2022-11-01 20:03:55
በክርስቶስ የቤዝዎት ሞት የቀድሞ ጠላቶች ሁሉ ታርቀዋል፤ የክፍፍል ግድግዳ ፈርሷል። በክርስቶስ አካል ውስጥ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ፣ ወንድ ወይም ሴት የሚል ክፍፍል የለም። ከመስቀሉ ሥራ የተነሣ የክርስቶስ ማኅበረሰብ መታወቂያውም ሆነ ውቅሩ ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ መደብ ወይም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም አይደለም። እነዚህ መለያዎች በሙሉ አንጻራዊ ሆነዋል። ገዢው ፋይዳ እግዚአብሔር በልጁ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በፈጸመው ፍጹም የዕርቅ ሥራ የተገኘው ማንነት ነው። በእርሱና በሰው፣ በሰውና በሰው እንዲሁም በሰውና በተፈጥሮ መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ ለአንዴና ለዘላላም በማፈረስ አንድ አዲስ ሰው ፈጥሯል። “. . . ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል (የማይታረቅ ጠላትነት) ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና” (ኤፌ. 2÷14-15)። አይሁድ፣ አሕዛብ፣ ወንድና ሴት፣ ባርያና ጨዋ አንድ ሆነዋል።
ልዩነት የለም - በምድር ላይ ካሉ ማኅበረሰቦች ሁሉ፣ የክርስቶስን ማኅበረሰብ ልዩ የሚያደርገው ይኸው በመስቀሉ ሥራ ብቻ የተገኘው ማንነት፣ ሰላምና አንድነት ነው። ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ሆኗል! “ከቅዱሳን ጋር የአንድ አገር ዜጋ፣ የእግዚአብሔርም ቤተሰብ አባል” የሆነው በክርስቶስ መስቀል ቤዛዊ ሥራ ነው። ይህ እግዚአብሔራዊ ቤተ ሰብነት፣ በየትኛውም መልኩ ወደ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጐራ የማይወርድ ነው።
በበዓለ አምሳ ቀን ከልዩ ልዩ ባህል፣ ነገድና ቋንቋ፣ የተሰበሰበውን ሕዝብ አንድ ያደረገው የሮም ፓለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ወይም ይሁዲነትን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩ ሃይማኖቶች፣ ባህሎችና ማኅበራዊ ዕሴቶች አልነበሩም። መንፈስ ቅዱስ ነበር። የአዲሱ ማኅበረሰብ ገዢው መለያ ከክርስቶስ ዋጆአዊ ሥራ የተነሣ የተገኘው ማንነት ነበር። ሌሎች ምድራዊ የማንነት ልዩነቶች ሁሉ የመለያየት ግድግዳ መሆናው አብቅቷል። ስለዚህ የክርስቶስ ማኅበረሰብ ውበቱ ልዩነቱ ነው። ለእግዚአብሔር ለራሱ የተለየ ሕዝብ በሆነበት ልክ ያህል ብቻ ነው ለሌላው ሕዝብ የዕርቅና ሰላም አማራጭ የሚሆነው።
“አራቱም ሕያዋን ፍጡራን እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት ክንፎች ነበሯቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸው በዐይኖች የተሞሉ ነበሩ፤ ቀንና ሌሊትም፦ 'ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የነበረው፣ ያለውና የሚመጣው፤ ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ' ማለትን አያቋርጡም። 'ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና።'” ( ራእይ 4 : 8 , 11)
“እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ 'መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል። በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ዘመሩ፤ 'የታረደው በግ ኀይልና ባለጠግነት፣ ጥበብና ብርታት፣ ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣ ሊቀበል ይገባዋል።'”
(ራእይ 5 : 9 , 12 )
በርግጥ ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከሆንን፣ የሚገዛንም ዋናው ፋይዳ ደግሞ ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ የተዋጀንበት ማንነት ከሆነ፣ እርስ በእርስም ሆነ ሌሎችን በብሔርተኝነት መነጽር ልንመለከት አንችልም። ከፍ ሲል ያሉትን ሦስት መዝሙሮች (ለነበረው፣ ላለውና ለሚመጣው፤ ሁሉን ለፈጠረው እንዲሁም ፍጥረትን በደሙ ለዋጀው ክርስቶስ የቀረቡ) የአምልኮው መካከል ያደረገ ክርስትናና ዘረኝት አብረው አይሄዱም።
(ተሐድሶ ይሁንልን! አሜን)
__ግርማ በቀለ (ዶ/ር)
@Gospel_of_God @Gospel_of_God
@Gospel_of_God @Gospel_of_God
1.1K views17:03