Get Mystery Box with random crypto!

› ‹‹ግቢ ውስጥ ነኝ እኮ!›› ‹‹ና ልብስ ቀይራ መኝታ ቤት ነን!››  ወደ መኝታ ቤት ስገባ ሚ | ሀላል ትዳር👫💍


‹‹ግቢ ውስጥ ነኝ እኮ!››
‹‹ና ልብስ ቀይራ መኝታ ቤት ነን!›› 
ወደ መኝታ ቤት ስገባ ሚቾና ኢንቱዬ  ልጃችንን እያለበሱ ነበር፡፡ ሶስቱንም ስሜ ልብሴን ቀያየርኩ፡፡
ተዘገጃጅተን እንደጨረስን ሚቾ ‹‹እስኪ dad አንተን ካላየ ከዛ ክፍል አይወጣም …… please ሂድና እንደጨረስን ንገረው!›› አለችኝ፡፡ ወደ ቢሮው ሄጄ በሩን ከፈትኩትና ‹‹ክቡር አቶ በየነ ትወጣለህ ወይስ በግድ ጎትተን እናስወጣህ?›› አልኩት፡፡ እየሳቀ ከወንበሩ ላይ ተነስቶ ተከተለኝ፡፡ ማህሌት ነጭ ሙሉ ቀሚስ …… ኢንቱዬ ደግሞ ነጭ ሂጃብና ሙሉ አረንጓዴ ቀሚስ ለብሰዋል፡፡
ወደ በረንዳው ስንወጣ ሁሉም በጭብጨባ ተቀበሉን፡፡ የበየነ ጓደኞችም ከቤተሰባቸው ጋር ተገኝተዋል፡፡ ሰዉ በልቶ እንደጨረሰ የኬክ መቁረሻው ሰዓት ሲደርስ እኔና ሚቾ ልጃችን ትንሳኤን አቅፈን ወደ ኬክ መቁረሻው ቦታ ቀረብን፡፡ ኬኩ ላይ አንድ ቁጥር ሻማ ተሰክታለች፡፡ አብዱኬ አቤላን በቪዲዮ አስገብቶ ዝግጅቱን በቀጥታ እያሳየው ነው፡፡
ኬኩ እንደተቆረሰ አቶ በየነ ፀሎት አድርገው ንግግራቸውን ከፈቱ፡፡
‹‹የዛሬ አመት ጌታ ይህችን የመሰለች ቆንጅዬ ልጅ አሳቅፎናል፡፡ ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን!››
‹‹አሜን!›› የታዳሚው ድምፅ አስተጋባ፡፡
‹‹እናም ዛሬ ጌታ እኛን የባረከበት ቀን ነውና ይህን አስመልክቼ ለሁለቱ ውድ ልጆቼ የማበረክተው አንድ ስጦታ ይኖራል፡፡›› አብዱኬ ልጁን እንዳቀፈ በእጁ በስጦታ ወረቀት የተጠቀለለ ትልቅ ፍሬም አቀበላቸው፡፡ ሁሉም በአንድነት እያጨበጨበ ስጦታውን ተቀበልን፡፡
‹‹ይከፈት …… ይከፈት!›› የሚል ድምፅ ተስተጋባ፡፡
ሚቾና እኔ በአንድነት ሆነን ስጦታውን ከፈትነው፡፡ ያየነውን ማመን አልቻልንም፡፡ ‹‹ትንሳኤ ሆስፒታል›› የሚል ፅሁፍ በትልቁ ሰፍሮበታል፡፡ በዮካን አቅፈነው በደስታ አነባን፡፡
በዮካ እንዳቀፈን ‹‹እንግዲህ ሆስፒታሉ በሁለቱ ልጆቼ ስም እየተገነባ ያለ ነው፡፡ ሁለቱም የህክምና ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ቀስ በቀስ ሙሉ ለሙሉ ተረክበው ያስተዳድሩታል፡፡ ስራው ለስጋም ለነፍስም አትራፊ ነው፡፡ ጌታ ደግሞ እንዲባርክላችሁ ፀሎቴ ነው፡፡›› አለ፡፡
መሰናዶው ተጠናቆ ቤተሰብና የፌሎው ልጆች ብቻ ቀረን፡፡ ኢንቱዬ እንባ እየተናነቃት ‹‹በእናንተ ሆስፒታል ግን መታከም አቅቶት የሚሞት አይኖርም አይደል?›› አለችን፡፡ ሚቾዬ እየተፍለቀለቀች ‹‹በፍፁም!›› አለች፡፡
እንደተሰበሰብን አቤላን በቪዲዮ አስገብተነው ማውራት ጀመርን፡፡
ኢንቱ እየሳቀች ‹‹የጅማው …… እንዴት ነው ሀገሩ? ›› አለች፡፡ አቤላ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ደርሶት የህክምና ትምህርቱን እየተከታተለ ነው፡፡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እናሟላለታለን፡፡
እየሳቀ ‹‹ጅማ ቀሽትዬ ናት …… እናንተ ናፈቃችሁኝ እንጂ!›› አለ፡፡
እየተወራ በመሀል አቤላ ‹‹ሚቾ ግን ምን እግር ጥሎሽ ነበር የዛን ቀን ላይብረሪ ኢቦዬ ጋ የመጣሽው?›› አለ፡፡
‹‹እኔስ ባሌ እንደሚሆን ታውቆኝ ይሆናል፡፡ አንተ ምን ሆነህ ነበር አጠገብህ ስቀመጥ ያመናጨቅከኝ?›› ሳቀች፡፡
‹‹እኔማ የሀብታም ልጅ አጠገቤ ሲቀመጥ ይጨንቀኝ ነበር፡፡ የምሸታቸው ምናምን ይመስለኝ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ሙድ ይዘውብኝ ያውቃሉ፡፡ ለዚያ ነው፡፡››
‹‹እሱማ ትሸታለህ እኮ!›› አልኩ፡፡ ሁላችንም በአንድነት ሳቅን!
