Get Mystery Box with random crypto!

“በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው' ማቴዎስ 17፥4 በዬት እየሆንን ነው ያለነው? እኛ የሆኖበት ያ | ፍኖተ ~ ጽድቅ

“በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው" ማቴዎስ 17፥4

በዬት እየሆንን ነው ያለነው? እኛ የሆኖበት ያ ስፍራ የእኛ ደስታ ስለሆነ በዛ ሆንን ወይስ ለእኛ መልካም ስለሆነ ነው? እስኪ እራሳችንን እንጠይቅ የት ነው እየሆንን ያለነው? ሞልቶ አይሞላ እያልን እየጎደልን ይሆን...? እግዚአብሔር መሃሪ ነው እያልን በድፍረት ኃጢአት ተጠምቀን ይሆን..? ለስጋ ደስታ የዘላለሙን ደስታችንን እየጠፈለቅን ይሆን..? ለምድር ድሎት ከእረፍታችን አየራቅን ይሆን..? ምድር እውቃን ሰማይ ያላወቀን ሆነን ይሆን..? እስኪ ያስደስተናል የምንለውን ነገር ሁሉ እናስበው በእውነት ያ ደስታ ወቀሳ የሌለው ደስታ ነው?

ለእኛ መልካም በሆነ ስፍራ ውስጥ ደስታችን በሙላት አለ። ያስደስተናል ባልነው ነገር ውስጥ ግን አንዳንዴ መልካም ካለመሆንም አልፎ ኃጢአት ሊኖር ይችላል። እኛ ደስታችን በክርስቶስ መሆን አለበት ለዛ ነው ቅዱሱ ቃል ሁሌ በጌታ ደስ ይበላችሁ የሚለን። በዚህ መሆን ደስታዬ ነው የምንለው የት ስንሆን ነው? በእውነት ነፍሳችን የሚያስደስታት ደስታ በእግዚአብሔር መገኘት ውስጥ መሆን ብቻ ነው። የክርስቶስ ክብሩ በሚገለጥበት፣ አብ ስለልጁ በሚመሰክርበት፣ የቅዱሱ መንፈስ ህልውና በሞላበት በዛ መሆን ደስታችን ከመሆኑም ባለፈ መልካማችን ነው።

እግዚአብሔር ያለስፍራ ገደብ የሚገኝ፣ ያለ እድሜ ቁጥር የሚኖር፣ ያለ ወሰን የሚከብር፣ ያለ ከፍታ የሚገለጥ አምላክ ነው። በህይወታችን እንዲገለጥ ክብሩ የኑኗአችን አላማ እንዲሆን ክርስትናችን ያስገድደናልና በዚህ ልክ መልካም የሆነልንን ማወቅና መረዳት የማስተዋል ሁሉ ዋና ነውና ይህ አይወሰድብን። ያኔ በዚህ መሆን፣ በእግዚአብሔር ህልውና ውስጥ መሆን ለእኔ መልካም ነው የማለትን ድፍረት እናገኛለን።

ዲያቆን ተስፋ መሠረት
ነሐሴ 13/2014 ዓ.ም

ይቀላቀሉ ➟ @fenote_tsedek
በቅንነት ያጋሩ ➟ @fenote_tsedek