Get Mystery Box with random crypto!

አለህ! ከመቀመጥ መነሳቱን ከመጠንከር መሳሳቱን ከሆንኩበት እንዳልገኝ ስውር ጥፍት የሚያደርገኝ አ | ግጥም እና ጥበብ

አለህ!

ከመቀመጥ መነሳቱን
ከመጠንከር መሳሳቱን
ከሆንኩበት እንዳልገኝ
ስውር ጥፍት የሚያደርገኝ
አለህ አስማት አለህ አዚም!

እንጃ ብቻ እንጃ እንጃ
የአንተን አስማት የ'ኔን ፍርጃ
ከደቆሰኝ የእብሪት ስሜት
ከልገኝም ባይነቴ
ካንተነትህ ስፍር ቀለም
ሲጠለስም እኔነቴ
ምን ይባላል አሁን ይሄ
አስማት ብሎ ከመሰየም?

ከንጣትህ የ'ኔ ፅልመት
ከብርታትህ የ'ኔ ድክመት
ቅይጥ ሆኖ ቢያብረቀርቅ
ቅኔ ቢሆንም
አጣሁለት ሰምናወርቅ
ልኬ ፈርሶ ልክ አጥቼ
ልክ ላገኝ ልኬን ሳጣ
ፈቅታዬን ከአካልህ ሳሳርፈው
ወዛም ፊቴ ከገረጣ
ከሄድኩበት የጉዞ ዕትም
እግሬ ቢገኝ ከእግርህ የትም
ምን ይባላል አሁን ይሄ
አዚም ብሎ ከመሰየም?

ምድረ ወንድ አዳም ተባይ ስፍሩ ሰው
ህቡዕ ሆኖ
ጣዕም ጠረኑን ያልቀመሰው
የ'ኔን ጣራ የዕድፌን ዳር
ማን ሸለመህ
ከልቤ ጋርውሎን ማደር?
አንተ ሆዬ በየት በኩል
የጠራረክ የነፍሴን ኩል
ጋን ኩራቴን
በንኬሉ ጨልፈህ የደፋህ
ለመሆኑ ማን ነኝ ባይነህ
ጨረር ገፄን ደርሰህ ያጠፋህ?

ቢኖር እንጂ×፪
አንድ መንፈስ የሆነ አካል
ብኩን ህልሜ
በእንቅልፍህ መች ይለካል
ከሸበተ ነጭ ካወጣ ከልቤ ቅል
ፍቅር የሚሉት ለጋ ነገር ቢበቃቅል
ግርም አለኝ ግ ር ም!
ለነገሩ……እንዴት አይደንቅ አያነቃን
ልብስ ጌጡ ለገላ ዕርቃን¡

[ረድኤት ሰኢድ መሀመድ]