‹‹ቆይ ልምጣላችሁ ብቻ!›› ዛተብን፡፡
እየተጫወትን መሸ፡፡ ሁሉም ሄደው አብዱኬና ኢንቱ ከልጆቻቸው ጋር ቀሩ፡፡ አብዱኬ ‹‹ጋሼ እንዳይደብረው ቶሎ እንሂድ!›› ብሎ ተነሳ፡፡ ከኢንቱዬ ጋር ተያይዘው ወጡ፡፡ መኪናቸው ከበር እስኪወጣ ድረስ ሸኝተናቸው ተመለስን፡፡ የአብዱኬ እናት አልፈዋል፡፡ እነአብዱኬ ቤተል ላይ ቆንጅዬ ቪላ ቤት ተከራይተው ይኖራሉ፡፡
እኔና ሚቾ ወደ መኝታ ክፍላችን ገብተን መጫወት ጀመርን፡፡
‹‹ስሚማ ሚቾዬ ዛሬ አንዲት የክፍላችንን ልጅ ተዋውቄ ……››
‹‹አምስት አመት ሙሉ ሳትተዋወቃት ……… እሺ?››
‹‹አንቺ ታውቂያታለሽ እኮ መሰለኝ ሀፍሷ ምናምን ነው ስሟ!››
‹‹አዎ አውቃታለሁ፡፡›› ሚቾ ለመውለድ ብላ ትምህርት ስላቋረጠች ከኛ አንድ አመት ትዘግይ እንጂ አንድ ባች ነበርን፡፡
‹‹እነሱ እዚህ ቤተል ቢሮ አላቸው ………›› የነገረችኝን ሁሉ ተረክኩላት፡፡
አብረን ለመሄድ ተስማማን፡፡
ሀፍሷ ጋር ደውዬ ቅዳሜ እንደሚመቸን ነገርኳት፡፡ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ከነገረችኝ በኋላ ቢሯቸውን የማየት ፍላጎቴ ጨምሯል፡፡
ቅዳሜ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ገደማ ከሚቾዬ ጋር ትንሳኤን እንደያዝን ወደ ቤተል አደባባይ አቀናን፡፡ ሀፍሷ ቤተል አደባባዩ ጋር እየጠበቀችን ነበር፡፡ ቤተል አልመሻን ህንፃ ፓርኪንግ ውስጥ መኪናችንን አቁመን የህንፃው መግቢያ ጋር ቆማ እየጠበቀችን ወደነበረችው ሀፍሷ ሄድን፡፡ ሀፍሷ ሚቾን ስማ እኔ ትንሳኤን እንዳቀፍኩ ወደ ፎቅ መውጣት ጀመርን፡፡ ሶስተኛው ፎቅ ላይ ደርሰን ወደ ግራ ታጠፍንና በትልቁ ‹‹ኡሚ›› የሚል ፅሁፍ ወዳለበት ቢሮ ገባን፡፡ ሚቾዬ በትናንሽ የውሀ መጠጫዎች ላይ የተነቀሰውን የተቋሙን መሪ ቃል አስነበበችኝ፡፡ ‹‹ለበጎነት መስፈርት የለውም!›› ይላል፡፡ ፈገግ አልኩ፡፡ ፕሬዝዳንቱ መጥቶ በትህትና ከተዋወቀን በኋላ ስለሚሰሯቸው ስራዎች እና ስለሚደግፏቸው ቤተሰቦች ችግር በደንብ አስረዳን፡፡ በልቤ እውነትም ችግሩን ተረድተውታል ብዬ አሰብኩ፡፡ ኖሬ ስላየሁት ከማንም በላይ ችግሩን አውቀዋለሁ፡፡ ሚቾ የአባልነት ፎርም እየሞላች ሀፍሷ ወደ ሌላኛው ክፍል ወስዳ ህፃናትን በጎነት ለማለማመድ የቀረፁትን ፕሮጀክት ታሳየኝ ጀመረች፡፡ ኮምፒዩተር ከፍታ ከዚህ ቀደም የሰሯቸውን ስራዎች በፎቶ አስጎበኘችኝ፡፡
እነሚቾ ወዳሉበት ክፍል ስንመለስ ፕሬዝዳንቱ ትህትና ተላብሶ ‹‹ነገ ከቻላችሁ አንፎ ቤተሰቦችን ልናይ ስለምንሄድ ብትመጡ ደስ ይለናል፡፡›› አለ፡፡ ሚቾ ዞር ብላ ተመለከተችኝ፡፡ አንገቴን በአሉታ ወዘወዝኩ፡፡
‹‹አንፎ ምንም አያደርግህም …… ሂድና ፍርሀትህን አሸንፈው፡፡›› አፈጠጠችብኝ፡፡
ውሳኔያችንን እንደምናሳውቃቸው ተነጋግረን ተመለስን፡፡
ለሊቱን ሙሉ ልሂድ አልሂድ የሚለውን ሳስብ ቆየሁ፡፡ ፍርሀቴን የማሸንፍበት ጉልበት ፈለግኩ፡፡ ሚቾ እንድሄድ ለማድረግ የቻለችውን ያህል ጣረች፡፡ ተሳካላት፡፡ እየቀፈፈኝም ቢሆን እናትና አባቴ ወደ ሞቱበት ሰፈር ለመሄድ ተስማማሁ፡፡
.
ይቀጥላል ….