Get Mystery Box with random crypto!

ከውጭ ሀገር ጉዞዬ ስመለስ አዲስ አበባ በጦርነት የፈራረሰች ይመስል ተመሰቃቅላ አገኘኋት። ከጠዋት | Housing in Addis Ababa የአዲስ አበባ ቤቶች

ከውጭ ሀገር ጉዞዬ ስመለስ አዲስ አበባ በጦርነት የፈራረሰች ይመስል ተመሰቃቅላ አገኘኋት። ከጠዋት እስከ ማታ ሸቀጥ ለመሸጥ፣ ለመግዛትና ኑሮን ለማሸነፍ በሚራወጡ ነጋዴዎች፣ ደላላዎችና ሸማቾች ፈንታ ግሬደር፣ አካፋና ዶማ የያዙ አፍራሾች ሲርመሰመሱ አየሁ።

ፈረሳው፣ መፈናቀሉና መሳደዱ ለኮሪደርና ለአረንጓዴ ልማት እንደሆነ በስፋት እየተዘገበ ነው። ከልማት ጋር ጠብ የለኝም። ጥያቄው ግን ምን ዓይነት ልማት? ማንን የሚያገለግልና ያማከለ ልማት የሚለው ነው ? ቁሳዊ ብቻ የሆነ ሰው ሰው የማይሸት ልማት ወይስ ቁሳዊና ሰብአዊነትን ያማከለ ልማት ?

እየታየ ያለው ማዋከብ፣ ማሸማቀቅ፣ መፈረጅ፣ ውጥረትና ትርምስ የሞላበት ዘመቻ "ልማቱ" ሰውንና ሰብአዊነትን ያላማከለ ሊሆን እንደሚችል በቂ ምልክት እየሰጠን ነው። አንዳንዴም "በልማት" ስም የሚካሄደው ግፍ የተሞላበትና ሰብአዊነት የጎደለው እንካ ሰላንታ፣ እድል የመንፈገና አማራጭ የማሳጣት ተግባር ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነው።

"የኮሪደር ልማቱን" ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና እሴት ከመፍጠር አኳያ ብንፈትሸው መልሳችን "ምንም" ይሆናል? "ጽዱ፣ አረንጓዴ፣ የእግረኛና የብስክሌት መጓጓዣ ያለው መንገድ ከመገንባት ውጭ መንገዱ ምርት የማያመርት፣ ምርት የማይመረትበትና ምርት የማይጓጓዝበት የከተማ ጌጥ ከመሆን አይዘልም። የእለት እንጀራውን ለሚያጣ ዜጋ "ጽዱና አረንጓዴ መንገድ" የተቀናጀና ሰብአዊ ልማት ካላመጣለት መንገዱ ብቻውን ፋይዳ አይኖረውም ?

"ልማቱ" የሚያስከትለውን ሰብአዊና ማህበራዊ ቀውስን እንመልከት። "በኮሪደር ልማቱ" ምክንያት ከ200 ሺህ ያላነሱ ነባር ይዞታዎችና ሱቆች እንደሚፈርሱ ይገመታል። ይህ ማለት ከነባር ባለ ይዞታዎቹና ከተከራይ ባለሱቆች ጋር መስተጋብር ፈጥረው የሚሰሩ ደላሎች፣ ጥበቃዎች፣ ጽዳት ሰራተኞች፣ ተቀጣሪ የምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጭዎች ሲደምሩበት ቁጥራቸው ከ500 ሺህ ሊበልጥ ይችላል። ቤተሰቦቻቸውንና ጥገኞቻቸውን ስናክልበት ደግሞ ከ1.5 ሚሊየን በላይ ሊሆኑ ይችላሉ።

"ልማቱን" ከስራ እድል ፈጠራና ከስራ እድል መክሰም አኳያ እንፈትሸው። የኮሪደር ልማቱ ከገጽታ ግንባታ ባለፈ የእነዚህን በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ለአጭር ጊዜም ሆነ ከነአካቴው ያሳጣል። ማህበራዊ መሰረታቸውን ይንዳል። ቤተሰባቸውን ይበትናል። በጥቅሉ ሕይወታቸውን ፈተና ያደርገዋል። በአጭር ጊዜ ሱቅ ፈልገው መቋቋም ስለማይችሉም ሊራቡ፣ ሊጠሙና ቤት ኪራይ የሚከፍሉት ሊያጡ ይችላሉ። በአስቸኳይ መፍትሔ እስካላገኙ ድረስ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብአዊ ቀውስ ይገጥማቸዋል።

