Get Mystery Box with random crypto!

የጠፋውን የሰው ልጅ ፍለጋ (Search for the lost human soul) ዘመኑ 1950ዎቹ | የስብዕና ልህቀት

የጠፋውን የሰው ልጅ ፍለጋ (Search for the lost human soul)

ዘመኑ 1950ዎቹ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ... ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ስካር የባነነው ዓለም ለሌላ ዓይነት ባርነት ራሱን ሲያዘጋጅ ተገኘ፡፡ ሥልጣኔውም አገዘው፡፡ የሥልጣኔ ቀዳሚው ተልዕኮ የሰውን ልጅ እንሰሳዊ ደመነፍስ ማላመድ (taming human animalistic aggresion) ቢመስልም ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ ለኤሮፓዊ ፋውስታዊ የዛገ መዳዳቱ ስምረት ቴከኖሎጂው ረዳት ሆነለት፡፡

ዘመኑ ሰው ወደ አሻንጉሊትነት የሚያደርገውን የመምዘግዘግ ጉዞ አሀዱ ያለበት ሆነ፡፡ በአዲሱ ፈጠራ ቴሌቪዥን በመታገዝ "ፖፕ ከልቸር" ሰለጠነ፡፡ ሁሉም አብረቅራቂው ዘመን አመጣሽ ሳጥን ጋር ፍቅር ወድቆ ለአዲሱ ጊዜ ባርነት ራሱን አዘጋጀ፡፡ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ቴክኖሎጂው በቀኝም በግራም እኩል ይመነደጋል፡፡ ቫይረሱ እና አንቲቫይረሱ፣ ሚሳኤሉና ጸረሚሳኤሉ እኩል ይበለጽጋሉ፡፡

ዛሬ ከሰባ ዓመታት በኋላ በዓለምአቀፍ ደረጃ ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጉ የቴሌቪዥኖች ዝግጅቶች ፣ ከ5 ቢሊዮን በላይ የሞባይል ስልኮች በሰው ልጆች እጆች ላይ ይገኛሉ። በአንጻሩ በሰው ልጆች የንባብ አትሮኖሶች ላይ እንደተዘረጉ የሚገመቱት መጻሕፍት ዓይነት ከ150 ሚሊዮን አይበልጥም፡፡

እነሆ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሞታችን ረክሶ ‹ላይቭ ስናየው ስንኳ ማስደንገጡ ቀንሷል፡፡ እንበላለን፤ ግን አናጣጥምም፡፡ እንዋሰባለን፤ ግን ፍቅርን ረስተናል፡፡ አብረን ሆነን ለብቻችንን ነን፡፡ አብረን እየኖረን አንዳችን ለሌላችን በዓድ፣ ሩቅ ነን፡፡ ወዳጅነት፣ ሣቅ፣ ፈገግታ፣ መታመን፣ ፍቅር፣ ፍትወት... ሸቀጥ ሆነው በገበያ ዋጋ ይቸበቸባሉ፡፡

ሰብዓዊት የማይቀለበስበት አስፈሪ ውጥንቅጥ ውስጥ ገብቷል፡፡ አንዳንዶች ይህ አረዳድ ጭፍንነት ሊመስላቸው ይችላል፡፡ አንዳንዶች ሀዘኑ ቤታቸው እስኪገባ ድረስ የመቃብር ደወሉ በየዕለቱ ለእነርሱ እንደሚደወል ይረሱታል፡፡

እናስ ኤሪክ ፍሮም እንዳስጠነቀቀው የሚቀጥለው ዘመን ሮቦቶች ለመሆን ምን ያክል ይቀረናል? በዚያ ዘመን (በ195oዎቹ አጋማሽ) የተነሱት እንደ ኤሪክ ፍሮም ዓይነት የሰው ልጅ ዕጣ ያስጨነቃቸው አሰላሳዮች ሰው ስለመዳረሻው እንዲጠነቀቅ አብዝተው ቢወተውቱም ሁሉም ከአጥበርባሪ ሳጥኗ ጋር ሲወዛወዝ ሰሚ አልነበራቸውም፡፡ ኤሪክ ፈሮም በ1955 እ.ኤአ በታተመ The Sane Society› በተሰኘ መጽሐፉ ላይ እንዲህ አለ፡፡

‹የ19ኛው ክፍለዘመን ጥያቄ፣ ትርክት ‹‹እግዚአብሔር ሞቷል›› ነበር፡፡ የሀያኛው ክፍለዘመን ፈተና ግን የሰው ልጅ ሞቷል› ሆነ፡፡ በ19ኛው ክፍለዘመን ኢ-ሰብዓዊነት ማለት ጭካኔ ነበር፡፡ በ20ኛው ክፍለዘመን ግን ኢሰብዓዊነት ማለት መደንዘዝ፣ ስሜት ማጣትና መነጠል ሆነ፡፡ የትናንት ስጋታችን የሰውን ልጅ ወደ ባርነት እንዳይገባ ነበር፡፡ የነገ ስጋታችን ግን የሰውን ልጅ ከሮቦትነት የመታደግ ሆኗል፡፡››

‹‹ሁላችንም በዘመናዊው የምዕራብ ዓለም የምንኖር ሰዎች እብደት ውስጥ ነን፡፡ ራሳችን እያታለልን ላለመሆናችን ምን ዋስትና አለን?››

