Get Mystery Box with random crypto!

ኢስላም ያለ አንድ ሰይፍ አውሮፓን እያጥለቀለቀ ነው ~ ኢስላም በአሁኑ ሰዓት በምእራቡ አለም በከፍ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

ኢስላም ያለ አንድ ሰይፍ አውሮፓን እያጥለቀለቀ ነው
~
ኢስላም በአሁኑ ሰዓት በምእራቡ አለም በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ነው። ብሪታንያን እንደ ምሳሌ እንመልከት። መረጃዎቼን የወሰድኩት የኢስላም በሃገሪቱ በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋት እንቅልፍ የነሳው ፀሐፊ “ለንደን 500 ቤ/ክርስቲያናትን ዘግታ 423 አዳዲስ መስጂዶችን ከፈተች” በሚል ርእስ ከፃፈው አርቲክል ሲሆን በዚህ ድረ ገፅ ታገኙታላችሁ። http://yournewswire.com/london-churches-mosques/
ኢስላም ብሪታንያን እየዋጣት ነው ይላል የፅሁፉ ጭብጥ። ይህንን ለማሳየትም የተለያዩ መረጃዎችን ዘርዝሯል። ሀሳቡ ሲሰበሰብ የሚከተለውን ይመስላል:-
በሂያት ዩናይትድ ቤ/ክ በግብፃውያን ኮሚዩኒቲ ተገዝቶ መስጂድ ሆኗል። ቅዱስ ጴጥሮስ ቤ/ክ “መዲና መስጂድ” ተብሎ ተቀይሯል። ብሪክ ሌን መስጂድ ቀድሞ የሜተዲስት ቤ/ክ ነበር።
ህንፃው ያለ ምክንያት አልተቀየረም። ህዝቡም እየተቀየረ ሆኖ እንጂ። አዎ የሰለምቴዎች ቁጥር በእጥፍ አድጓል። ፀሐፊው ዴይሊ ሜይልን አጣቅሶ እንደፃፈው በለንደን እምብርት ውስጥ በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ቤ/ክ እና መስጂድ ይገኛሉ። ይሄ ምንም አይደንቅም። የሚደንቀው 1,230 ሰዎችን ለማስተናገድ የተዘጋጀው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሰኘው ቤ/ክ ውስጥ ሳምንታዊ ባእልን ለማክበር የተገኘው ክርስቲያ 12 ሰዎች ብቻ መሆናቸው ነው። በሳንታ ማሪያ ደግሞ 20 ብቻ። በአንፃሩ በአቅራቢያው የሚገኘው የብሩን ስትሬት ኢስቴት መስጂድ የገጠመው ችግር ከዚህ የተለየ ነው፣ ለሰጋጆች የሚበቃ ቦታ በማነሱ መጨናነቅ! መስጂዱ 100 ሰዎችን ብቻ የሚያስተናግድ ጠባብ ክፍል ያለው በመሆኑ ለጁሙዐ የሚታደመው ምእመን ጎዳና ላይ ሊፈስ ግድ ሲለው ይታያል። ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ክርስትና በእንግሊዝ ወደ ታሪካዊ ቅርስነት እየተቀየ ሲሄድ ኢስላም ግን የሃገሪቱ የወደፊት ሃይማኖት ይሆናል።
ይህን ግምት የሚያጠናክሩ ተጨባጭ እውነታዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ አንዱ ከሃገሪቱ ሙስሊም ማህበረሰብ ውስጥ ግማሽ (50%) አካባቢው ከ25 አመት እድሜ በታች መሆኑ ሲሆን ከክርስቲያኑ ህዝብ ደግሞ ሩቡ (25%) ከ65 አመት እድሜ በላይ ያሉ አዛውንቶች መሆናቸው ነው። ይህም ከ20 አመታት በኋላ ወደ ቤ/ክ ከሚሄዱ ክርስቲያኖች የሚልቁ ንቁ ሙስሊሞች ይኖራሉ ማለት ነው፤ የናሺናል ሴኪዩላር ሶሳይቲ ዳይሬክቴር የሆነው ከይዝ ፖርቺየስ እንደገለፀው።
በሌላ በኩል የሃገሪቱ ክርስቲያን በየጊዜው ለክርስትናው ጀርባውን እየሰጠ በመሆኑ የተነሳ የቤ/ክርስቲያናቱ ቁጥር በፍጥነት እያሽቆለቀለ ነው። ከ2001 ጀምሮ ለንደን ውስጥ ብቻ 500 ቤ/ክርስቲያናት ወደግል መኖሪያነት ተቀይረዋል። በተመሳሳይ ጊዜ በሃገሪቱ የሚገኙ መስጂዶች ቁጥር ሲታይ ግን በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ ነው ያለው።
