Get Mystery Box with random crypto!

ዒድ - ህግጋትና ስርአቱ ~ በኢስላም አመታዊ በአሎቻችን ሁለት ናቸው። እነሱም ዒደል ፊጥርና ዒደል | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

ዒድ - ህግጋትና ስርአቱ
~
በኢስላም አመታዊ በአሎቻችን ሁለት ናቸው። እነሱም ዒደል ፊጥርና ዒደል አድሐ። የመጀመሪያው ረመዳን እንዳለቀ በሸዋል ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ ይውላል። ሁለተኛው - ዒደል አድሐ- ደግሞ የዙልሒጃ ወር በ10ኛው ቀን ላይ። ነብዩ ﷺ መዲና ሲገቡ የመዲና ሰዎች የሚጫወቱባቸው ሁለት በአላት ነበሯቸው። “ምንድን ናቸው እነኚህ ቀናት?” ሲሉ ጠየቁ መልእክተኛው ﷺ። እነሱም “ከጃሂሊያህ ዘመን ጀምሮ የምንጫወትባቸው ቀናት ናቸው” ብለው መለሱ። ነብዩ ﷺ “አላህ ከነሱ በተሻሉ ቀናት ተክቷችኋል፡- በአድሐ ቀን እና በፊጥር ቀን” አሉ። [ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 1039]

ጥቂት ስለዒድ፡-

1. ቀኑ የደስታ ቀን ነው፡-
1.1. “ተቀበለላሁ ሚና ወሚንኩም” እያሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት መለዋወጥ ከሶሐቦች ተገኝቷል። [አልፈታዋ፡ 24/253]
1.2. ልጃገረዶች እየዘፈኑ መጫወት ይችላሉ። [ቡኻሪ፡ 949] [ሙስሊም፡ 892]
1.3. እለቱ የደስታ፣ የመብያና የመጠጫ ቀን ነው። [ሶሒሑ ቲርሚዚይ፡ 777]
1.4. ስለሆነም ቀብር ዚያራና የመሳሰሉ የእለቱን የደስታ ድባብ የሚያደፈርሱ ድርጊቶችን መፈፀም አይገባም። [አልኢብዳዕ፡ 263]
1.5. የምንደሰትበት ግን ፈፅሞ በሐራም ነገር መሆን የለበትም። “የትም ብትሆን አላህን ፍራ!” የሚለው ሐዲሥ አይረሳ።

