Get Mystery Box with random crypto!

በሁለት ታዳጊ ሴት ልጆቹ ላይ የግብረ ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል የፈፀመው ወላጅ አባት በ20 አመት | FastMereja.com

በሁለት ታዳጊ ሴት ልጆቹ ላይ የግብረ ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል የፈፀመው ወላጅ አባት በ20 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እና የአባትነት መብቱ እንዲታገድ በፍርድ ቤት ውሳኔ መተላለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።

ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ኮተቤ ቦኖ ውሃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከልጆቹ ጋር ተከራይቶ ከሚኖርበት ቤት ውስጥ ነው። ግለሰቡ እና የልጆቹ እናት ከሆነችው ባለቤቱ ጋር በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ተለያይተዋል። የ9 እና የ10 አመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊዎቹ የ2015 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት አድርገው ወደ አጎታቸው ቤት በሄዱበት አጋጣሚ ተመልሰው ወደ አባታቸው ቤት መሄድ እንደማይፈልጉ እና ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ በመግለፃቸው ጉዳዩ ወደ የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሴቶች እና ህፃናት ወንጀል ምርመራ ክፍል መምጣቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውሷል ።

ተከሳሹ ልጆቹን በፒንሳ እየቆነጠጠና እያስፈራራ ከ2010 ዓ/ም ጀምሮ የግብረ ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል ሲፈፅምባቸው መቆየቱ በምርመራ መረጋገጡን የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ፤ በአስር አመቷ ታዳጊ ላይ የክብረ ንፅህና መገርሰስ ጉዳት እንደደረሰባት፣ በ9 አመቷ ህፃን ግን ምንም እንኳ የክብረ ንፅህና መገርሰስ ባይደርስባትም ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈፀመባት የህክምና ማስረጃው ያሳያል ብሏል።

ግለሰቡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ ከተጣራበት እና በዓቃቤ ህግ ክስ ከተመሰረተበት በኋላ ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ ወንጀል ችሎት ሰሞኑን በዋለው ችሎት በ20 ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እና ከቤተዘመድ ስልጣን እንዲሁም ከአባትነት መብቱ እንዲታገድ ውሳኔ ያስተላለፈበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።

በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ከአካላዊ ጉዳት ባሻገር በስነልቦና ላይ ዘላቂ ጉዳትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ጭምር በመሆናቸው የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።

@FastMereja