ከ2012 እስከ 2014 ባሉት አመታት ራሳቸውን የአንግሊካን ክርስትና ተከታዮች እንደሆኑ ሲገለፁ የነበሩ እንግሊዛውያን ቁጥር ከ21% ወደ 17% በማሽቆልቀል በሶስት አመታት ውስጥ ብቻ ቤ/ክርስቲያኗ የ1.7 ሚሊዮን ተከታይ ኪሳራ ደርሶባታል። የሙስሊሙ ቁጥር ግን በአንድ ሚሊዮን አካባቢ እድገት አሳይቷል። ይሄ 5% ከማይሞላው ከሃገሪቱ የሙስሊሙ ቁጥር አንፃር ሲታይ እጅግ ከፍተኛ እድገት ነው። (ይስተዋል! በጁላይ 2015 በተካሄደው የህዝብ ቆጠራ መሰረት የእንግሊዝ ህዝብ ብዛት 64 ሚሊዮን ሲሆን የሙስሊሙ ቁጥር ከዚህ ውስጥ 4.4% ነው።) ሆኖም ግን ግምቶች እንደሚያስቀምጡት በ2020 የጀማዐ (ህብረት) ሶላት ላይ የሚገኙ ሙስሊሞች ቁጥር ቢያንስ ወደ 683ሺ ያሻቅባል ተብሎ ይጠበቃል። በአንፃሩ ሳምንታዊው በዓል ላይ የሚገኙት ክርስቲያኖች ቁጥር ወደ 679ሺ ይወርዳል ተብሎ ይገመታል።
ወደ ቤ/ክ የሚመላለሰው ህዝብ ቁጥር ወደ መስጂድ ከሚመላለሰው ሙስሊም ህዝብ ጋር ሲነፃፀር በአንድ ትውልድ ዘመን ውስጥ ብቻ ሶስት እጥፍ ያነሰ ይሆናል።
በ2015 በተደረገ ትንተና በሃገሪቱ የብዙ ሰዎች ስያሜ በመሆን ልቆ የተገኘው “ሙሐመድ” የሚለው ስም ነው። ታላላቅ የሃገሪቱ ከተሞች ከፍተኛ የሙስሊም ቁጥር አላቸው። ማንቸስተር 15.8%፣ በርሚንግሀም 21.8%፣ ብራድፎርድ 24.7%። በክርስቲያን ቤተሰብ ከሚወለደው ይልቅ በሙስሊም ቤተሰብ የሚወለደው ህፃን ቁጥርም የላቀ ነው። በብራድፎርድና በሌስተር ከከተማዎቹ ህፃናት ግማሾቹ ሙስሊሞች ናቸው። ከተወሰኑ አመታት በኋላ የከተማዎቹ ነዋሪዎችን የህዝብ ብዛት ስብጥር ይገምቱ እንግዲህ።
በሌላ በኩል ለንደን ውስጥ ብቻ ኦፊሻሊ የሚታወቁ 100 የሸሪዐ ፍርድ ቤቶች አሉ። የሃገሪቱ ህግ አንዳንድ የሸሪዐ ህጎችን እንዲያካትት በሃገሪቱ ታዋቂ የሆኑ ግለሰቦች ሳይቀሩ እየጠየቁ ነው ያሉት። የብሪታኒያ ዩኒቨርሲቲዎችም ኢስላማዊ ህግ እያስተማሩ ነው። (የኛዎቹ ያሉትንም እየዘጉ እንደሆነ ልብ ይሏል።)
በሳዑዲ ዐረቢያ የብሪታኒያ አምባሳደር የሆነው ሲሞን ኮሊስ ኢስላምን ተቀብሎ ወደ መካ በመሄድ ሐጅ አድርጓል። ጠላቶቹ የፈለገ ቢያሴሩ መጪው ዘመን የኢስላም ነው። በሃገራቸው ያለው አንፃራዊ ነፃነት ለኢስላም መስፋፋት ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነ የገባቸው ምእራባውያን በነፃ መድረኩ “ፍልሚያ” ኢስላም ልቆ እየወጣ እንደሆነ ቢረዱ ጊዜ በሙስሊሞች ላይ የነፃነት ምህዳሩን ማጥበብ፣ ሃይማኖቱን ጭራቅ አድርጎ የመሳል (islamophobia) ሰፋፊ ዘመቻዎችን መደገፍ፣ እንደ ዳዒሽ (isis) ያሉ ጠርዘኞችን በስውር መደገፍ፣ ኢስላማዊ ሃገራትን ማፈራረስና ሙስሊሞችን በገዛ ቀያቸው መጨፍጨፍ እንዲሁም ፀረ ኢስላም ፖሊሲ የሚያራምዱ አምባገነን ሃይላትን በፀረ ሽብር ዘመቻ ስም ያልተገደበ ድጋፍ ማድረግ አማራጭ ፖሊሲያቸው ሆኖ በገሃድ እየታየ ነው። “ልፋ ያለው በህልሙ ዳውላ ይሸከማል” እንዲሉ መስሏቸው እንጂ የኢስላም ግስጋሴን ምድራዊ ሃይል አይገታውም። ምክንያቱም ከላይ የተገባ መለኮታዊ ቃል አለና።
{ یُرِیدُونَ لِیُطۡفِـُٔوا۟ نُورَ ٱللَّهِ بِأَفۡوَ ٰ⁠هِهِمۡ وَٱللَّهُ مُتِمُّ نُورِهِۦ وَلَوۡ كَرِهَ ٱلۡكَـٰفِرُونَ }
“የአላህን ብርሃን በአፎቻቸው ሊያጠፉ ይሻሉ። አላህም ከሃዲዎቹ ቢጠሉም እንኳ ብርሃኑን ገላጭ ነው።” [አሶፍ፡ 8]

(ኢብኑ ሙነወር፣ ሚያዚያ 03/2010)
=
* ቴሌግራም ቻናል፡- https://t.me/IbnuMunewor
* ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/Ibnu.Munewor?mibextid=ZbWKwL
* ዋትሳፕ፦ https://whatsapp.com/channel/0029VaA3X1e5kg7BlsJboa2M