Get Mystery Box with random crypto!

#አሟሟት አወዳደቅ አይነት አለው ፈርጅ፣ የብርዝ አወቃቀር እንደሆነው ጠጅ። ያኔ ገና አንቺ ላይ | ግጥምና ሙዚቃ በፌሊኖቫ🖊🎹

#አሟሟት
አወዳደቅ አይነት አለው ፈርጅ፣
የብርዝ አወቃቀር እንደሆነው ጠጅ።
ያኔ ገና አንቺ ላይ ሲጥለኝ፣
አሰባበሬን ፈራሁት እንዳይገነጥለኝ።
ማልቀስ አምሮኝ ነበር ከዛፍ እንደተፈጠፈጠ፣
ግን ዋጥኩት አይቻልም ብዬ ካልተጋፈጠ።
የሰው አጥር አናት ቆመው፣
ከግንብ ከተንሸራተቱ ቀድመው።
መች ያሽና የዘንድሮ ወጌሻ፣
ዘዴ አለኝ ብሎ ለቅምሻ።
ቢቋምጥ ገረመኝ ለምላሴ እጥፋት፣
ወደሱ መምጣቴ እኮ ነው የኔ ጥፋት።
እንደው ስራመድ ስሬ ዞሮ፣
ጓዴ ቢያመጣኝ እንዲመልሱት አብሮ።
እንኳን ሊያሽለኝ አለብኝ ባስ፣
እንዴት ልድረስ አንቺ ጋርስ።
አካሄዴም መርገጥ እዚና እዛ፣
በቆሎ ብላ አትበይኝ የጠነዛ።
አይደለም እሸት ወዳጄ እሸቱም አልበጀ፣
የዚ ዘመን በሽታ ካላንገላጀጀ፣
ይተው መስሎሻል አፍልቶ ዝንጅብል፣
በሻይ አይፈታም የፋሻ ጥቅልል።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ማቀፍና መጭመቅ የተምታታብሽ ፍጡር፣
አድኜ ብሸክፍልሽ የሚጋጥ ከዱር።
ከነፈረው አንጀቴ ዘለሽ ብትጠመጠሚ፣
ቁጢጥ እንዳልኩ ቀረሁልሽ አይ አጋጣሚ።
ያሳርራልና የኩሽናሽ መጥበሻ፣
መክደኛ ስሪለት አፉን ማልበሻ።
እንጨቱ ቤትሽ ጭቃ ተመረገ፣
ምናለ ትያለሽ ለውርጭ ካልዳረገ።
ባይጠፋም ከመደብሽ ቁርበት ለመተኛ፣
በጎችሽ አለቁ በአጎዛሽ መሸኛ።
ሴት አደረገሽ እንጂ አቤት ስትበልቺ፣
ቆዳ በሳው ብለሽ መቆራረጥ አትሰልቺ።
አትከፊ ከበሮ ይወጠራል ተልጎ፣
ማን ይደክማል ጀሪካን ፈልጎ።
የሠረጋችን ለታ ደብዳቢው እጁ ጉዱ ፈላ፣
እስክስታ ለሚያስወርድ ዘፈን ካላደላ።
እጮኛ አያገኝም ካልማረካት ምቱ፣
ይሻለዋል በቃ በሽምደዳ መሰንበቱ።
ከጭፈራው ቦታ ካልገባ አጥንቶ፣
ፍቅሩን አይወስድም ከልቧ አፅንቶ።
በእንጋጠም ምክንያት ይዞ ካላሽኮረመመ፣
ለጥየቃ ጉብኝት የውሸት ካልታመመ።
ከሰማይ አትወርድም ከምድር አትበቅልም፣
ካልቀለበ ቶሎ የአይኖቿን ስልምልም።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ከድግሱ መልስ ቀርቻለሁ ከአልጋ፣
ወረተኛው መውደዷ ከኔ ባይጠጋ።
አሁንስ ልፀልይ አሟሟቴን አሳምረው፣
በፍቅሯ ህመም ውስጤን አትወግረው።
ጥሎሽ ካልተሰጠ ሚስት ትነጠቃለች፣
ሰማንያዋ ፈርሶ የራስነት ታበቃለች።
ያስተናገደሽ ጎጀዬ አስለትሞ ቆርቆሮ፣
በእርግቦች መናቆር ሆንኩልሽ ደንቆሮ።
ምነው አምላኬ ከምትገለኝ በኦና፣
እሷን ባታስለምደኝ ያኔ ገና።
መዘባበቻ መጠቋቆሚያ መደምደሚያ ፍፃሜዬ፣
ማፍቀሬ ነበር ወይ ብልሹ ስራዬ።
እስኪብርቶው ሳይከደን ፊርማችን ሳይደርቅ፣
የትዳራችን መንኮታኮት ከድጋፉ ማለቅ።
ምን ሚሉት ጨዋታ ምን ሚሉት ቅዠት፣
በፈሰሰ ኃይል መዶል ውሸት።
አሁንስ ልፀልይ ጣሬን አታብዛው፣
በማፍቀር ስቃይ ሀዘኔን አትግዛው።
ምትፈታተን ህይወት እስከመጨረሻ ህቅታ፣
ኩርኩም የምትጨምር ከእንቅልፍ አንቅታ።
የለም ቃሏ ከፍራሽህ ስትባንን፣
የምታበረታታ እርኩስ ግለኝነትን።
አትፍረጂብኝ ፍቅርሽ ነው ሚያፈላስመኝ፣
በመጫር ውስጥ ከጭነት ሚከተኝ።
በብዕር ዝምታ እንደእብድ አስለፍልፎ፣
ድምፄን የሚያራግፍ ከጥሞናዬ አልፎ።
አወዳደቄ ያላመረ አሟሟቴ አይሰምርም፣
ካልመጣሽ አሰባበሬ መወላለቅ መሆኑ አይቀርም።
#መኮንን_ዮሴፍ