2. ተክቢራ፡-
2.1. የሚባልበት ጊዜ፡-
* በዒደል ፊጥር - የረመዷን ወር መጨረሻ ቀን ፀሐይ ከጠለቀችበት ወይም የሸዋል ጨረቃ ከታየችበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ምክንያቱም አላህ ተክቢራውን ከረመዷን ፍፃሜ ጋር አያይዞ ነውና የገለፀው። [አልበቀረህ፡ 185] ተክቢራው እስከ ዒድ ሰላት ድረስ ይዘልቃል።
* በዒደል አድሐ - ደግሞ ከዐረፋ ቀን ፈጅር ሶላት አንስቶ እስከ ዙልሒጃ 13 ዐስር ድረስ ከግዴታ ሰላቶች በኋላ ተክቢራ ማድረጉ ከሶሐቦች ተገኝቷል። [አልኢርዋእ፡ 653] እንዲያውም ኢጅማዕ (ወጥ ስምምነት) የመጣበት ጉዳይ እንደሆነ ነወዊይና ኢብኑ ረጀብ ጠቅሰዋል። [አልመጅሙዕ፡ 5/32] [ፈትሑል ባሪ] በዒደል ፊጥር ጊዜ ከግዴታ ሶላቶች በኋላ ተክቢራ ማድረጉ በቂ ማስረጃ የለውም።
2.3. አደራረጉ፡- ሁሉም በየፊናው እንጂ አንዱ እያወጣ ሌሎች በመከተል በህብረት ባንድ ድምፅ አይባልም። [መጅሙዑፈታዋ ኢብኒ ባዝ፡ 13/21] ባይሆን ይሄ ጉዳይ በዑለማዎች የተለያየ ሀሳብ የተሰነዘረበት ፊቅሃዊ ጉዳይ እንደመሆኑ ጉዳዩን በልኩ መያዝ ይገባል።
2.4. ድምፅን በተክቢራ ከፍ ማድረግ የተወደደ ነው። [ሶሒሑል ጃሚዕ፡ 4934]
2.5. ተክቢራው ሴቶችንም በተመሳሳይ የሚመለከት ነው። [ቡኻሪና ሙስሊም] ድምፃቸውን ግን ዝቅ ሊያደርጉ እንደሚገባ ዑለማዎች ይመክራሉ።
2.5. አንዳንድ አካባቢዎች እንደሚታየው በተክቢራ ሙሉ ሌሊቱን ሳይተኙ ማሳለፍ፣ ሰፈር ጎረቤቱን በከፍተኛ ድምፅ ማወክ ማስረጃ የሌለው ስራ ነው። “የሁለቱን ዒድ ሌሊቶች ነቅቶ ያደረ ሰው ልቦች በሚሞቱበት ቀን ልቡ አይሞትም” የሚለው “ሐዲሥ” በነብዩ ﷺ ላይ የተቀጠፈ እንጂ ጤነኛ መረጃ አይደለም። [አዶዒፋህ፡ 520]
2.6. ከሶሐቦች የተለያዩ የተክቢራ አፈፃፀሞች የመጡ ሲሆን የተለየ አይነት ገደብ የለውም። ከሰሐቦች የተገኙትን መያዙ በላጭ ነው።
2.7. እነዚህን ተክቢራዎች ማለት በጀማዐ ለሰገደም፣ ብቻውን ለሰገደም የተወደደ ነው። ግዴታ ግን አይደለም። [ሸርሑል ሙምቲዕ፡ 5/165]

3. ወደ መስገጃው ቦታ መውጣት፡-
3.1. ወደ መስገጃ ቦታ ሲወጣ መታጠብን፣ ሽቶ መቀባትን የሚመለከት ከሶሐቢዩ ኢብኑ ዑመር ተገኝቷል። [አልኢርዋእ፡ 104] ከነብዩ ﷺ ግን ምንም የለም። የመታጠቢያ ጊዜውም ከእለቱ ፈጅር ሶላት መልስ ቢሆን ይመረጣል። ይህን የሚያመላክት ከሰለፎች ተገኝቷል። [አልመጣሊቡል ዓሊያህ፡ 2753]፣ [አሕካሙል ዒደይን ሊልፊርያቢይ፡ 16] ትጥበቱም ሴት ከወንድ፣ ህፃን ከአዋቂ ሳይለይ ሁሉንም እንደሚመለከት ነወዊይ ጠቁመዋል። [አልመጅሙዕ፡ 2/233]
3.2. በእለቱ አቅም በፈቀደ ባማረ ልብስ ሽክ ማለት ተወዳጅ ነው። [ቡኻሪና ሙስሊም]
3.3. ለቻለ ሰው ወደ መስገጃው ቦታ በእግር መሄዱ ሱና ነው። [አልኢርዋእ፡ 636]
3.4. የወር አበባ ላይ ያሉ ሴቶች ወደ መስገጃው ሜዳ መውጣታቸው ከሱና ነው። ከመስገጃው ቦታ ግን ገለል ይላሉ። [ቡኻሪ] ሴቶች ወደ መስገጃው ቦታ ሲወጡ ሽቶ ከመቀባትና ካላስፈላጊ አለባበስ መራቅ አለባቸው።
3.5. ስጋትና እንቅፋት ከሌለ ልጆችም ሊወጡ እንደሚችሉ የሚጠቁም ማስረጃ አለ። [ቡኻሪ፡ 977] ባይሆን ሰጋጆችን እንዳይበጠብጡ ወላጆች ሊቆጣጠሯቸው ይገባል።
3.6. ከመስገጃው ቦታ ሲመለሱ መንገድ ቀይሮ መመለሱ በላጭ ነው። [ቡኻሪ፡ 986]

