Get Mystery Box with random crypto!

የልማድ ምስጢር! “ደጋግመን የምናደርገውን ነገር ነን፡፡ ስለሆነም፣ ልቀትና ምርጥነት የአንድ ጊዜ | የስብዕና ልህቀት

የልማድ ምስጢር!

“ደጋግመን የምናደርገውን ነገር ነን፡፡ ስለሆነም፣ ልቀትና ምርጥነት የአንድ ጊዜ ተግባር ጉዳይ ሳይሆን የልማድ ጉዳይ ነው” - Aristotle

“እኔ የአንተ የዘወትር አጋርህ ነኝ፡፡ ታላቅ የሆንኩ ረዳትህ ነኝ ወይም ደግሞ ከባድ የምባል ሸክምህ፡፡ ወደ ስኬት ልገፋህ እችላለሁ፣ ወይም ደግሞ ወደ ውድቀት ልጎትትህ ብቃት አለኝ፡፡ ሁል ጊዜ እንዳዘዝከኝ ለመሆን ዝግጁ ነኝ፡፡ በየእለቱ ከምታደርጋቸው ነገሮች ገሚሶቹን ለእኔ አሳልፈህ ብትሰጠኝ ባፋጣኝና በትክክለኛው መንገድ አከናውናቸዋለሁ፡፡ ጠንከርና ጨከን ካልክብኝ፣ በቀላሉ ልትገራኝና ልታስተዳደረኝ ትችላለሀ፡፡ አንድ ነገር በምን መልኩ መደረግ እንዳለበት አሳየኝና ትንሽ ካለማመድከኝ በኋላ በፈለከው ጊዜ ሁሉ በፍጥነት አከናውንልሃለሁ፡፡ ታላላቅ የተሰኙ ሰዎች አገልጋይ ነኝ፤ ሆኖም የውድቀትና ያለመሳካትም ምክንያት እኔው ነኝ፡፡ ታላላቅ የሆኑን ሰዎች ታላቅ ወደ መሆን ያመጣኋቸው፤ የወደቁና ያልተሳካላቸውንም ሰዎች ለዚያ ያበቃኋቸው እኔ ነኝ፡፡ ማሽን አይደለሁም፤ ነገር ግን ልክ እንደ ማሽን የተሰጠኝን ሁሉ ሳላዛባ፣ ልክ እንደሰው ደግሞ በብልህነት እሰራለሁ፡፡ ከፈለክ ለትርፍ ተጠቀምብኝ ካለዚያም ለክስረት ተጠቀምብኝ፣ በእኔ በኩል እንደሆነ ምንም ልዩነት አያመጣም፡፡ ውሰደኝ፣ የራስህ አድርገኝ፣ አሰልጥነኝ፣ ጠንከርና ጨከን በልብኝ እኔም በተራየ አለምን አስገዛልሃለሁ፡፡ ቀለል በልልኝና ችላ በለኝ፣ አጠፋሃለሁ፡፡ ማን ነኝ? እኔ ልማድ እባላለሁ!” – Anonymous

ልማድ ማለት በአንድ ነገር አቅጣጫ ራሳችንን ከማስለመዳችን የተነሳ ያንን ነገር በቀላሉ ማድረግ ስንጀምርና እንደውም ማቆም ሲሳነን ማለት ነው፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ ለጤናማውም ሆነ ለጤና ቢሱ ልማድ የሚሰራ እውነታ ነው፡፡ ልማድ ማለት ካለምንም የውጭ ግፊትና ጉትጎታ ማድረግ የጀመርነውና “የማንነታችን” ክፍል ወደ መሆን የመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ከመልካም ልማድ ውጪ ማንም ሰው ምንም ነገር ማድረግ አይችልም፡፡ በሌላ አባባል ወደ ልማድ ባልመጣ መልካም ነገር ወደ ስኬት መምጣት አንችልም፡፡

ብቃትና ጥራት ማለት የተለመደን ነገር ባልተለመደ መልኩ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ መልካምን ልማድ ማዳበር የግድ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በአንድ ስፖርት ኦሎምፒክ ላይ የሚወዳደሩ ሰዎች በአማካኝ ካለማቋረጥ ለስድስት ዓመታት ሙሉ በአመት ለ310 ቀናት፣ በየቀኑ ለአራት ሰዓታት ልምምድ ያደርጋሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች ቀኑን ሙሉ የማይሰሩትን ስራ እነዚህ ስፖርተኞች ጠዋት አንድ ሰዓት ከመሆኑ በፊት ሰርተው ይጨርሳሉ፡፡ 

አሁን ምንም አይነት የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰን ሰው ተመልከትና ጀርባውን አጥና፤ ለረጅም ጊዜ ደጋግሞ ያደረገውንና የገነባውን አንድ ነገር ታገኛለህ፡፡ በሌላ አባባል፣ አሁን የደረሰበት የላቀ ደረጃ የደረሰው በአጋጣሚ ሳይሆን አንድን መልካም ልማድ አዳብሮና በዚያ ልማድ ዙሪያ ደጋግሞ በመስራትና በመሻሻል ነው፡፡

የንጽህና ልማድ ቤትን፣ አካባቢንና አገርን በንጽህና ልቀው እንዲገኙ ያደርጋቸዋል፡፡ የስራ ልማድ በብልጽግና ልቀን እንድንገኝ ያደርገናል፡፡ የጥናት ልማድ በእውቀት እንድንልቅ መንገዱን ይጠርጋል፡፡ ከማንኛውም ውብ ነገር ጀርባ መልካም ልማድ አለ፡፡ በእኔና በአንተም ኑሮ ስሌቱ ያው ነው፡፡

አንድ ቀን ከእንቅልፋችን ስንነሳ በአንድ ነገር ልቀን አንገኝም፡፡ ከአንድ ግብ አንጻር በየእለቱ የገነባናቸው ልማዶቻችን ናቸው የነገን ልቀታችንን የሚወስኑት፡፡ ልማድ የሕወታችንን አብዛኞዎቹን (ምናልባት ሁሉንም) ነገሮች አቅጣጫ ወሳኝ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ጤንነታችንን፣ ኢኮኖሚያችንን፣ ወዳጅነታችንን የኑሮአችንን ጥራትና ሌሎችም ዋና ዋና ነገሮችን ስለሚወስን፤ ልማድ ሲጨመቅ ማንነት ይሆናል፡፡  

ዶ/ር እዮብ ማሞ
@Human_Intelligence