Get Mystery Box with random crypto!

#እንግዶች እንግዳ ለሄደበት ቤት ጊዜያዊ እንጂ ከራሚ ሊሆን አይችልም፡፡ የቆይታ ጊዜው በጨመረ ቁ | ፍኖተ ~ ጽድቅ

#እንግዶች

እንግዳ ለሄደበት ቤት ጊዜያዊ እንጂ ከራሚ ሊሆን አይችልም፡፡ የቆይታ ጊዜው በጨመረ ቁጥር እንግደነቱ ተረስቶ የቤቱ አባል ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል፡፡ በዚህ ርዕስ ዉስጥ አንባቢው እንዲረዳ የሚፈለገው አንድም እንግዳ መሆኑን እናም እንግዳ አለመሆኑን ነው፡፡ ለምትኖርበት የእናት የአባትህ ቤት እንግዳ ነህ ብትባል በፍፁም ልብህ ይህን ሊቀበል አይችልም ምክንያቱም ያ ቤት የእንድነት ቤትህ ሰይሆን የመኖርያህ ስፍራ ነው፡፡ ይህቺ የምንኖርባት ምድር የኑሮ ዘመናችን የሚፈፀምባት ብትሆንም ግን የመኖሪያ ስፍራችን ሳትሆን በእንግድነት የመጣንባት ስፍራ ናት፡፡ ብዙ ሰው ግን ሲኖር እንግዳ እንደሆነ አስቦ አይደለም የሚኖረው፡፡ እንግዳ ለሆነባት ምድር ድንበሬ ተነካ ቅጥሬ ተዘለለ ብሎ በየ ክሱ ስፍራ ይባዝናል፡፡

ጳውሎስ ሃገራችን በሰማይ ነው (ፊሊ 3፡20) ያለው ምድር ሃገራችን እንዳልሆነች ተረድቶ ነው፡፡ ምድር ሀገር የምትሆነው ምንም አይነት ሰማያዊ ተስፋ ለሌለው ብቻ ነው፡፡ እርሱ ሁልሙ እና ግቡ ምድር ምድር የሚሸት ስለሆነ የሰማዩን ማሰብ ሞኝነት ይሆንበታል ለዚህም ነው በምድር እና በውስጧ ላሉት በመገዛት ለዘላለም ከሚሆነው ነገር የሚጎደለው፡፡ መፅሐፍ በዚህ የምትኖር ከተማ የለንም (ዕብ 13፡14) በማለት እንግደነታችን ያስረግጥልናል፡፡ እንግዳ በእንግድበት በገባበት ቤት አመፀኛ እንደማሆን፣ በነፍስ አጥፊነት እንደማይሰማራ፣ የክስ መዝገብ እንደማይከፍት፣ ምላሱ እንደሚቆጠብ፣ ድርጊቱ በልክነት እንደሚታጀብ እንዲሁ የሰው ልጅ ሁሉ በምድ ላይ ላለው ኑሮ እንዲ ሊሆን ይገባዋል ማለት ነው አሊያማ ይህ ከቀረ እንግደነቱም መቅረቱ ነውና ማስተዋል ያሻል፡፡ ይህቺን ምድር ልክ እንደ ዘላለም መኖሪያችሁ መሳል የስህተት ክፍል ነው፡፡ እንግዶች እንግድነታችሁን አስተውሉ እንደ እንግዳ ኑሩ፡፡

ለምድር እንግዶች ከሆንን ነዋሪ የሆነው ለማን ነው? ጥያቄውም ሊጠቁም እንደሚፈልገው ነዋሪነታችን ለሰማይ ነው፡፡ የእግዚአብሄር መንግስት የቅዱሳን መሰብሰቢያ እና የሰው ዘር በሙሉ ቢሰበሰብት ልትጠብ የማትችል መንግስት ናት፡፡ እስኪ በማስተዋል ይህን ቃል ያንብቡ በእርሱ ስራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሄር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና ምፃተኞች አይደላችሁም፡፡ (ኤፌ 2፡18-19) ይህን የሰማይ የነዋሪነት መብትን የሰጠን የኛ መሻት እና ትጋት አይደልም ይልቁንም ይህን መብት ያገኘነው ክርስቶስ በከፈለልን ትልቅ ዋጋ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የእግዚአብሄር መንግስት መኖሪያችን እንጂ ከቶም እንግዳ የምንሆንባት ስፍራ አይደለችም፡፡ በዚች ምድር እንደ ነዋሪ መኖር ልክ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ በላይ ባለው መንግስት እንደ እንግዳ መሆን ትክክል ሊሆን አይችልም።

በምታልፈው ምድር እንደ እንግዳ ሰው እንደሆን በማታልፈው መንግስት እንደ ነዋሪ እንደሆንን እንድንረዳ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን። አሜን

ዲያቆን ተስፋ መሠረት
ሐምሌ 28/2014 ዓ.ም

ይቀላቀሉ ➟ @fenote_tsedek
በቅንነት ያጋሩ ➟ @fenote_tsedek