለችኝ፡፡ ለአላህ ሰጥቻታለሁ፡፡ እኔና ቤተሰቦቼ በሷ ላይ በጭቃና በድንጋይ አድርገን መስጅድ ገንብተንባታል፡፡ ግንባታው ቢጠናቀቅም ምንጣፍና ጥቂት ነገሮች ቀርተውት ነበር፡፡ ለዚህ መስጂድ እንዴት ምንጣፍ እንደማገኝ ተቀምጬ አስብ ነበር” አለ፡፡
ይህን ሲል የእውነት ሁላችንም አለቀስን፡፡ “አሳቡ ኣኺራ የሆነ ሰው ዱንያ እንዳለች ትመጣለታለች” የሚለውና “አሳቡ ኣኺራ የሆነ ሰው አላህ መብቃቃቱን ከልቡ ውስጥ ያደርግለታል፡፡ ነገሩንም ይሰበስብለታል፡፡ ዱንያ በግዷ ወደሱ ትመጣለች፡፡ አሳቡ ዱንያ የሆነ ደግሞ አላህ ድህነቱን በአይኖቹ መሀል ያደርግበታል፡፡ ነገሩንም ይበትንበታል፡፡ ከዱንያም የተወሰነለት ብቻ እንጂ አይመጣለትም” የሚለው የነብዩ ﷺ ንግግር ትዝ አለኝ፡፡
በዚህን ጊዜ ወዳጄን ለሰውየው እንዲጨምረው ጠየቅኩት፡፡ ተጨማሪ 2 እሽግ ፖስታ ሰጠው፡፡ በድምሩ 20 ሺ ሪያል አገኘ ሰውየው፡፡ ሰውየው ከመኪናው ከመውረዱ በፊት እያለቀሰ ያጉተመትምና ዱዓ ያደርግ ነበር፡፡
* “በአላህ ላይ እውነተኛ የሆነውን መመካት ብትመኩ ኖሮ ልክ ወፍን እንደሚረዝቀው ይረዝቃችሁ ነበር፡፡ ተርባ ወጥታ ጠግባ ትመለሳለች” የሚለው የነብዩ ﷺ ሐዲሥ መጣብኝ፡፡
የተተረጎመ
(ኢብኑ ሙነወር፣ መጋቢት 25/2010)

የቴሌግራም ቻናል፦
https://t.me/IbnuMunewor