ዓለም መልክ የሌለው መገማሸር ውስጥ ገብታለች፡፡ ልክ አንደ ሁልጊዜው!... በዚህ ሂደት ሰው የመሆናችን ቀለም አጥተናል፡፡ ሰው የመሆናችን ውሉ በምን ይረጋገጥ? ከቅድመ አያቶቻችን የሚያስተሳስረን ፈትለነገር ከተቋረጠ ሺህ ዘመናት አልፈዋል፡፡ በሕንጻ ሰንሰለቶች መካከል እየተመላለስን ስንኳ ሕልማችን የተራራ፣ የሸንተረር፣ የአደን፣ የለቀማ ነው፤ እንደ ግዞተኛ ነን፤ ፊሊፒናዊ፣ ቼካዊ፣ ቱርካዊ... መሆናችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የቅዱስ ቁርዓን፣ ወይም የማናቸውም ቅኝት ሥሪት መሆናችን እውነታውን አይቀይረውም፡፡

እኔ ግን የዓይኑ ቀለም ያላማራቸውን በጅምላ ኮንነው ሰልፊ እየተነሱ ዘቅዝቀው የሚሰቅሉ ሕዝቦች ሀገር ዜጋ ነኝ፡፡ ያ ሁሉ የሺህ ዘመናት ወንጌል፣ ሥነምግባር፣ ሀፊዝ፣ ሥርዓት፣ ትምህርት፣ ግብረገብነት በቅፅበት ውኃ በልቶት መቅላት፣ እስከነፍስ ማቃጠል፣ መደፍጠጥ፣ ማሳደድ... ሁሉም በሚያስደነግጥ ፍጥነት ሲከናወን አቅመቢስ ስዱድ፣ ዲዳ ሆኘ ተመልከቻለሁ፡፡ ታምሜያለሁ፡፡ ብዙ ኢፍትሃዊነት ባለበት ምንም ማድረግ ካለመቻል በላይ የሚያም ምንስ ነገር ይኖራል?

ለነገሩ በየትኛውም የዓለም ክፍል በሰብዓዊነት፣ በአጠቃላይ በስነፍጥረት ላይ የሚቃጣ በደል ካላመመኝ የስካሩ አካል ሆኛለሁ ማለትም አይደል? አንዳንዶች ለዚህ መድኃኒቱ ዜግነትን ማስረጽ፣ ሕገመንግስት መቀየር... ዓይነት _ ጨዋ ሐሳቦችን ሲሰነዝሩ እሰማለሁ፡፡ ምንኛ የዋሆች ሆነዋል ጃል! የታመመው በአጠቃላይ የሰው ልጅ (ሰብዓዊነት) መሆኑን ማየትስ እንዴት ይሳናቸዋል? ይህ የሰብዓዊነት ማሽቆልቆል፣ ስርዓት በመቀየር፣ ደንደሳም ዴሞክራሲ በማስረጽ፣ በአዋጅ በማስነገር፣ ኢትዮጵያን እንደ አሜሪካ በማበልጸግ ብቻ ሊሻሻል አይችልም፡፡ እንዲውም ሁላችንም ከጫፍ እስከ ጫፍ እንደ ሰው ካላሰብን አንተርፍም፡፡


ዘመናዊው የሰው ልጅ ከቅድመ አያቶቻችን አንጻር የሁሉም ነገር ውስጥ መትረፍረፍ ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ የአንድ አሜሪካዊ ቤተሰብ አማካይ የመገልገያ ቁሳቁሶች ብዛት እስከ 300,000 ይገመታል፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር 5000% እጥፍ ተመንድጓል፡፡ ዘመኑ በሁሉም ነገር የመትረፍረፍ (Abundance) ቅዠት ውስጥ የሚዳክር ይመስላል፡፡ ነገርግን መትረፍረፍ መቅሰፍት ሆኖብን ምኞታችን፣ እውነታችን፣ የሕይወት ትርጉማችን አሳክሮብናል፡፡ ምንም የማይፈይድልን የመረጃ ናዳ ያጥለቀልቀናል፡፡ በተሳከረ የመረጃ ቱማታ ተዋክበን እውነታችን ራሱ ዋጋ አጥቷል፡፡

ዘመኑ እንደየትኛውም ግልብ ዘመን ነበርና ኤሪክ ፍሮምና መሰሎቻቸው አድማጭ አላገኙም፡፡ እንደየትኛውም ዘመን... ዛሬ ለስሙ እንሰዋለን የሚሉ ቢሊዮናት ተከታዮች ያሉት መሲሁ በቁርጡ ቀን ከመስቀሉ ፊት ለፊት ለብቻው እንደነበረበት ዘመን፡፡ የሚያሳዝነው ዘመን ልብ መግዛት ሲጀምር ዕድሎች ቁጭት ሆነው ከተፍ ማለታቸው እኮ ነው፡፡

የሰው ልጅ የለየለት ዕብደት ውስጥ ገብቷል፡፡ ነጠል ብሎ ለሚታዘብ ተመልካች የሚታየው የሚሰማው  ሁሉ  አጃኢብ ነው፡፡ ሥልጣኔው ሁሉ በየዕለቱ የሚያስመዘግበው መካን፣ መራቀቅ የአውዳሚነት መሆኑ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ከጦር መሣሪያ ጋር ያልተነካካው ቴክኖሎጂያዊ ፈጠራ ስንኳ በየዕለቱ ሰብዓዊነትን የሚያኮሰምን የመሆኑ ነገር ያስደነግጣል፡፡

ተመራማሪዎች በቅርቡ ሰው በማይደርስባቸው አስፈሪ የአርክቲክ አካባቢዎች ሳይቀር ብዙ ሺህ ቶን የሚመዝን የማይበሰብስ ቆሻሻ አግኝተዋል፡፡ የሰው ልጅ አሁን በተያያዘው ግዴለሽ ጎዳና ከቀጠለ ሩቅ በማይባል ዘመን ሕይወት ከውቅያኖሶችና ባህራት ተጠቃልሎ ሊጠፋ ይችላል፡፡


በፍም እሳት መቃመስ
ያዕቆብ ብርሀኑ

ይቀጥላል
@Zephilosophy