Get Mystery Box with random crypto!

አያ ጅቦ አለህ ? አለሁ ምን እየሰራህ ነው?.... እናንተን ልበላ እናቴ የአምስተኛ እና የስድስ | የስብዕና ልህቀት

አያ ጅቦ አለህ ? አለሁ ምን እየሰራህ ነው?....
እናንተን ልበላ

እናቴ የአምስተኛ እና የስድስተኛ ክፍል ጂኦግራፊ አስተማሪ ነበረች፤ ጡረታ ከመውጣቷ በፊት፡፡ የምታስተምርበት ትምህርት ቤት ብማርም እሷ የምታስተምርበት ክፍል አልተማርኩም። ልጆች ስለምትወድ፣ እንደ ልጆቿ ስለምትቀርባቸው እንደሚወዷት በርካታ ጊዜ ምስክርነት ሰምቻለሁ፡፡ አሁን እንኳን ጡረታ ወጥታ መንገድ ላይ ያስተማረቻቸው ተማሪዎች ፍቅር እና አክብሮታቸውን ሲገልጹላት ብዙ ጊዜ አይቻለሁ።

እናቴ የላላ፣ የተቆጠበ ማኅበራዊ ግንኙነት ያላት፣ ረጋ ያለች፣ ፈገግታ የማይለያት ደርባባ ሴት ናት። ሙሉ ጸጉሯ ሃጫ በረዶ መስሎ ጥቁር ነበረው ቢባል ለማመን ይቸግራል። ብቻዋን ነው ያሳደገችኝ፡፡

ልጅ ሳለሁ እቴቴ አባቴ የት ነው ያለው? እላታለሁ፡፡

“ይመጣል ሰላም ለማስፈን ነው የሄደው” ትለኝ ነበር!! በስንት ተረት ሰላም ምን ማለት እንደሆነ ከገባኝ በኋላ ሁከት እና ግርግር ሳይ አባቴ አልደረሰም ማለት ነው እያልኩ፣ ሲደርስ አባቴ ሁሉን ያስተካክላል እያልኩ አደግሁ።
ሲደርስ ሰላም ይሆናል።

"ትንሽ ነፍስ ሳውቅ አባቴ ጦርነት እንደሄደ፣ እናት ሀገሬ ብሎ ሸልሎ ወጥቶ አድሮ ወጥቶ መቅረቱ ተገለጸልኝ። አባቴ እንዴት ነበር? እለዋለሁ ከእኔ በዕድሜ በልጦ ተወልዶ በጥቂትም ቢሆን አባቴን የሚያውቀው ወንድሜን።

“አባታችን ተጫዋች፣ እናታችንን የሚንከባከብ፣ ደ'ሞ ደ'ሞ ከሥራ ማታ ሲመጣ ሁሌም በፌስታል ለእኛ አንድ ነገር ሳይዝ የማይመጣ፤ ከሥራ ደክሞት እንኳን መጥቶ ሳያጫውተን የማያድር ነበር” እያለ ይተርክልኛል።

በትንሹም በትልቁም አባቴ ቢኖር እላለሁ፤ ጉድለቱ ሲሰማኝ... አባት እና ልጅ ሲሄዱ የልጁ ዕድለኝነት ሲታየኝ የአባት ፍቅር ጉድለት ስሜት እየጠዘጠዘኝ፣ እኔም እንደ ማደግ ወንድሜም ለአቅመ አዳም ደረሰ።
ወንድሜ ሥልጣን ላይ ያሉትን የአባቴን ገዳዮች ለመታገል ፖለቲካን ማደሪያው አደረገ። ተቃዋሚ ነን ካሉት ጋር ሁሉ ቀድሞ ይሰለፋል፡፡ ሁሌም የተቃዋሚዎች ባንዲራ ያዥ እሱ ነው፡፡ ደፋር ነው ይሉታል።

አንድ ቀን ማታ እናቴ “ወንድሜ ቤት አላደረም” ብላ ሀገር ይያዝ አለች... ፈለገች፣ አስፈለገች... እሱን የበላ ጅብ አልጮህ አለ። ከጥቂት ቀን በኋላ ግን መታሰሩን ሰማን... እናቴ አነባች፣ ተንገበገበች! ያኔ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍቶኝ ስቅስቅ ብዬ ያለቀስኩት። ንፍጤን እና እንባዬን እየጠረግኩ አይመጣም እኮ እሱም እንደ አባዬ አይመጣም በኋላ ማንም የሚያግዝልኝ፣ ወንድሜ አይመጣም
የሚያስጠናኝ አይኖርም... እያልኩ አለቀስኩ!

