Get Mystery Box with random crypto!

‍ ኢክራም ፀሀፊ ሂራ ክፍል አንድ የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ምግብ፣ውሀና መጠለያ እ | ʜᴀʟᴀʟ ꜰᴏɴǫᴀᴀ || ሀላል ፎንቃ

‍ ኢክራም
ፀሀፊ ሂራ
ክፍል አንድ

የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ምግብ፣ውሀና መጠለያ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ፍቅርም ለመኖር ያስፈልገዋል።ፍቅርን ሲያጣ በሰው ተከቦ ብቸኝነት ይሰማዋል መኖር ያስጠላዋል በአንድ ግለሰብ ፍቅር ካጣ ከሌላ ግለሰብ ዳግም የሚያገኝ አይመስለውም።ሁሉም ሰው አንድ ይመስለዋል።እኔ የደረሰኝ እጣ ፈንታ ይሄው ነው።

ሰው የመጥላት ምክንያቶቼ ዘመዶቼ ናቸው።በነሱ ምክንያት ሀሉም ሰው መጥፎ ይመስለኛል።በተለይ ሀብታሞችማ ከሰው የተፈጠሩ አይመስለኝም።

ስሜ ኢክራም ይባላል የተወለድኩት አዲስ አበባ ነው።በድህነት ተወልጄ በድህነት ነው ያደግኩት።አሁን ላይ ግን ደና ኑሮ ነው የምኖረው።እናትም አባትም የለኝም።እህትና ወንድምም እንዲሁ።በቃ በአጭሩ ብቸኛ ነኝ።መጀመርያ ጥላኝ ወደ አኼራ የሄደችው እናቴ ናት ከዛን አባቴ።ግን በመሀላቸው የረዥም አመት ልዩነት አለ።እናቴን አላስታውሳትም በህፃንነቴ ነበር የተለየችኝ።አባቴ ደግሞ በሃያ አመቴ ነው ጥሎኝ የነጎደው።
አባቴ በጣም ሲበዛ ደግ ሰው ነው።በጣም የመገርመኝ ከሚያገኘው አነስተኛ ገቢ እራሱ ከኔ የባሱ ተንቀሳቅሰው መስራት የማይችሉ ስለሚኖሩ እያለ ለተቸገረ የሚሰጠው ነገር ነበር።መስጠት የማይሰለቸው ሰውን የማይንቅ ለትንሹም ለትልቁም ክብር ያለው አባት ነበረኝ።እናቴ ከሞተች ቡሀላ እንደናትም እንደ አባትም ሁኖ አሳደገኝ።እኔን ለማሳደግ ያየው ስቃይ የበረታ ነበር።ግን ያንን ስቃይ ሲያይ ምን ልርዳህ ያለው ሰው አልነበረም።
እራሴን አስክችል ድረስ ጠዋት ት/ቤት እያደረሰኝ ከሰአት ከትምህርት ቤት አውጥቶ ስራ የሚሰራበት ቦታ እየወሰደኝ ማታ አብረን ወደ ቤት አንገባለን።ራሴን በደንብ ካወቅኩ ቡሀላ ግን እኔ ተማሪና የቤት እመቤት አባቴ ደግሞ የቤት አባወራ ሁነን መኖር ጀመርን።
አባቴ ለትምህርቴ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጥ እንድቀልድ አይፈልግም።እኔም ተምሬ የሱን ህልም ለማሳካት እጥራለው።ያው ለወጉ የቤት እመቤት ነኝ አልኳችሁ እንጂ የኔ ስራ ቤት ማፅዳት ብቻ ነው ሌላውን አባቴ ነው የሚሰራው።

