Get Mystery Box with random crypto!

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዘዘ #FastMereja ኮሜዲያን | FastMereja.com

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) ማረሚያ ቤት እንዲወርድ ታዘዘ
#FastMereja
ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም ባልቻ በቅጽል ሥሙ (ልጅ ያሬድ) በቀረበበት ተደራራቢ ክስ ማረሚያ ቤት እንዲወርድ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ የፀረ-ሽብርና የሕገ-መንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ተላልፏል።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም ባልቻ በቅጽል ሥሙ( ልጅ ያሬድ) በተባለ ግለሰብ ላይ ተደራራቢ ክሶችን አቅርቧል።

በተለይም በኮምፒዩተር የሚፈጸም ወንጀል ድንጋጌን መተላለፍ፣ የቤተክርስቲያንና የሰዎችን ክብርና መልካም ስም በማጉደፍ፣ ጥላቻ ንግግር ማሰራጨት የሚሉ ነጥቦች ይገኙበታል።

ክሱ ከደረሰው በኋላ ተከሳሹ ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄው ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል አዟል።

ይሁንና ተከሳሹ ችሎት በቀረበበት ጊዜ ዐቃቤ ሕግ ለቤተክርስቲያን ክብር፣ ለማህበረሰቡ ስነልቦና፣ እሴትና ባህል ሲባል በክሱ ላይ የቀረቡ ዝርዝር ነጥቦች እንዳይታተም በሚዲያ እንዳይቀርብ እንዲሁም ችሎቱ በዝግ እንዲሆን አቤቱታ አቅርቧል።

አቤቱታውን የመረመረው ፍርድ ቤቱም የማህበረሰቡን ክብርና ስነልቦናን ከግምት ውስጥ በማስገባት የክሱ ዝርዝር ጉዳይ በሚዲያ እንዳይሰራጭ ችሎቱ በዝግ እንዲሆን ብይን መስጠቱን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።

ልጅ ያሬድ በቅርቡ ለማህበራዊ ትስስር ገፅ ተከታዮቹ ባጋራው የቲክቶክ ቪዲዮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ክብር የሚነካ እና የእምነቱ ተከታዮችን ያስቆጣ ተግባር መፈጸሙን ተከትሎ፤ በርካቶች "በሕግ መጠየቅ አለበት" የሚል ሃሳባቸውን ሲያንፀባርቁ እንደነበር ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በቲክቶክ ቪዲዮ ባጋራው ሕገ ወጥ ይዘት ያለው መልዕክት ሳቢያ፤ ነሃሴ 27/2015 በቁጥጥር ሥር መዋሉ ይታወቃል ሲል አዲስ ማለዳ ነው ያስነበበው።

@fastmereja