የኮሪደር ልማቱን ከንብረት ወይም ከሀገራዊ እሴት አኳያ ስንፈትሸው ደግሞ በቢሊየን የሚቆጠር ሀብትና ንብረትን ያወድማል። ሕንጻዎች፣ ቤቶች፣ ሱቆች ዛኒጋባዎችንና መሰረተ ልማቶችን ያፈርሳል። የመንገዱ ግንባታ የሚጠይቀው አቅርቦት በቢሊየኖች የሚቆጠር ብር ስለሆነ አዲስ ፍላጎት በመቀስቀስ ወትሮውንም እጥረት የነበረባቸውን እንደ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ድንጋይ፣ ጠጠርና አሸዋ... ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ይስከተላል። እጥረቱንም ያባብሳል።

ከአቅርቦትና ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ ስንፈትሸው ደግሞ አገልግሎት ሰጭ የሆኑ ባለ ሱቆችንና ተጓዳኝ አገልጋዮችን የግብይት ስርዓት ስለሚረብሽ የተገልጋዮችንም የግብይት ስርዓት ይረብሻል። ሱቅ የፈረሰባቸው ዜጎች ምትክ አግኝተው ስራ እስኪጀምሩ ድረስ (የሱቅ ኪራይ ዋጋ በእጥፍ አድጓል፣ በቂ አቅርቦትም የለም) ሸቀጦችና ቁሳቁሶች በየመጋዘኑና በየቤቱ ስለሚታሸግባቸው ከግብይት ስርዓት ውጭ ይሆናሉ። አርቲፊሽያል የአቅርቦት እጥረት ይፈጠራል። እጥረቱንም ተከትሎ የዋጋ ንረት መከሰቱ የሚጠበቆ ነው።

እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ሁለገብ በሆነ ጥናት የተደገፉ ቢሆኑ ተፈናቃዮች ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉና መውደቂያቸውን እንዲያመቻቹ እድል ከወዲሁ ይሰጥ ነበር። ይህ ግን አልሆነም። ዘመቻው ሱሪ ባንገት ነው። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከ12 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ይዞታቸውን እንዲለቁ የተፈረደባቸው አንዳሉ እየተሰማ ነው።

ማንኛውም መጠነ ሰፊ ማፈናቀልና በጀት የሚጠይቅ ፕሮጀክት ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስን ሊታደግ በሚችል መልኩ መልታይ ዲሲፕሊነሪ በሆኑ ባለሙያዎች አማካኝነት መልታይ ዳይሜንሽናል መፍትሔ ሊቀረጽለት ይገባል። ይህ እንዳልሆነ ግን መገምገም የሚቻለው አስፈጻሚዎች መልስ ሲያጡ የሚያሳዩት ጥድፊያ፣ ትርምስ፣ ማሸማቀቅ፣ ስም መለጠፍ፣ የበላይ ትዕዛዝ ነው፣ አይመለከተኝ ማለት ወጥ አሰራር ሲሆን ነው።

ሌላው አመላካች ነገር "የልማቱ ፋይዳ" ጥያቄ ማስነሳቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መረጥነው የሚሉት መስተዳድርም ጉዳዩ የሚሊየን ነዋሪዎቹ ጉዳይ መሆኑን ተረድቶ፣ በሰከነ መንፈስ፣ በውይይት፣ አማራጭ በሚሰጥና ምትክ ፈልገው ስራቸውንና ኑሯቸውን እንዲታደጉ እድል በሚያግዝ መልኩ አለመፈጸሙ ነው።

ልማት መቼ? በማንና እንዴት? ለምን ? የሚሉ ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ ባላገኙበት፣ የሕዝብን ንቁ ተሳትፎ ባልተረጋገጠበት ተጠቃሚነቱ ባልተካተተበት ሁኔታ በግብታዊነት፣ በጥድፊያ፣ አይመለከተኝምና ትለቅ እንደሆነ ልቀቅ በሚል ቀጭን ትዕዛዝ የሚተገብር ልማት ጥያቄ ላይ መውደቁና መጠላቱ የሚጠበቅ ነው።

የተጀመረው ፕሮጀክት ምንም ያህል ተዓምር ሰሪ አቅም ቢኖረው ሰው ሰው ካልሸተተና መጨረሻው ሚሊየኖችን አፈናቅሎ፣ ቤተሰብ በትኖ፣ መድረሻ የሚያሳጣ ከሆነ ፋይዳውና ሚናው አጠያያቂ ይሆናል።

በእኔ እምነት አሁንም አልዘገየም። ልማቱ በራሱ "ጽዱ አረንጓዴና ሰፊ መንገድ" ከመስራት ባሻገር በተጓዳኝ በልማቱ ሰበብ የኑሮ መሰረታቸው የተናደባቸውና የሚፈናቀሉ ዜጎችን እንባ የሚያብስ፣ ተስፋ የሚያሰንቅ፣ የእፎይታ፣ የመደራጀትና የመቋቋም እድል የሚሰጥ ከዚህ በላይ ደግሞ ሰብእናቸውን የማይነካ፣ የማያዋክብና የማያሸማቅቅ መሆን አለበት።

ሙሼ ሰሙ