በወንድሜ መታሰር ድብርት ይሆን ብቸኝነት የሆነ ውሉ የማላውቀው መንፈስ ወረረኝ። ደፋር እኮ ነው እያሉ ከፊት ሲያሰልፉት የነበሩት ሰዎች አንድ ቀን እንኳን ለመጠየቅ አልደፈሩም፡፡ የታሰረበትን የሚነግረን አጥተን ስንከራተት ያውቁ እንደሆን ስንጠይቃቸው እሱን ራሱ አናውቀውም አሉን፡፡

እናቴ የተነሳውን ርእስ ወደ ወንድሜ ስባ አምጥታ “አሄሄሄሄ ያልታደልኩ” ትላለች። በሰልኩ መሰለኝ ድሮ ስለ አባቴ እያወራችኝ ስታለቅስ፣ ሕመሟ ስለማይገባኝ ጀመራት የምል የነበርኩ ልጅ ዛሬ እኔ አለሁልሽ እያልኩ አጽናናት ጀመር።

ወንድሜ በታሰረ በሁለተኛ ወሩ እስር ቤት ውስጥ በተፈጠረ ጠብ መሞቱን ፖሊሶች ቤታችን መጥተው ሦስት መሥመር በማትሞላ ደብዳቤ አረዱን። እርማችንን ተንሰቅስቀን፣ ተንቀጥቅጠን አወጣን።

አባቴ እና ወንድሜ ሞቱ። ነገር ግን ለሞታቸው መታሰብያ የሞቱለት ጨለማን የማውደምም ሆነ ብርሃን የማፈንጠቅ ሂደት አልተከናወነም።

የቤታችን ሁለት የሙቀት ምስሶዎች ተገንድሰው ያለ ሙቀት፣ ያለ ምሰሶ እንኖራለን!
እኔ ስሜ ብርሃኑ ቢሆንም እናቴ ብርሃኔ ነው የምትለኝ፡፡ “ብርሃኔ” ስትለኝ 'ኔ' ን እርግጥ ጫን አድርጋ ስለምትጠራኝ የሆነ ማያዬ፣ እይኔ፣ ጧሪዬ የምትለኝ ነው የሚመስለኝ።

እንደ መርፌ ቀዳዳ አንድ ሆኜባት የኑሮ ፍልስፍናዋ በእኔ እና በኔ ዙሪያ ያጠነጥናል። ትንሽ ካመሸሁ ሰቀቀኗ ልክ የለውም። ሁሉም ነገር በሷ ሐሳብ ልክ ብቻ መሆን አለበት። አስራ ሁለት ሰዓት ቤት መግባት አለብኝ። አንድ ደቂቃ ካለፈ ስልኬ ይጮሃል። ቤት ገብቼ የማወራቸው ወሬዎች ከሀገር፣ ከመንግሥት፣ ከፖለቲካ የራቁ መሆን አለባቸው። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለፖለቲካ ቀረበ፣ ለሀገር መቆርቆር ስሜት ያለው ወሬ ማውራት አልችልም።

“ብርሃኔ አደራህን አታምሽ፣ በማያገባህ አትግባ፣ በፖለቲካም ቢሆን፤ ደ'ሞ ደ'ሞ ፖለቲካ ሽንፍላ ነው አይጸዳም፤ የራስ ወዳዶች መጠቀሚያ ቃታ ነው፤ የግል ችግሩን እኛ እያለ እየቸረቸረ ዝና እና ፍራንክ የሚለቅም ብቻ ነው ያለው፡፡"

ሐሳብ ከሐሳብ አይፋጭም። እኔ ልብላው፣ እኔ ካልበላሁት በሚል ይናጫሉ እንጂ ትግሉ የሐሳብ፣ ለሕዝብ ጥቅም የቆመ አይደለም፡፡ ሕዝብ ሕዝብ የሚሉት ለቲፎዞ ነው። አየህ ልጄ በፖለቲካ ጥሩ የደደበው ያሸንፍና ሥልጣን ይይዛል። ትዕቢት የወጠረው ደግሞ ይወድቃል፤ እኔ የማውቀው እና ያየሁት ፖለቲካችን ይሄ ነው፤ እንዳትበላብኝ አበባዬ።

