Get Mystery Box with random crypto!

የንብረት ታክስ ፍተሀዊ የታክስ አይነት ነውን? የአንድ ታክስ አይነት ፍተሀዊነት የሚለካው የታክስ | Farankaa - ፈራንካ

የንብረት ታክስ ፍተሀዊ የታክስ አይነት ነውን?

የአንድ ታክስ አይነት ፍተሀዊነት የሚለካው የታክስ አየነቱ ተግባራዊ በሚየደርጋቸው የተለያዩ መርሆች እና አሰራሮች ነው፡፡ ከዚህም አንጻር የንብረት ታክስን ፍተሀዊ ሊያደርጉ የሚችሉ እና እንደየአገሮች ነባራዊ ሁኔታ ተገባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ መርሆች እና አሰራሮች አሉ፡፡
እነዚህ የተለዩ መርሆች እና አሰራሮች እንዳሉ ሆነው የንብረት ታክስን መሰረታዊ ጽንሰሀሳብ በመመልከት ይህ የታክስ አይነት ፍተሀዊ ነው ወይንስ አይደለም የሚለውን ማየት ይቻላል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ይህንን የታከስ አይነት ከተጠቃሚነት መርህ (Benefit principle) እና የመክፈል አቅም መርህ (Ability to pay principle) አንጻር መመልከት አሰፈላጊ ነው፡፡እነዚህ ሁለት መርሆች ወይም ጽንሰሀሳቦች የአንድን የታክስ አይነት ፍተሀዊነት ለመለካት የሚገለግሉ ሲሆን የንብረት ታክስ ከእነዚህ መርሆች አንጻር ምን እንደሚመስል በአጭሩ እነደሚከተለው መመልከት ይችላል፡፡

በተጠቃሚነት መርህ ውስጥ ያለው መሰረታዊ ጽነሰሀሳብ እንደሚያስገነዝበው ታክስን መክፈል ያለባቸው ከሚከፈለው ታክስ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ የታክስ ፍተሀዊነት ይሰፍናል፡፡ ይህ የሰጥቶ መቀበል መርህ ሁሉም የታክስ አይነቶች የሚከፈሉበትን ጠቅላላ ምክንያት የሚያሳይ ነው፡፡የአንድ ሀገር ነዋሪዎች ማንኛውንም ታክስ ሲከፍሉ ታከስን የሚሰበስበው አካል ማለትም መንግስት በሚሰበስበው ታክስ ለነዋሪዎች ማቅረብ የሚገባውን አገልግሎት ማቅረብ እንዲያስችለው ነው፡፡
ይህ ጽንሰሀሳብ ሁሉም የታክስ አይቶች የሚከፈሉበትን ምክንያት የሚያሳይ ቢሆንም በንብረት ታክስ ውስጥ ስንመለከተው ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ያለው ነው፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው የንብረት ታክስ በዋናነት የከተማ መስተዳድሮች የሚጥሉት የታክስ አይነት ነው፡፡ ከዚህ ታከስ የሚሰበሰበውም ገንዘብ ስራ ላይ የሚውለው በከተማ መስተዳድሮቹ ውስጥ ለሚካሄዱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና ህዝባዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ነው፡፡ በመሆኑም የየከተማዎቹ ነዋሪዎች የሚከፍሉት የንብረት ታክስ በሚኖሩበት ከተማ ስራ ላይ ስለሚውል የተጠቃሚነት መርህ በተለየ ሁኔታ በንብረት ታክስ ውስጥ ፍተሀዊነትን ያረጋግጣል፡፡

የመክፈል አቅም መርህን በተመለከተ የንብረት ታክስ ያለው ገጽታ ምን ይመስላል የሚለውን ስንመለከት የንብረት ታክስ ከፋዮች እነማን ናቸው የሚለውን ማየት ይኖርብናል፡፡ የንብረት ታክስ የንብረቶችን ዋጋ መሰረት ያደረገ የታክስ አይነት እንደመሆኑ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ንብረቶች ባለቤት የሆኑ ሰዎች ከፍ ያለ የንብረት ታክስ የመክፈል ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ንብረቶች ባለቤት የሆኑ ሰዎችም አነስተኛ የሆነ የንብረት ታክስ የመክስል ግዴታ ስለሚኖርባቸው ይህ የታክስ አይነት የመክፈል አቅምን ያገናዘበ ፍተሀዊ የታክስ አይነት ነው ሊባል ይችላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአብዛኛዎቹ የንብረት ታክስ ስርአቶች ከታከስ ነጻ የሚደረጉ የንብረት አይነቶች አሉ፡፡ንብረቶችን ከታክስ ነጻ የማድረግ ስርአቶችም ተፈጻሚ ከሚሆኑበት ዋነኛ ሁኔታዎች ውስጥ የንብረቶቹን ባለቤቶች ታክስ የመክፈል አቅም ከግምት በማስገባት የሚደረገው አንዱ ነው፡፡ ይህም የንብረት ታክስን ፍተሀዊነት ለማስፈን ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

