Get Mystery Box with random crypto!

መንግስት ‘’የመንግስት ሰራተኞች እንዲደራጁ’’ የሚከለክለውን አዋጅ እንዲያሻሽል ተጠየቀ፡፡ የኢት | Housing in Addis Ababa የአዲስ አበባ ቤቶች

መንግስት ‘’የመንግስት ሰራተኞች እንዲደራጁ’’ የሚከለክለውን አዋጅ እንዲያሻሽል ተጠየቀ፡፡

የኢትየጵያ መንግስት፤ የመንግስት ሰራተኞች እንዲደራጁ አለመፍቀዱ ሰራተኞቹ ህብረት ፈጥረው መብታቸውን እንዳያስከብሩ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በአለም ስራ ድርጅት በኩል የወጣውን አለም አቀፍ ስምምነትን በሚቃረን መንገድ  በአሰሪና ሰራተኛ አዋጇ የመንግስት ሰራተኞች ተደራጅተው ስለመብታቸው እንዳይጠይቁ መከልከሏ ተነግሯል፡፡

ይህም ለወራት ደመወዝ ያልደረሳቸውን ጨምሮ፣ በከፍተኛ የገቢ ግብር እና በመሰል ችግሮች የሚንገላታው የመንግስት ሰራተኛ ተደራጅቶ እና ህብረት ፈጥሮ ስለ መብቱ  እንዳይከራከር እንዳደረገው ተጠቅሷል፡፡

ይህንን ለሸገር የነገረው የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን(ኢሰማኮ) ነው፡፡

በኢትዮጵያ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ፤ የመንግስት ሰራተኞች የመደራጀት መብት ስለሌላቸውና የማህበሩ አባል መሆን ስለማይችሉ፤ ሰራተኞቹ  ስለሚደርስባቸው የመብት ጥሰት መከራከርም ሆነ መታገል አልቻልንም ሲሉ የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዚደንት ካሳሁን ፎሎ ለሸገር አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ መንግስት ሰራተኞቹ እንዲደራጁ ይከልክል እንጂ፤ ይህንን የመንግስት ሰራተኞች እንዲደራጁ የሚፈቅደውና በዓለም ስራ ድርጅት  በኩል የተደነገገውን ስምምነት ኢትዮጵያ ፈርማለች፡፡

በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀፅ 13 መሰረት ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈረመቻቸው ሰነዶችና ስምምነቶች የሀገሪቱ ህግ አካል ሆነው እንደሚቆጠሩ ይደነግጋል፡፡

በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ የፈረመችውን ስምምነት አክብራ፤ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጇን እንድታሻሽል በየጊዜው መንግስትን እንየጠየቅን ነው ብለውናል የኢሰማኮ ፐሬዚደንት፡፡

ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት የፈረመቸው ነገር ግን የተፈፃሚ ያላደረገችው፤ ይህንን የመንግስት ሰራተኞች የመደራጀት መብትን በተመለከተ በዓለም ስራ ድርጅት በተደጋጋሚ እየተከሰሰችና እየተጠየቀች እንደሆነም  አቶ ካሳሁን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት መደራጀት የሚችሉት በግል እና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩት ብቻ ናቸው፡፡

ከአፍሪካ ሀገራት፤ የመንግስት ሰራተኞችን እንዳይደራጁ የከለከሉት ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡

https://tinyurl.com/yc3vn754

ማንያዘዋል ጌታሁን
ሸገርን ወሬዎች