Get Mystery Box with random crypto!

የገላትያ መልእክት ማብራሪያ ክፍል /3/ የጳውሎስ በእግዚአብሔር መጠራት (1÷11-24) 1 | ሕያው ቃል

የገላትያ መልእክት ማብራሪያ ክፍል /3/

የጳውሎስ በእግዚአብሔር መጠራት (1÷11-24)

11-12 በእነዚህ በቁጥሮች ጳውሎስ እወነተኛ ሐዋርያ እንደ ሆነ ለገላትያ ሰዎች ይናገራል ። የሚሰብከው እወነተኛ ወንጌል ሲሆን ይሄንንም የተቀበለው በቀጥታ ከኢየሱስ ክርስቶስ በራዕይ ነው (ቁ 12)። ጳውሎስ ይህንን ራዕይ በመጀመሪያ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ በደማስቆ ሲገልጥለት ነው ። (የሐዋ 9÷3-5) ። የክርስቶስ ወንጌል በሰዎች የተፈጠረ ልብ ወለድ አይደለም ። ከአይሁድ እምትና ከክርስትና እምነት በስተቀር በዓለም ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሃይማኖት ከሰዎች ፍልስፍናና ሀሳብ የተወለዱ ናቸው ። የክርስቶስ ወንጌል ግን እግዚአብሔር ራሱ ያደረገው የምስራች ነው ። ሰለጠኑ እግዚአብሔርና ድህነት ሰለሚገኝበት መንገድ በቂና የመጨረሻው ፍጹም እውነት ነው ። ክርስቲያኖች በመጀመሪያ ወንጌል የተቀበል መንፈስ ቅዱስ ገልጦልን ወይም መጸሐፍ ቅዱስ አንብበን ነው ። አንዳንድ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በቀጥታ ከክርስቶስ በሆነው ትምህርት ወንጌል እንቀበላለን ። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በቀጥታ ትምህርትን ስንቀበል ከቅዱስ ቃሉ የተለየ ወይም አዲስ መልእክት አይመጣም ፥ መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የሚስማማ መልእክት ነው ያለው ። ጳውሎስ ግን ወንጌል የተቀበለው አዲስ ኪዳን ከመጻፉ በፊት በቀጥታ ከክርስቶስ ነው ። ጳውሎስ ወንጌል ከሌላ ሰው የተቀበለ ቢሆን ኖሮ ከዚያ ሰው « ያነሰ » ይሆን ነበር ማለትም « ተማሪ ሐዋርያ » ይሆን ነበር ። እርሱ እውነተኛ ሐዋርያና የሚሰብከውም ወንጌል እውነተኛ ወንጌል ነው ። ስለዚህም የገላትያ ክርስቲያኖች ይህን ሊጠራጠሩ አይገባም ። የጳውሎስ መልእክት የምናጠና እኛም አንጠራጠርም ። የክርስቶስ ወንጌል እወነተኛ ወንጌል ነው ።

(ቁ .ር 13-14) ጳውሎስ በህይወቱ የተከናወነውን ታላቅ ለውጥ ለገላትያ ክርስቲያኖች ያስታውሳቸዋል ። በመጀመሪያ እጅግ በክፉ ሁኔታ የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ያሳድድ ነበር ። ( የሐዋ 8÷3 ፣ 9÷1-2 ) የአይሁድ ሃይማኖት ይሆነውን ይሁዲነት በጥብቅና ለሃይማኖቱ በመቅናት ይከተል ነበር ። (የሐው 22÷3 ፣ ፊል 3÷4-6) በአይሁድ እምነት አንድ ሰው ሊድን የሚችለው የአይሁድ ሕግን ሲፈጸም ብቻ እንደሆነ ያስተምራል ። ጳውሎስ እንዲ ያምን ነበር ። “ አሁን ግን የጳውሎስ ዋና መልእክት ሰው በጸጋ በክርስቶስ በማመን ብቻ ይድናል የሚል ነው”። እጅግ በክፉ ሁኔታ ያስድዳቸው የነበሩት ሰዎችም የክርስቶስ ተከታይ ናቸው ። በጳውሎስ ሕይወት እንዲህ ያለውን ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው ።

(15), ጳውሎስ ከመወለዱ በፊት ሐዋርያው እንዲሆንለት እግዚአብሔር መርጦት ነበር ።እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ከመወለዳችን በፊት መርጦናል ። (መዝ 139÷-13-16) ። ይለቁን አለም ከመፈጠሩ በፊት አሰቀድሞ እግዚአብሔር መርጦናል ። (ኤፌ 1÷4 ) ። እግዚአብሔር እኛን የመረጠበት በጸጋው እንጂ እንደ ስራችን አይደለም ። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ በጸጋው የጠራኝ (1ቆር 15÷9-10) ። እግዚአብሔር የጠራን ለምን ጉዳይ ነው ? በመጀመሪያ ለድህነት ጠራን ። ሁለተኛ ከመዳናችን ጋር የእርሱ ልጆች እንድንሆን ጠራን ። (ኤፌ 1÷5) ማለትም ከክርስቶስ ጋር አብረን እንወርስ ዘንድ ጠራን (ሮሜ 8÷17)። ሦስተኛው እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀልን ሥራ ወይም ተግባር እንድንፈጽም ጠራን ። (ኤፌ 2÷10) ። የጳውሎስ የተለየ አገልግሎት ለአሕዛብ ወንጌል መስበክ ነበር ።

ቁ(ር 16) እግዚአብሔር ልጁን በእኔ ለመግለጥ ወደደ ሲል ፦ ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ጽፏል ። ክርስቶስ «ለእኛ »መገለጡ ብቻ በቂ አይደለም ። «በእኛም »መገለጥ አለበት ። የክርስቶስ መንፈስ በውስጣችን ማደር አለበት ። አለዚያ እምነታችን ደካማ ሕይወታችን መንፈሳዊ ኃይል የሌለው ይሆናል ።

