Get Mystery Box with random crypto!

ከተራራው ላይ ክፍል አስራአራት (ፉአድ ሙና) . ‹‹በፍቅርሽ እሳት፣ ባንቺው ሱባዔ፣ ጨለማው ነጋ፣ | ሀላል ትዳር👫💍

ከተራራው ላይ
ክፍል አስራአራት
(ፉአድ ሙና)
.
‹‹በፍቅርሽ እሳት፣ ባንቺው ሱባዔ፣
ጨለማው ነጋ፣ መጣ ትንሳኤ!
እሳት ያበራል?››
.
ፈገግ ስል ድፍረት አገኘች መሰል ውትወታዋን ቀጠለች፡፡ ‹‹በላ ንገረኝ!›› በጉጉት ትመለከተኛለች፡፡
ታሪኬን ዘና ለማለት እየሞከርኩ አጫወትኳት፡፡ ምናልባት ለሚሰሩት ስራ ይጠቅማቸው ይሆናል ብዬ አስቤያለሁ፡፡
ማኪያቶዋን እየማገች ‹‹ግን እኮ አሁንም ለምን ሐይማኖቱን ቀየረ የሚለውን ጥያቄ አልመለስክልኝም!›› አለች፡፡
በረዥሙ ተንፍሼ ማብራራት ጀመርኩ፡፡
‹‹እንደነገርኩሽ ሙስሊም ልባል እንጂ ስለእስልምና ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ድሀ እንደመሆኔ ልማር የምችልበት ቀላል መንገድም አልነበረም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የመከራ አይነት ያለማቋረጥ ይዘንብብን ነበር፡፡ በመከራችን ጊዜ ሁሉ ከጎናችን ሆነው ያላቸውን ያካፈሉን ደግሞ ሙስሊሞች ሳይሆኑ እነማህሌት ነበሩ፡፡››
‹‹ሚቾ የኛ ግቢዋን ነው?››
አንገቴን በአዎንታ ነቅንቄ ቀጠልኩ፡፡ ‹‹እና ከእኔ ምንም ሳይፈልጉ …… የተረጂነት መንፈስም እንዳይሰማኝ ጓደኛ ሆነው ያገዙኝ እነሱ ነበሩ፡፡ በሂደት ደግሞ ከማህሌት ጋር የነበረን ግንኙነት ወደ ፍቅር ተቀየረ፡፡ እኔ እልም ያልኩ ድሀ …… እሷ የናጠጠ ሀብታም ልጅ! ግን የኪስ ብቻ ሀብታም አልነበሩም፡፡ አባቷ እንዴት ከደሀ ጋር ተፋቀርሽ አላላትም፡፡ መሰናክል የሆነብን የሀይማኖቱ ጉዳይ ብቻ ነበር፡፡ እሷ ስለሀይማኖቷ በደንብ ታውቃለች፡፡ እኔ ደግሞ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ፍቅረኛ በሆንን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አባቷ ጠርቶ አናገረኝ፡፡ እንደልጁ እያየ የሐይማኖቱ ጉዳይ እንዳሳሰበውና ምን መፍትሔ ልናበጅለት እንደምንችል ጠየቀኝ፡፡ ምንም ሳላመነታ ሐዋርያት እሆናለሁ አልኩት፡፡ በጣም ደስ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ልጁ እንደሆንኩ ነገረኝ፡፡ ከህመምተኛ እህቴ ጋር ተቀብሎን በቤቱ እንድንኖር አደረገ፡፡››
‹‹ስለሀይማኖቱ ሚቾ የነገረችህ ነገር ነበር? አምነህበት ነው ወይስ?››
