Get Mystery Box with random crypto!

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ለሽያጭ ያቀረባቸውን ቤቶች ጨረታ ማራዘሙን አስታውቋል የአዲስ አ | Housing in Addis Ababa የአዲስ አበባ ቤቶች

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ለሽያጭ ያቀረባቸውን ቤቶች ጨረታ ማራዘሙን አስታውቋል

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ጋር በመተባበር ያስገነቧቸውን 3 ሺህ 452 የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን በሽያጭ ለማስተላለፍ የጨረታ ሰነድ በመሸጥ ላይ ይገኛል።

ይኽን ተከትሎ “ከሕብረተሰቡ በመጣ ጥያቄ መነሻነት” በማለት የጨረታ መዝጊያ ጊዜው ለ10 ቀናት የተራዘመ መሆኑን ገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ ጥር 27 ቀን 2016  ጀምሮ ይፋ ባደረገው ማስታወቂያ፣ አጋጠመኝ ያለውን የፋይናንስ አቅም ችግር ለመፍታትና ተጨማሪ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ለመገንባት በማለት፣  የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ሱቆችን በጨረታ ለመሸጥ የጨረታ ሰነዶችን ሽያጭ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ለተከታታይ 20 ቀናት እንደሚያካሂድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚህም የጨረታ ማስታወቂያ ከወጣ በኃላ ለበርካታ ዓመታት ኮንደሚኒየም ቤት ለማግኘት የቆጠቡ እና እየቆጠቡ የሚገኙ ነዋሪዎችን ያስቆጣ ሲሆን የጨረታ ሂደቱ እንዲቆም ቋሚ ኮሚቴ በማቋቋም መጠየቃቸውም ይታወሳል።

በወቅቱ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የ1997 ተመዝጋቢዎች እና ቆጣቢዎች “ደሃው ህብረተሰብ ለዓመታት ከልጆቹ ጉሮሮ ነጥቆ እየቆጠበ መንግስት ቤቶችን ለጨረታ ማቅረቡ ያሳዝናል” ሲሉም ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ ግለሰቦች ለበርካታ ዓመታት የቆጠቡ እንዲሁም ሙሉ ክፍያውን የፈጸሙ ሲሆኑ አሁን መንግስት እያደረገ ያለው ነገር ለረጅም ዓመታት ተስፋ ያደረጉበትን መኖሪያ ቤት “ማግኘት የማይቻል ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር።

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን በወቅቱ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ያልሰጠበት ቢሆንም፤ በድጋሚ “ከሕብረተሰቡ በመጣ ጥያቄ መነሻነት” በማለት የጨረታ መዝጊያ ጊዜው ማራዘሙን አስታውቋል።

(አዲስ ማለዳ)