Get Mystery Box with random crypto!

በባንኮች ላይ ዘረፋ የፈፀሙ የጥበቃ ሰራተኞችና ግብራበሮቻቸው ተቀጡ #FastMereja በኦሮሚያ | FastMereja.com

በባንኮች ላይ ዘረፋ የፈፀሙ የጥበቃ ሰራተኞችና ግብራበሮቻቸው ተቀጡ
#FastMereja
በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እና በወጋገን ባንክ ላይ ዘረፋ የፈፀሙ ሁለት የጥበቃ ሰራተኞች እና ሰባት ግብራበሮቻቸው በእስራት ተቀጡ፡፡

አለሙ አሰፋ የተባለው ተከሳሽ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጃክሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በከልቻ ቅርንጨፍ ውስጥ በጥበቃ ስራ ተቀጥሮ እያገለገለ ነበር፡፡

ተከሳሹ መስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም የምሽት ተረኛ የሆነው የስራ ባልደረባውን "ዛሬ እኔ ልሸፍንልህ አንተ ወደ ቤት ሂድ" ብሎ እንዲሄድ ካደረገ በኋላ ይርጋለም አድማሱ ከተባለው ግብረ አበሩ ጋር በመሆን በፌሮ ብረት ካዝና በመስበር 2ሺህ 414 የአሜሪካ ዶላር እና ከ2 ሚሊዮን 280 ሺህ በላይ ብር ዘርፈው በበመውሰድ ተሰውረው ቆይተዋል፡፡

በሌላ በኩል ገበየሁ ምስጋና የተባለ የወጋገን ባንክ የረር ቅርንጨፍ የጥበቃ ሠራተኛ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ በተፈፀመው ወንጀል ተሳትፎ ከነበረው ይርጋለም አድማሱ እና ከሌሎች አራት ግለሰቦች ጋር በመተባበር ሃምሌ 3 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ገደማ የዘረፋ ወንጀል ፈፅመዋል፡፡

ተከሳሾቹ በዕለቱ በባንኩ የጥበቃ ስራ ላይ የነበረው ታሪኩ መንገሻ የተባለውን ግለሰብ እጅና እግሩን በማሰር የውንብድና ወንጀል ከፈፀሙበት በኋላ 419 ሺህ ብር ዘርፈው ወስደዋል፡፡

ፖሊስ የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት ከደረሰው በኋላ መረጃዎችን በማሰባሰብ እና ያልተቋረጠ ክትትል በማድረግ በተለያየ ደረጃ ተጠያቂነት ያለባቸውን በአጠቃላይ ዘጠኝ ግለሰቦችን ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ጭምር በቁጥጥር ስር በማዋል ክስ እንዲመሰረትባቸው አድርጓል፡፡

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ይርጋለም አድማሱ በሁለቱም ባንኮች ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎች በመሳተፉ በ14 ዓመት ከ 3 ወር እስራት እንዲቀጣ ሲወስን ገበየሁ ምስጋናው በ 8 ዓመት፣ እዮብ ተመስገን፣ አለሙ አሰፋ፣ እና ሀይለማርያም መለሠ እያንዳንዳቸው በ7 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ እንዲሁም ተሾመ ደምለው በ 4 ዓመት ፣ አቤል ንጉሴ በአንድ ዓመት እስራት እና በ1 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ የወሰነ ሲሆን በመሸሸግ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸውና ለጊዜው ያልተያዙት ጥላሁን ወልዴ እና ጌታሁን ተፈራ የተባሉ ተከሳሾች በሌሉበት እያንዳንዳቸው በ 1 ዓመት ከ6 ወር እስራት እና በ2ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል ።

ሁለቱ የባንኮቹ የጥበቃ ሰራተኞች ሲቀጠሩ በቂ ዋስትና እና ሰነድ ያልነበራቸው መሆኑ የምርመራ እና የክትትል ስራውን አስቸጋሪ አድርጎት እንደቆየ የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት የጥበቃ ሠረተኞችን ሲቀጥሩ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

@fastmereja