የንብረት ታክስ ውጤታማ የታክስ አይነት ነውን?
የታክሶች ውጤታማነት የሚለካው ታክሶቹ የሚያስገኙትን ገቢ እና ታክሶቹን ለመሰብሰብ የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን ከግምት በማስገባት ነው፡፡ በዚህም መሰረት ውጤታማ ታክስ የሚባሉት አነስተኛ ወጪ የሚያስፈልጋቸው እና በተነጻጻሪነት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ የታክስ አይነቶች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አነድ የታክስ አይነት በአጠቀላይ ኢኮኖሚ ውስጥ ከሚፈጥሩት የኢኮኖሚ ማዛባት(distortion) አንጻር ሊታይ ይችላል፡፡

የንብረት ታክስን ውጤታማነት ከሚያስገኘው ወጪ እና ከሚያስገኘው ገቢ አንጻር የሚወሰነው ታክሱ በሚጠቀመው የንብረት ዋጋ አሰላል ዘዴዎች እንዲሁም በሌሎች በታከስ ህጉ በተግባር ላይ በሚውሉ አሰራሮች ነው፡፡ የንብረት ታክስን ለመጠል ሲባል የንብረቶች ዋጋ በተለያዩ መንገዶች ሊተመን ይችላል፡፡ ከእነዚህም መንገዶች ውስጥ የንብረቶች የገበያ ዋጋ፣(capital value system) የንብረቶች የኪራይ ዋጋ (rental value system)፣ የመሬት ዋጋ (site value system) እና ንብረቶች ያላቸው የይዞታ ስፋት (area based system) በዋናነት በስራ ላይ ይውላሉ፡፡ እነዚህ የአተማመን ስልቶች የተለያየ ወጪ የሚያስወጡ ሲሆን እነደየሀገራት ነባራዊ ሁኔታ በስራ ላይ ይውላሉ፡፡

የንብረቶች የገበያ ዋጋን የሚከተለው የአተማመን ስልት ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ በመሆኑ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ ሀገራት ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ በሌላ በኩል የንብረቶችን የይዞታ ስፋትን መሰረት የሚየደርገው ስልት በአሰነስተኛ ወጪ ተጋባራዊ ሊሆን የሚችል ቢሆንም በቂ ገቢ ለማስገኘት ከፍተኛ የታክስ የማስከፈያ ልክ (tax rate) የሚያስፈልገው በመሆኑ ብዙውን ጊዜ ተመራጭ አይሆንም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ የአተማመን ስልት በተለያየ የጥራት ደረጃ ላይ የሚገኙ ንብረቶችን በተመሳሳይ ሁኔታ የዋጋ ተመን ስለሚያወጣላቸው የታከስ ፍተሀዊነት ይጎድለዋል፡፡ በመሆኑም የንብረቶች የኪራይ ዋጋ እና ንብረቶች ያላቸው የይዞታ ስፋትን የሚጠቀሙት የአተማመን ስልቶች የንብረት ታክክን ውጤታማነት ከፍተሀዊነት ጋር ለማስፈን ያገለግላሉ፡፡

የንብረት ታክስን ውጤታማነት ታክስ በኢኮኖሚ ውስጥ ከሚያስከትለው መዛባት አንጽር ስንመለከት የንብረት ታክስ ይልቁንም የመሮት ዋጋ የተካተተበት የንብረት ታክስ በገበያውስጥ የሚፈጥረው መዛባት አነስተኛ በመሆኑ ውጤታማ የታክስ አይነት ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይህም የሚሆንበት ዋነና ምክንያት በዚህ የታክስ አይነት መጣል የተነሳ ታክስ ከፋዮች ወይም የንብረት ባለቤቶች ከንብረት ባለቤትነታቸው ጋር በተያያዘ ባህሪያቸውን ብዙም ስለማይቀይሩ ነው፡፡


የንብረት ታክስ በኢትዮጵያ

በአሁኑ ግዜ በሀገራችን ያለው የንብረት ታክስ በተለምዶ የጣሪያ እና ግብር በመባል የሚታወቅ ነው፡፡ በሀገራችን ያለውን የንብረት ታክስ የሚገዙ ዋና ዋና የህግ ድንጋጌዎች አራት አስርት አመታት ያስቆጠሩ ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ ያለው የንብረት ታክስ በዋናነት የሚመራው በአዋጅ ቁጥር 80/1968 ነው፡፡ይህ አዋጅ የከተማ መሬት ኪራይን እና የከተማ ቤቶችን ታክስ ወይም ግብርን አስመልክቶ የተደነገገ ሲሆን በዚህ አዋጅ አንቀጽ 5 መሰረት በከተሞች የሚገኙ ቤቶች ባለቤት የሆኑ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ ድርጅቶች፣ ወይም ህብረት ስራ ማህበራት ባለቤት በሆኑበት ቤት ላይ ግብር ወይም ታክስ መክፈል እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
ከአዋጅ ቁጥር 80/1968 እንደምንረዳው በሀገራችን ያለው የንብረት ታክስ በከተማ ቤቶች ላይ የተገደበ ነው፡፡ የንብረት ታክስን በሚጠቀሙ በሌሎች ሀገራት ይህ ታክስ ሰፊ ሽፋን ያለው ነው፡፡ በአብዛኛዎቹ ሀገራት የከተማ መሬቶች እና ህንጻዎች በመርህ ደረጃ የንብረት ታክስ የሚጣልባቸው ሲሆን የከተማ መሬቶች የንብረት ታክስ የሚጣልባቸው በተነጻጻሪነት ከፍ ያለ ታክስ ይጣልባቸዋል፡፡