ይሄውልህ ብርሃኔ ብሔር፣ ጎሳ፣ ዝምድና የፖለቲካችን መሠረት ነው። በእሱ ትሰባሰባለህ፣ ሴራ፣ ውሸት፣ ሆድ፣ ክሕደት፣ ድድብና አለው፡፡ ዓለሜ የታላቅነት እውነተኛ ሕልም፣ እውቀትህ ያስበላሃል። እውነተኛ ከሆንከ ያሴሩብሃል፣ ያድሙብሃል፣ ስምህን ያጠለሹታል። የማያውቅህ ወታደር ጥንካሬውን ይፈትሽብሃል ወይ ደግሞ እንዳባትህ እና ወንድምህ ግንባርህን ይልሃል።”

"ፖለቲካችን ሞት አለው፤ ካልጨከንክ፣ ካልደደብክ መከራ ይጥልብሃል፣ ያሻህን ተናግረህ አትኖርም፣ አትወጣም፣ አትገባም፣ ሚስትህን ባል አልባ፣ ልጅህን አባት ታስናፍቀዋለህ። ቂመኛ ነው ቀን ይጠብቅልሃል። እንደኔ ባል እና ልጅ እንዳንተ አባት እና ወንድም ደቼ ትበላለህ።

ብርሃኔ እኔ ልሙት እልሃለሁ ፖለቲካችን ውስብስብ አይደለም። ለመጉላት ደደብ እና ራስ ወዳድ መሆን መስፈርቱ ነው። የሚወደድ ነገር የለውም፡፡

አበባዬ የሚፈልጉትን የሚያጎሉት እና የሚያፈዙት እነርሱ ራሳቸው ናቸው። ይሄውልህ ብርሃኔ በዚህ ጸድቶ በማይጸዳ ፖለቲካ ብትሞትብኝ ለአንድ ሳምንት ብሶቴ፣ እንባዬ፣ ለቅሶዬ በየሰፈሩ በየካሜራው ይንከባለላል። ከዛ... ይረሳል፤ ሐዘኑ እና ስብራቱ እኔ ጋ ብቻ ይቀራል።


ብርሃኔ የተበላሸ ሂደት ውስጥ ትክክል መሆን ስሕትት ነው!!
ልጄ የዚህ ሀገር ፖለቲካ ይቅርብህ፤ ትበላብኛለህ። አንዲት ጣት ማጣት ለማይገባው ዓላማ ባል እና ልጄን ገብሬያለሁ። ይበቃኛል።

ዜናው፣ ትግሉ፣ ፕሮፖጋንዳው፣ ጽንፈኝነቱ ከሰውነት ማማ ላይ ያወርዳል።
አደራህን ዓለሜ ግርግር ስታይ ለማጣራትም ብለህ ቢሆን እንኳን አትገተር። አትቀላቀል፤ ፖለቲከኞች ለግል ጥቅም ነው ተናጭተው የሚያናጩት። ሕዝብ ጥቅም ማግኛ ቃታቸው ነው። ችግሩ ወደ አንተ ካልመጣ አንተ ወደ ችግሩ አትሂድ።”
ከእናቴ የተለየ ሐሳብ ባይኖረኝም ያጣችውንም ስለማውቅ ስትናገር ጣልቃ ሳልገባ እሰማታለሁ፡፡
ዛሬም አባቴን እና ወንድሜን የበሉት ጅቦች ይጮኻሉ። ፕሮፖጋንዳቸውን ይነዛሉ። አንዱ ጎራ “ተነስ ከእኔ ጋ ብርሃን፣ ሰላም፣ ብልጽግናን በጋራ እናምጣ” ሲል አንዱ ጎራ “ሁሉም ሰላም ነው ተኛ! ዋ!” ይለኛል። ሁለቱም ጎራ እያንዳንዱን ክስተት ሥልጣን ማቆያ እና ሥልጣን መጨበጫ እንድትሆን አድርገው ይቀነብቧታል። ለሁሉም ና ከእኛ ጋ ሁን ጥሪዎቻቸው መልሴ ግን አንድ ነው፡፡

ወንድሜን እና አባቴን መልሱልኝ እና!!!

መፅሀፍ- አዎ እሱጋ ያመኛል
ደራሲ - አድሀኖም ምትኩ
share& Join
@Human_Intelligence