(17) ጳውሎስ የሕይወቱ ለውጥ ካገኘ በኋላ ለሦስት ዓመታት እንደ ጴጥሮስና የጌታ ወንድም ከሆነው ያዕቆብ ካሉት ሐዋርያት ጋር አልተገናኘም ። ከሌላ ሰው ምንሞ ትምህርት አልተቀበለም ። እርሱ በቀጥታ ከእግዚአብሔር የተቀበለ ነው ። ከሕይወቱ ለውጥ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ዓረብ አገር ሄዶ ነበር ። ነገር ግን እዛ ምንም ያደረገው እንደነበር የሚታወቅ ነገር የለም ። ምናልባት እግዚአብሔር ለጠራው ሥራ የሚያዘጋጀው ጸሎትና የብሉይ ኪዳን መጸሐፍት በማጥናት ጊዜውን ያሳልፍ ይሆናል ። የሕይወት ለውጥ አግኝቶ በዓረብ አገር ካደረገው ቆይታ በኋላ በመጀመሪያ ደማስቆ ተመለሰ ። ከዚያም ሶስት ዓመት በደማስቆ ከቆየ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ በቁ.ር 18 ። ከዚህ የምንመለከተው ጳውሎስ የሚዘጋጅበት ጊዜ አስፈልጎት እንደ ነበር ነው ። ይህም ሁላችን የሚያስፈልግ ነው ። በአንድ ጊዜ የበሰሉ ክርስቲያኖች አንሆንም ። እግዚአብሔር እያንዳንዳችን ሊያዘጋጀን ይፈልጋል ። ይህም ደግሞ ጊዜን የሚጠይቅ ነው ። በብሉይ ኪዳን የአይሁድ ታላቅ መሪ የነበረው ሙሴ ለማዘጋጀት ዓርባ ዓመታት ወስዷል ። ሰለዚህም በቅጽበት ለአገልግሎት እንበቃለን ብለን አናስብ ። የተጠራነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው ። ለአገልግሎት የምንዘጋጀውም በእግዚአብሔር ጸጋ ነው ። እያንዳዳችን በእየለቱ ሳያቋርጠ እንዘጋጃለን ። ሁሉ በጸጋ ነው ። በእግዚአብሔር ጸጋ ከዋክብትና ዓለማትን በምህዋራቸው ይጠበቃሉ ።

በሙቀት ብዛት እንዳንቀልጥ ወይሞ በቅዝቃዜ መክንያት በረዶ እዳንሆን በመሬትና በፀሐይ መካከል ያለው ርቀት በእግዚአብሔር ጸጋ የተጠበቀ ነው ። በእግዚአብሔር ጸጋ እንተነፍሳልን ፣ እንበላለን ፤እንጠጣልን ደግሞም እንኖራልን ። እግዚአብሔር አላማውን ለመፈጸም የሰው ድካም አያስፍልገውም ። እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅሩን ለእርሱ በምናደርገው በእኛ ሥራላይ የተመሰረተ አይደለም ። ይህም የእርሱ ልጆቾ በመሆናችን ነው ። የእርሱ ልጆች የሆነው በጸጋ በኩል ነው ። ስለዚህም ወዳጆቼ ሕይወታችንን በሙሉ ክብር ለሆነው ጸጋ ለመኖር እንፈልግ ኤፌ 1÷6

(ቁር ,18) ጳውሎስ የሕይወቱ ለውጥ ካገኘ ከሶስ አመት በኋላ ከጴጥሮስ ጋር ተገናኘ ። ጳውሎስና ጴጥሮስ በሐዋርያነት ስልጣን እኩልነትን ናቸው ። ታዲያ ጳውሎስ ይህን መጻፍ ለምን አስፈለገ ? ምክንያት በገላትያ የነበሩት የጳውሎስ ተቃዋሚዎች ጴጥሮስ እወነተኛ ጳውሎስ ግን ሐሰተኛ ሐዋርያ አድርገው ይናገሩ ሰለ ነበር ነው ። ጳውሎስ ከጴጥሮስ ጋር ለመገናኘት ያደረገው ጉዞ በሐዋርያት ሥራ 9÷26-30 ላይ ተገልጧል ።( 19-20 ) በዚህ ቦታ የተጠቀሱት ሌሎች ሐዋርያት (የአስቆሮቱ ይሁዳን ሳይጨምር ) አስራ ሁለቱ የኢየሱስ ደቀመዝሙር ናቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ በተጨማሪ ሌሎች ሐዋርያት ነበሩ ከእነሱም የኢየሱስ ወንድም ያዕቆብ ይገኝበታል (1ቆሮ 15÷7) ። ጳውሎስ ይህን መልእክት ለገላትያ ክርስቲያኖች በሚጽፍበት ጊዜ ያዕቆብ በኢየሩሳሌም የነበረ «እናት ቤተ ክርስቲያን » ዋና መሪ ነበር ። (የሐዋ 21÷18 ፤ ገላ 2÷9) ። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ እንደሚለው በዚህ የጉበኝት ጊዜ ከያዕቆብ በስተቀር ከማንም ሐዋርያ ጋር አልተገናኘም

(21) ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የቆየው ለአስራ አምስት ቀናት ብቻ ነበር ።(በቁ.18) በይሁዳ ባልት ስፍራዎች ዙሪያ አልሰበከም ። ነገር ግን ይህንንም አከባቢ ትቶ ከአይሁድ ወገን ውጪ ለሆኑት ወንጌልን ለመስበክ ወደ ሶሪያ ኪልቅያና ሂዷል ።