Get Mystery Box with random crypto!

ሰው አግተው ገንዘብ ተቀብለዋል የተባሉ የአዲስ አበባ የፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሠረተ። የተሰ | FastMereja.com

ሰው አግተው ገንዘብ ተቀብለዋል የተባሉ የአዲስ አበባ የፖሊስ አባላት ላይ ክስ ተመሠረተ።

የተሰጣቸውን ኃላፊነት ያለአግባብ በመገልገል ሰው አግተው ገንዘብ ተቀብለዋል የተባሉ የአዲስ አበባ የፖሊስ አባላት ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተ።

ክሱን ያቀረበባቸው የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ነው።

ክስ የተመሰረተባቸው አጠቃላይ አራት ሲሆኑ፥ ሶስት ተከሳሾች የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት እንዲሁም አንድ ተከሳሽ በግል ስራ ይተዳደራል የተባለ ግለሰብ ነው።

ተከሳሾቹ 1ኛ ረ/ሳ ሰለሞን ባህሩ ከበደ፣ 2ኛ ም/ሳ ሲሳይ ተገኝ እንግዳው፣ 3ኛ ም/ሳ ተስፋዬ መኳንንት ላቀው እና 4ኛ በግል ስራ ይተዳደራል የተባለው ዮናታን ሳሙኤል ሙሉብርሃን ናቸው።

ተከሳሾቹ አንደኛ ክስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ እንዲሁም ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ በሚል ነው።

በዚህም የክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን የክትትል እና ኦፕሬሽን ኦፊሰር የስራ መደብ ሲሰሩ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ በመስከረም 02 ቀን 2016 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 12፡30 ሲሆን፥ በኮልፌ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ክልል ልዩ ቦታው ሆላንድ ኤምባሲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሶ ተሽከርካሪ ይዞ ሲጓዝ የነበረውንና በስራ አጋጣሚ የሚያውቁትን ግለሰብን እንዲቆምላቸው እና ትብብር እንዲያደርግላቸው ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ ሌላ መኪናን ማለትም የግል ተበዳይ የሆነ ግለሰብ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2-A36466 አ/አበባ መኪና ሲያሽከረክር የነበረ ግለሰብ ታርጋን ለይተው መያዛቸውንና ግለሰቡ በህግ ተፈላጊ እንደሆነ አድርገው በመግለጽ መኪናውን ተከታትሎ እንዲያስቆምላቸው መጠየቃቸው በክሱ ተዘርዝሯል።

ከዚህ በኋላ የግል ተበዳይ ተከታትለው ተሽከርካሪውን ካስቆሙት በኋላ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የግል ተበዳይ መኪና ውስጥ ያለፈቃድ በመግባት መኪናውን ወዳልታወቀ ቦታ እንዲያሸከረክር በማስገደድና ለወላጅ አባቱ ስልክ በማስደወል 1ኛ ተከሳሽ የተበዳይን አባት ለግዜው ባልተያዘ ግብረ አበራቸው ስም ወደ ተከፈተ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 10 ሚሊዮን ብር ካላስገባ ልጁን እንደሚገድሉት በመግለጽ የማስፈራራት የወንጀል ተግባር መፈጸማቸው ተጠቅሷል በክሱ።

በተለይም ገንዘቡን እስከሚያገኙ ድረስ ተበዳዩን አግተው በማቆየት ከተበዳይ አባት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ በሞባይል ባንኪንግ ሲሰተም 100 ሺህ ብር እንዲገባ ማስደረጋቸውና ገንዘቡም መግባቱን ሲያረጋግጡ ተበዳዩን የለቀቁት በመሆኑ በክሱ ተገልጿል።

በተጨማሪም 1ኛ ተከሳሽ ያለህን ገንዘብ አምጣ በማለት ከግል ተበዳይ 6 ሺህ ብር ተቀብሎ ለ2ኛ ተከሳሽ መስጠቱን ተከትሎ ተከሳሾች በተደረገባቸው ክትትል ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ጊዜ ከ2ኛ ተከሳሽ ኪስ ውስጥ ከግል ተበዳይ የወሰደው 6 ሺህ ብር ጥሬ ገንዘብ መገኘቱን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል።

3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት የግል ተበዳይን ባስቆሙበት ጊዜ ከግል ተበዳይ ጋር በመኪና ውስጥ የነበሩ ሁለት ግለሰቦችን መኪናው ውስጥ በመግባት እንዳይንቀሳቀሱ አግቶ በማቆት በተበዳይ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ህገወጥ ድርጊት እንዳያስቆሙ የተከላከለ እና ለ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ሽፋን የሰጠ መሆኑ ተጠቅሶ በክሱ ላይ ተዘርዝሯል።

በአጠቃላይ ተከሳሾች በመላ ሃሳባቸው በወንጀል ድርጊቱ ሙሉ ተካፋይ በመሆን የተሰጣቸውን ሃላፊነት በግልጽ ተግባር ያለአግባብ በመገልገል 3 ግለሰቦችን በማገት 106 ሺህ ብር አስፈራርተው በመውሰድ ጉዳት ያደረሱ በመሆኑ በፈጸሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በሁለተኛ ክስ ደግሞ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 1/ ሀ እና በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ፣ ለ እና ሐ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል ተብሎ ክስ ቀርቦባቸዋል።

በዚህም የክስ ዝርዝር ላይ 1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመገልገል የሚያገኙትን ገንዘብ ህገወጥ ምንጭ ለመደበቅ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ከግል ተበዳይ አባት የወሰዱትን ገንዘብ ዮናታን ሳሙኤል በተባለ ግብረአበራቸው ስም በተከፈተ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ እንዲያስገባ በመግለጽ በአካውንቱ በሞባይል ባንኪንግ 100 ሺህ ብር እንዲገባ ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል፡፡

4ኛ ተከሳሽ ደግሞ ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ በስሙ ተከፍቶ ገቢ ከሆነለት ከ100 ሺህ ብር ውስጥ 40 ሺህ ብር ከባንክ በጥሬ 10 ሺህ ብር ደግሞ በኤቲኤም ወጪ በማድረግ 20 ሺህ ብሩን በስሙ በአዋሽ ባንክ ወደ ተከፈተ ሂሳብ ማስተላለፉና 30 ሺህ ብር ደግሞ በስሙ በህብረት ባንክ በተከፈተ ሂሳብ ካስተላለፈ በኋላ ሙሉውን ገንዘብ ወጪ አድርጎ የተረከበ መሆኑ መጠቀሱን ኤፍቢሲ ዘግቧል።

በዛው ጊዜ ሙሉውን ገንዘብ በካሽ ወጪ በማድረግ ህገወጥ ተግባር የተገኘውን ገንዘብ የተረከበ በመሆኑ ባጠቃላይ በተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ ሶስቱ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን፥ የዋስትና ጥያቄ ላይ ክርክር ለማድረግና የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ከነገ በስቲያ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል ሲል ፋና ነው የዘገበው።