Get Mystery Box with random crypto!

እግዚአብሔር በዙፋኑ አለን? በህይወታችን ብዙ ልክ ያልሆኑ ነገሮች ተፈጥረው ይሆናል። የተፈጠርነው | ፍኖተ ~ ጽድቅ

እግዚአብሔር በዙፋኑ አለን?

በህይወታችን ብዙ ልክ ያልሆኑ ነገሮች ተፈጥረው ይሆናል። የተፈጠርነው ለመከራ እስኪመስለን ህይወታችን ጥዕም አልባ ሆኖብን ይሆናል። ምድር ከሰማይ ጋር ተደበላልቆብን ይሆናል። አንዳንዴ ደግሞ በመከራችን ውስጥ ሆነን እግዚአብሔርን እንፈትነዋለን። የመከራችን ብዛት አፋችን እግዚአብሔርማ በዙፋኑ የለም እንድንል በሮችን ይከፍትልን ይሆናል። ብዙ ሰዎች ገጥመውኝ ያውቃሉ በልጆቻቸው ላይ የሚደርሰው መከራ የእግዚአብሔርን መኖር ያጠራጠራቸው፤ በህይወታቸው የተከሰተው ፈተና በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን ተስፋ ያሟጠጠባቸው፤ ለክፉዎች ሲሳካ፣ ለተንኮለኞች ሲሰምር፣ ለሌቦች ሲደላደል፣ አመጸኞች ከፍ ሲሉ፣ ተሳዳቢዎች መሪ ሲሆኑ ሲያዩ አንዳንድ ሰዎች አንተማ የለህም የለህማ ሲሉት ይሰማሉ።

ሰዎች ከደረሰባቸው ነገር የተነሳ እግዚአብሔር የለም ሲሉ ከመስማት በላይ ልብን ዝቅ የሚያደርግ ነገር አይኖርም። የሌለውን እንዲኖር ያደረገ የለም ሲባል መስማት በእጅጉ ለጆሮ ይፈትናል። የመከራችን ብዛት የእግዚአብሔር መኖር መወሰን ከጀመረ እጅግ ሰነባብቷል። ስለተፈተንን የለም እግዚአብሔር ያልንበት ችግር ስለተፈራረቀብን እምነታችን የሻከረብን ብዙዎች ነን። አንድ ነገር ግን ማስተዋል አለብን በኑሯአቸው ብዙ የተሳካላቸው፣ ቅንጦት ምቾት የነሳቸው፣ ገንዘባቸው ደስታ የሚሰጣቸው፣ ዝናቸው ክብር ይሆነላቸው፣ ምድር አላኝ የምትለውን ሁሉ የራሳቸው መድረግ የሚቀላቸው፣ ሰው እንዲኖረው የሚመኘውን ሁሉ ያላቸው ነገር ግን ትልቁን እግዚአብሔር በህይወታቸው የሌላቸው ብዙ ያለቸው ግን ምንም የሌላቸው ምስኪን ፍጥረታት ምድር ላይ ሞልተዋል።

ጠላት በህይወታችን ብዙ ፈተና የሚያመጣው እግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ለመደርመስ እና አፋችን እግዚአብሔርን ለመሳደብ ዝግጁ እንዲሆን ለማድረግ ነው። ታስታውሳላችሁ ሰይጣን ኢዮብን የፈተነብን ክስተት? እግዚአብሔር ለሰይጣኑ ስለኢዮብ ሲመሰክር እንዲ አለ "በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም”(ኢዮብ 2፥3) በዚህ ጊዜ ሰይጣን ይህን አለ "ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳብስ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል አለው። እግዚአብሔም ሰይጣንን፦ ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፥ እርሱ በእጅህ ነው አለው። (ኢዮብ 2:5-6) ይህ ክፍል ግርም ይለኛል ኢዮብ ለመከራ ተላልፎ የተሰጠው በእግዚአብሔር ፍቃድ ነው በእርሱ የደረሰው መከራ እግዚአብሔር እንዲሳደብ የሚጋብዘው ቢሆንም በዛ ፈተና ውስጥ ግን እግዚአብሔር አለመሳደቡ እግዚአብሔር ከእርሱ የሚጠብቀው ነገር ነው።

በመከራችን ውስጥ እግዚአብሔር አለ ብለን እንድንቀጥል ተፈልጎ ስንት ጊዜ ለፈተናዎቻችን ወዳቂ ሆነን እግዚአብሔር የለም ብለን ይሆን? ስንቶቻችን እግዚአብሔር ከእኛ ለሚፈልገው የጸና እምነት ጸንተን ይሆን ስንቶቻችን አለ ለምንለው እግዚአብሔር መኖር ምስክሮች ሆነን ይሆን? በችግሮቻችሁ ውስጥ ከችግሮቻችሁ አልፋችሁ አሻጋሪውን አስቡ። መኖራችሁ በአኗሪው ነውና መኖሩ አያጠራጥራችሁ። እግዚአብሔርን እንድትሰድቡት ወደ እናንተ ለመጣ ፈተና ወዳቂ እንዳትሆኑ። የእግዚአብሔርን መኖር ከመጠራጠር የከፋ በሽታ በፍጹም የለም። በሌላ በየቱም በሽታ ብትያዛ አዳኙ እግዚአብሔር ነው እግዚአብሔር የለም በሚል በሽታ የተያዝክ እንደሆነ ማነው አትራፊህ ማነው የሚደርስልህ? ነገ ለማታየው መከራ ብለህ ከመፈጠርህ በፊት ያየህን እግዚአብሔርን አትካደው።

እግዚአብሔር በማይናወጥ ዙፋኑ የነበረ፣ ያለ እና የሚኖር ዘላለማዊ አምላክ ነው። አሜን

ዲያቆን ተስፋ መሠረት
ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም

ይቀላቀሉ ➟ @fenote_tsedek
በቅንነት ያጋሩ ➟ @fenote_tsedek