4. የዒድ ሶላት፡-
4.1. ሶላቱን በተመለከተ ሚዛን የሚደፋው አቋም “ግዴታ ነው” የሚለው እንደሆነ ኢብኑ ተይሚያ፣ ሶንዓኒይ፣ ሲዲቅ ሐሰን ኻን፣ ሸውካኒይ፣ አልባኒይ፣ ኢብኑ ዑሠይሚን እና ሌሎችም አስረግጠው ተናግረዋል።
4.2. ወቅቱ፡- ፀሀይ ወጥታ የጦር ቁመት ያክል ከፍ ካለች ጀምሮ በአናት ትይዩ እስከምትሆን ድረስ ያለው ነው። የዒደል ፊጥር ሶላት ዘግየት፣ የዒደል አድሐ ደግሞ ቀደም ቢል ተመራጭ ነው። [አተልኺስ፡ 144] [ሙስነዱ ሻፊዒይ፡ 74] ምክንያቱም የዒደል ፊጥር ጊዜ ዘግየት ማለቱ ዘካተል ፊጥር ለሚሰጡ ሰዎች ጊዜ እንዲኖራቸው ሲያደርግ የዒደል አድሐ ጊዜ ቀደም ማለቱ ደግሞ ከሶላት ቶሎ ተመልሰው ኡዱሒያ የሚያርዱበት ጊዜ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል።
4.3. የሚሰገድበት ቦታ፡- ዝናብ፣ የፀጥታ ስጋት፣ ወዘተ ካልኖረ ወጣ ያለ ሰፊ ሜዳ ላይ መሆኑ ሱና ነው። [ቡኻሪይና ሙስሊም]
4.4. ለዒድ ሶላት አዛንም ኢቃማም አይደረግም። [ቡኻሪይ፡ 962] [ሙስሊም፡ 886]
4.5. የረከዐው ብዛት፡- 2 ነው። [ቡኻሪይ፡ 964] [ሙስሊም፡ 884]
4.6. የዒድ ሶላት ውስጥ ያሉት ተጨማሪ ተክቢራዎቹ ሙስተሐብ እንጂ ግዴታ አይደሉምና በመርሳትም ሆነ ሆን ተብሎ ቢቀሩ ሶላቱ አይበላሽም። [አልሙግኒ፡ 3/275]
4.7. ቁጥራቸውም የመጀመሪያው ረከዐ ላይ ከመክፈቻው ተክቢራ ውጭ 7፤ ሁለተኛው ረከዐ ላይ ደግሞ ከመነሻው ተክቢራ ውጭ 5 ተክቢራ ነው። ይሄ ከብዙሃኑ ሶሐቦችና አኢማዎች የተገኘው እንደሆነ ኢብኑ ተይሚያ ገልፀዋል። [አልፈታዋ፡ 24/220] ብዙሃኑ ዑለማዎች ያሉትም እዚህ ላይ ነው። ባይሆን የመጀመሪያውን 7 የሁለተኛውን ስድስት፣ የመጀመሪያውን 6 የሁለተኛውን 5 ማድረጉም ተገኝቷል። 4፣ 11፣ 12፣ 13 ተክቢራዎችን ማለት እንደሚቻልም ከሰለፎች ተገኝቷል። ከዚህ በመነሳት ነገሩ ሰፊ እንደሆነና በሶሒሕ ማስረጃ በመጡት ሁሉ መስራት እንደሚቻል ያሳያል ይላሉ ሸይኹል አልባኒይ ረሒመሁላህ። [አልኢርዋእ፡ 639]
4.8. በተጨማሪ የዒድ ተክቢራዎች ላይ እጅን ማንሳት ከሶሐቦች፣ ከዐጣእ፣ አውዛዒይ፣ አቡ ሐኒፋህ፣ ሻፊዒይ፣ አሕመድና ሌሎችም ተገኝቷል። ነብዩ ﷺ ደግሞ ጥቅል በሆነ መልኩ የሶላት ተክቢራዎች ላይ እጃቸውን ያነሱ እንደነበር ማስረጃ አለ። [ሶሒሕ አቢ ዳውድ፡ 715]