‹‹ስለሐዋርያት እንኳን ስለእስልምና ከማውቀው ያነሰ ባውቅ ነው፡፡ ሐይማኖት ያኔም ሆነ አሁን ጉዳዬ አይደለም፡፡ ያመንኩት ማህሌትን ነው፡፡ ፈጣሪ ካለ እንኳን ያለ የሚመስለኝ ማህሌት ላይ ነው፡፡ የደስታዬ …… የእረፍቴ ሁሉ ምንጭ እሷ ነበረች፡፡ እሷን ሳይ ደስታን የማይ ይመስለኛል፡፡ ተያይዘን ወደ ገሀነም እንግባ ብትለኝ እንቢ አልልም፡፡ ገሀነምን ገነት የማድረግ አቅም ያለው ደግነት እንዳላት ይሰማኛል፡፡ እንደዚያ ተርቤ በእጇ የበላሁትን አልረሳም፡፡ በየአንዳንዱ አዲስ ቀን እንደ አዲስ የማስታውሰው ጨጓራዬ ሲነድ ማህሌት ያጎረሰችኝን ጉርሻ ነው፡፡  ሙስሊሞችን ሳይ ……… በተለይ ሙስሊም ሀብታሞችን ሳይ በጣም እናደዳለሁ፡፡ እኛ ስንራብ እነሱ ከቤተሰባቸው ጋር በምቾት ሲደሰቱ ነበር፡፡ እዚያ የመከራ መሸሸጊያ ተራራ ላይ ስናነባ አንዳቸው እንኳን አለንላችሁ አላሉንም፡፡ እህቴ ሀይማኖቷን መማር ፈልጋ ገንዘብ ስለሌላት መማር አልቻለችም፡፡ አንዳንዱ በራሱ ጫማ እየለካን ስለእህቴ ቀሚስ መወጣጠር ሊወቅሰን ይፈልጋል፡፡ እሷ እኮ እሱን እንኳን በስርዓቱ ለመማር ፈልጋ ገንዘብ የላትምና አልቻለችም፡፡ እኔን ከሴት ጋር በነበረኝ ግንኙነት ሊተቹኝ ይፈልጋሉ፡፡ እኔ መጀመሪያ እምነቱን ሳውቅ ነው እኮ እንደነሱ ሊያሳስበኝ የሚችለው አይደል እንዴ? መጥፎ ነገር መፈለግ ብቻ! ስትሳሳቺ አሉ! ሲርብሽ ግን የሉም! በሰዎች ደግነት ተማርከሽ ሀይማኖትሽን ስትቀይሪ በዘይት አታለሏቸው እያሉ ያሙሻል፡፡››
እንባዋ አይኗን ሞልቶ ለመውረድ እየታገለ ሳግ ባጠረው ድምፅ ‹‹ግን እኮ ሐይማኖቱ እንደዚያ አይደለም ……›› አለች፡፡
‹‹እኔ ሐይማኖቱን ሳይሆን ሐይማኖተኞቹን ነበር ያገኘሁት! ወሬ ሳይሆን ተግባር ነው የሚታየው!››
‹‹እህትህስ? እሷስ እንዴት ሆነች?››
‹‹ህክምናዋን ተከታትላ …… አሁን ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች እናት ናት፡፡››
‹‹እሷም ሀይማኖቷን ቀየረች?››
‹‹አልቀየረችም!››
‹‹ሙስሊም ነው ያገባችው?››
‹‹አዎ!›› 
ልጅቷ እየተንሰቀሰቀች ማልቀስ ጀመረች፡፡ አቅፌ ላባብላት አልኩና ሙስሊም መሆኗ ትዝ ሲለኝ እጄን ሰበሰብኩ፡፡ እንድትረጋጋ በማሰብ ‹‹ሰፈርሽ የት ነው?›› ብዬ ጠየቅኳት፡፡
እንባዋን እየጠራረገች ‹‹አየርጤና ……›› አለች፡፡ 
ሰዓቴን ስመለከተው የትምህርት ሰዓታችን እየደረሰ ነበር፡፡ እንድንመለስ ጠየቅኳት፡፡ ሂሳብ ለመክፈል ከተጨቃጨቅን በኋላ እሷ ከፍላ ወደ መኪናዋ ተመለስን፡፡ ወደ ጥቁር አንበሳ እየነዳች ዋናውን መንገድ እንደያዝን ‹‹ከዚያ በኋላ ወደ ድሮ ሰፈርህ ሄደህ ታውቃለህ?›› አለችኝ፡፡
‹‹አላውቅም! የሰፈሩ ስም ሲጠራ ትዝ የሚለኝ ያሳለፍነው መከራ ነው፡፡ አባቴም እናቴም የሞቱበት ሰፈር ነው፡፡ ብሄድ እዚያው የምቀር …… ድጋሚ ድሀ የምሆን የምሆን ይመስለኛል፡፡  ድርሽ ብዬ አላውቅም፡፡››
