Get Mystery Box with random crypto!

† “ሃላኻህ”አዊ ሕይወት † “ሃላኻህ” የሚል የዕብራይስጥ ቃል አለ፡፡ ትርጓሜውም አኗኗር፣ አካሔ | ገብረ እግዚአብሔር ኪደ

† “ሃላኻህ”አዊ ሕይወት †

“ሃላኻህ” የሚል የዕብራይስጥ ቃል አለ፡፡ ትርጓሜውም አኗኗር፣ አካሔድ፣ ምልልስ ማለት ነው፡፡ የይሁዲ እምነት ከምንም በላይ “ሃላኻህ”አዊ ነው፡፡ ማለትም፥ አንድ የይሁዲ እምነት ተከታይ በአበላሉ፣ በአለባበሱ፣ ቀዳሚት ሰንበትን በሚያሳልፍበት አኳኋን ይለያል፡፡ አንድ ሰው ወደ ይሁዲ እምነት ገባ ማለት በሕይወት ምልልሱ በጠቅላላ እስከ ዘለቄታው ይለወጣል ማለት ነው፡፡ ከላይ በገለፅናቸው አኳኋኖች ራሱን እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ይገልፃል፡፡ በቀን አራት ጊዜ መጸለይ፣ እምነቱን ለልጆቹ ማስተማር ግዴታው ነው፡፡ አንድ አይሁዳዊ ቤተሰብ አይሁዳዊ ኾኖ ለመቆየት በዚህ መንገድ መመላለስ ግዴታው ነው፡፡

እኛም እንደ ኦርቶዶክሳውያን ይህ “ሃላኻህ”አዊ ሕይወት እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ በተለይም እንደ ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ ራሱን በቻለ አኗኗር፣ ራሱን በቻለ አካሔድ፣ ራሱን በቻለ ምልልስ የሚገለፅ ሕይወት እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡

ርግጥ ነው፥ ስለ ብዙና ስለ ልዩ ልዩ ምክንያት ይህንን ቸለል ብለነዋል፡፡ ኦርቶዶክሳዊ እምነታችንን መሬት ላይ ማውረድ የምንችለው ግን በዚህ በቤተሰባዊ ሕይወት፣ አኗኗርና ምልልስ ነው፡፡ ለአንድ ቀን፣ ወይም ለአንድ ሳምንት፣ ወይም ለአንድ ወር በሞቅታ በመለወጥ አይደለም፡፡ ግጻዌውን በተከተለ መንገድ ከዓመት እስከ ዓመት ብሎም እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ በሚዘልቅ ለውጥ እንጂ፡፡

እንደ ቤተሰብ መጸለይ ብሎም ማስቀደስ፣ እንደ ቤተሰብ ከምሥጢራት መሳተፍ (መቊረብ)፣ እንደ ቤተሰብ ቃለ እግዚአብሔርን ማድመጥ፣ እንደ ቤተሰብ መጾም፣ እንደ ቤተሰብ መመጽወትና የመሳሰሉት ኹሉ የሥነ ምግባር ሰዎች እንድንኾን ሳይኾን ክርስቶሳውያን - ክርስቶስን እንድንለብሰው - ያደርገናልና ይህ እንዲኖረን ያስፈልጋል፡፡ “ሃላኻህ” እያልነው ያለነው ይህን ነውና፡፡

ከቤተሰብ አባላት ለምሳሌ ልጆቻችን ነገረ መለኮትን አይረዱም፡፡ በመድረክ ላይ የሚሰጠውን ጥልቅ ትምህርት አይገነዘቡትም፡፡ እግዚአብሔር ማን እንደ ኾነና እንዴት እንደሚመለክ፣ ቅዱሳን እነማን እንደ ኾኑና እንዴት እንደሚከበሩ፣ ክርስቲያን ማለት ምን እንደ ኾነና እንዴት መኖር እንደሚገባው በቀላሉ የሚረዱት በዚህ “ሃላኻህ”አዊ ሕይወት ነው፡፡ ከመብላታችን በፊት ስንጸልይ፣ በልተን ስንጨርስ ስብሐት ስንል - እምነታቸውን ይማሩታል - የእነርሱ መድረክ ይህ ነው፡፡ ይማሩታል ብቻ ሳይኾን በተግባር መኖር ይለማመዱበታል - “ሃላኻህ”አዊ ሕይወት!

እናስ? እናማ ቤታችን እንዲሁ ተሰብስበን የምንኖርበት ብቻ እንዳይኾን እምነታችንን ወደ መሬት ማውረድ የምንችልበት ዓውድን መፍጠር እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ስናደርግም እግዚአብሔር እንዲሁ ምናባዊና ሩቅ ሳይኾን ከእኛ በላይ ለእኛ ቅርብ የኾነ አምላክን እናደርገዋለን፡፡ ባልና ሚስት፣ ወላጆችና ልጆች በዚህ መንገድ ስንኖር ቤታችን መንፈሳዊ በዓት ይኾናል፡፡ በቤታችን ውስጥ ቃል ሥጋ ይኾናል፡፡ ዕርቅ ይደረጋል፡፡ ፍቅር ይጸናል፡፡ ድኅነት ይደረጋል፡፡

ገብረ እግዚአብሔር ኪደ
ጥር 13 – 2015 ዓ.ም.
-------
ሼር ብታደርጉት ደግሞ ብዙ ሰው ሊያተርፍ ይችላል!
------