የምንተዳደረው አባቴ ድንጋይ ተሸክሞ በሚያመጣው ገንዘብ ነው።እሱን ስራ እራሱ የማያገኝበት ግዜ ይኖራል።ምግብ ከቤታችን ማይኖርባቸው ግዜያቶችም በርካታ ነበሩ።እኔ በጣም ጌታዬን አማርር ነበር አባቴ ግን ᐸᐸሁሉም ነገር ለኸይር ነው ጨለማው የፈለገውን ያክል ድቅድቅ ቢሆንም መንጋቱ ግን አይቀርም ይሄ የተፈጥሮ ህግ ነው።ጌታሽን ማማረር የለብሽም እሱ አንቺን ሲፈጥርሽ በምክንያት ነው።ደግሞ በድሎት ዱንያ ላይ እንድትኖሪ ሳይሆን እሱን እንድትገዢው ነው የፈጠረሽ።አንቺ እሱን በብቸኝነት ተገዝተሽ የጎደለሽን ለምኝው።እሱ ደግሞ ላንቺ የመረጠልሽን ይሰጥሻል >>ይለኛል ለኔ መንገር ብቻ ሳይሆን ለራሱም የሚያደርገው ነገር ነው።
በዚህ መልኩ እየኖርን ህይወት መልኳን መቀየር ጀመረች።አባቴ ብር ማግኘት ጀመረ።መጀመርያም የምንኖረው በራሳችን ቤት ነበር።በምን ገዛችሁት ድሀ አልነበራችሁ ትሉ ይሆናል።የአባቴ እናት ለአባቴ ያወረሱት ቤት ነው።አባቴ የተወለደው እዚሁ አዲስ አበባ ነው።እናም የቤት ኪራይ የለብንም።እኔም የምማረው አከባቢያችን በሚገኘው የመንግስት ት/ቤት ስለሆነ ምንም አይነት ወጪ አላስወጣም።እናም በዚህ ምክንያት አባቴ የተወሰነ ብር ማጠራቀም ቻለ።ብሩ በደንብ ሲጠራቀም የወንዶች ቡቲክ ነበር የከፈተው።በስራውም ውጤታማ ሆነ።ይህ ስራ ከብዙ ሰዎች ጋር አገናኘው።እና ስራውን ለማሳደግ ወደ ዱባይ እየሄደ የወንድም የሴትም ልብሶችን ማምጣት ጀመረ።እንዲህ እንዲህ እያለ ዱንያ ቤታችንን አንኳኳች።አባቴ በሩን ቢከፍትላትም ግን እስከነ ሸሯ እንድትገባ አልፈቀደላትም።ሸሯን ወደ ውጪ አሽቀንጥራ ጥሩ ነገሯን ይዛ እንድትገባ አደረጋት።ቤታችን ከጭቃ ቤት ወደ ዘመናዊ ቪላ ቤት ተቀየረች።እኔ ከመንግስት ትምህርት ቤት ወደ ግል ት/ቤት ተሸጋገርኩ።አባቴ ከባስ ወደ ቤት መኪና ተሸጋገረ።ግን አሁንም የተቸገረን መርዳቱን አልዘነጋውም።ረዥሙን የእረፍት ሰአቱን የቲሞችንና ሚስኪኖችን በመዘየር ነው የሚያሳልፈው።አላህ በነሱ ሰበብ ይህንን ሀብት እንደሰጠው ያምናል።ግቢያችን ውስጥ ተጨማሪ ሰርቪሶች አሉ።አባቴ እንደ መጋዘን ነው የሚጠቀምባቸው።
አባቴ ኸይር ስራው በዚህ አያበቃም።በየመስጂዱ እየዞረ ምንጣፍ የሚያስፈልገው ከሆነ ሲገዛ።ሽንት ቤት ከሌለው ሲያሰራ መታደስ የሚያስፈልገው ከሆነ ሲያሳድስ ይህንን ሲያደርግ ሀብቱም ይጨምር ነበር።በዚህ ግዜ አይንህን ላፈር ያሉት ዘመዶቹ ወደሱ ይጎርፉ ጀመር።አይ ሰው ይሄ ሁሉ አመት ይሙት ይኑር የማያውቁ ሰዎች ዛሬ ህይወቱ ሲያምር ሊያሽቃብጡ ይመጣሉ።አባቴም ምንም ሳይል የወንድምነት የዘመድነት ቦታቸውን ሳይነግፍቸው በፍቅር ተቀበላቸው።ቅርበታቸውን እያበዙት ሲመጡ እንዲህ ይሉት ጀመር።
ᐸᐸአንተ እኮ በዚህ ግዜ ማግባት ይኖርብሀል።ምክንያቱም ከስራ ደክመህ ስትመጣ ቤቱን አሟሙቃ የምትጠብቅህ ለልጅህም እናት የምትሆን ሴት ታስፈልግሃለች።እንዲሁም ይሄንን ሀብት የሚጠብቅ ወንድ ልጅ ያስፈልግሃል>>
ሲሉት አባቴ እንዲህ በማለት ያከሽፍባቸው ነበር።

"""""ክፍል ሁለት ይቀጥላል"""""
«ቶሎ እንዲቀጥል ጫን አርጓት»

ይቀላቀሉን ይቀላቀሉን

@Halal_Fonqaa @Halal_Fonqaa