‹‹በአቅምህ የድሮ ሰፈርህ ላይ የነበሩ ሰዎችን ለመርዳት አልሞከርክም?››
‹‹እኔ አልሂድ እንጂ እነማህሌት አሁንም ይሄዳሉ፡፡ ኢንቱዬም ትሄዳለች፡፡››
ልጅቷ መረበሿን ላለማሳየት እየጣረች ‹‹ድፍረት አይሁንብኝና ድጋሚ ብንገናኝ ደስ ይለኛል፡፡ እዚህ ሳይሆን እዚያው ሰፈርህ ማለት ነው፡፡ ቢሯችንን ባሳይህ …… ፕሬዝዳንታችንን ባስተዋውቅህ ደስ ይለኛል፡፡›› አለች፡፡
‹‹ችግር የለውም፡፡ ስራችሁ ተመችቶኛል ቀኑን ንገሪኝና ከሚቾ ጋር እንመጣለን፡፡››
‹‹ሲመችህ!››
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ገብተን መኪናዋን ቦታ ፈልገን ካቆምን በኋላ ወደ ክፍል ገባን፡፡ የተቀመጥነው አብረን ነበር፡፡ ትምህርቱ እንዳለቀ ተማሪው በግርምት ይመለከተን ጀመር፡፡ በፍፁም ይሆናል ብለው ያላሰቡትን ነገር ያዩ ይመስላሉ፡፡ በእርግጥ ከሙስሊም ተማሪ ጋር አብሬ ስቀመጥ የመጀመሪያዬ ነበር፡፡ ከወትሮው በተለየም ፊቴ ላይ ፈገግታ ነበር፡፡ ልጅቷ አስገድዳኝም ቢሆን ስላወራሁ ደስ ብሎኛል፡፡
‹‹ስምሽ ግን ማነው?›› አምስት አመት አብረን ተምረን ስሟን አለማወቄ አሳፍሮኛል፡፡
በግርምት እያየችኝ ‹‹የምርህን ነው? ማለቴ አታውቀውም?›› አለች፡፡
አንገቴን በአዎንታ ነቀነቅኩ፡፡ እየሳቀች ‹‹ሀፍሷ እባላለሁ፡፡›› አለችኝ፡፡
ከሀፍሷ ጋር እስከ መኪናዬ እያወራን ከሄድን በኋላ ተሰነባበትን፡፡ ከእሷ ጋር እንደተሰነባበትን ማህሌት ደወለች፡፡
‹‹ሚቾዬ የኔ ቆንጆ ……››
‹‹አብርሽዬ ማር ……››
‹‹ወዬ ምን ልታዘዝ?››
‹‹ከclass ወጣችሁ አይደል?››
‹‹አዎ አሁን መኪናዬ ውስጥ ገባሁ፡፡ እየመጣሁ ነው፡፡››
‹‹በቃ አፍጥነው ሁሉም ሰው መጥቷል አንተ ነህ የቀረኸው! One last thing ርችት ረስቻለሁ፡፡ ይዘህ ና!››
‹‹ሰምቻለሁ ክቡርነትዎ! በመቶ ሰማንያ ነው እየነዳሁ የምመጣው!››
‹‹ስርዓት ያዝ!››
ሳቅኩኝ፡፡ ተሰነባብተን ወደ ቤት መንዳት ጀመርኩ፡፡ ያዘዘችኝን ገዛዝቼ ቤት ደረስኩ፡፡ ግቢው ውስጥ ድንኳን ተጥሎ ምግቡ ሁሉ በአይነት በአይነቱ ተዘጋጅቷል፡፡ ገና ስገባ ምህረት እየሳቀች ‹‹በልጅህ ልደት ቀን እንኳን Class የማትቀጣ ጉድ!›› አለችኝ፡፡ እየሳቅኩ አቅፌያት ወደ ድንኳኑ ተጠጋሁ፡፡ የፌሎው ልጆች በሙሉ አሉ፡፡
አብዱኬ ልጁን አቅፎ እንደቆመ ‹‹እሺ አባትየው …… ለልጅህ ልደት እንኳን ቀድመህ አትገኝም አይደል? …… ምነው ግን እኔ ካልገባሁ የአስተማሪው ልብ አይመታም አልክ?›› አለኝ፡፡ የሚያምር እርሳስ ቀለም ያለው ሱፍ ለብሷል፡፡ እየሳቅኩ ተጠመጠምኩበት፡፡  ምህረት ርችቱን ተቀብላኝ ሄደች፡፡ ሁሉንም እየዞርኩ ሰላም ካልኩ በኋላ ማህሌት ደወለችልኝ፡፡
‹‹አልደረስክም እንዴ?›