Get Mystery Box with random crypto!

የንብረት ታክስ ምንነት እና ባህሪያት የንብረት ታክስን ምንነት በተመለከተ የተለያዩ እና አከራካሪ | Farankaa - ፈራንካ



የንብረት ታክስ ምንነት እና ባህሪያት

የንብረት ታክስን ምንነት በተመለከተ የተለያዩ እና አከራካሪ አመለካከቶች በመኖራቸው ወጥ እና ተመሳሳይ የሆነ ትርጉም ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የታክስ አይነት ተግባራዊ በሚየደርጉ አገሮች እና የዚህን የታክስ አይነት አጠቃላይ የህግ ፍልስፍና በመመልከት መሰረታዊ የሆኑ እና የታክስ ህግ ምንነትን ሊያሳዩ የሚችሉ የጋራ ትርጉሞችን ማስቀመጥ እንችላለን ፡፡
በአጠቃላይ የንብረት ታክስን ታሪክ ስንመለከት ይህ የታክስ አይነት የረጅም ግዜ ታሪክ ያለው ነው፡፡ ይህ የታክስ አይነት በተለያዩ አገራት ከ3000 አመታት በላይ ለሆነነ ግዜ አየተተገበረ ያለ ሲሆን ተግባራዊ የሚደረገውም ይዞታን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡የዚህ ታክስ ከፋዎች የሚሆኑትም የንብረቶች ባለቤቶች ወይም ባለ ይዞትዎች ናቸው፡፡

ከሌሎች የታክስ አይነቶች ለምሳሌ ከ ተጨማሪ እሴት ታክስ እና ከገቢ ግብር በተለየ መልኩ ይህ የታክስ የሚጣለው ግብየትን መሰረት ባላደረገ መልኩ ነው ፡፡ ይህም በመሆኑ በተነጻጻሪንነት የማይቀያየር (static) የሆነነ ባህሪ ይኖረዋል፡፡በአንጻሩ እነደተጨማሪ እሴት ታክስ አይነት ያሉ ታክሶች በየግብየቱ ስለሚጣሉ የተለዋዋጭነት ባህሪ ይኖራቸዋል፡፡

የንብረት ታከስ የንብረቶችን ዋጋ መሰረት በማድረግ የሚጣል የታክስ አይነት መሆኑ ሌላኛው መለያው ሲሆን ከሌሎች ንብረቶች በተለየ መልኩ ይህ ታክስ በማየንቀሳቀሱ ንብረቶች (real properties) ላይ በአብዛኛው ተፈጻሚ ሚደረግ ነው፡፡ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በመባል የሚታወቁት መሬት እና ህንጻዎች ሲሆኑ በእነዚህ ንብረቶች ላይ የንብረት ታክስ የሚጣልበት ሁኔታ እና ታክሱ የሚጣልበት መጠን እንደየአገራቱ የታክስ አጣጣል ስርአት የሚለያይ ነው፡፡

ከሌሎች የታክስ አይቶች ጋር ሲነጻር የንብረት ታክስ በቀላሉ በከፋዮች እይታ ውስጥ የሚገባ (visible) የታክስ አይነት ሲሆን ይህም ከአከፋፈል ስርአቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የገቢ ግብርን እና የሽያጭ ታክስን ስንመለከት የገቢ ግብር በመሰረታዊነት ከምንጩ ተቀናሽ በመደረግ የሚከፈል ሲሆን የሽያጭ የታክስ ደግሞ በየግዜው በሚደረጉ ግብይቶች በአነስተኛ መጠን የሚከፈል ነው፡፡ በአንጻሩ የንብረት ታክስ ከፋዮች የሚከፍሉትን ታክስ በቀጥታ ለታክስ ባለስልጣን የሚከፍሉ በመሆኑ እና ይህም አብዛኛውን ግዜ በአመት አንድ ጊዜ ስለሚከፈል በቀላሉ በእይታ ውስጥ የሚገባ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የንብረት ታክስ በዋናነት የሚከፈለው የከተማ መስተዳድሮች የመሰረተ ልማት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ በሚያቀርቡበት ግዜ የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን ነው፡፡ ከዚህ ታክስ የሚሰበው ገነዘብም ለዚህ አገልግሎቶች የሚውል በመሆኑ ታክስ ከፋዮች በአካቢያችው የሚገነቡትን የመሰረተልማት ግንባታዎች እና የሚቀርቡትን አገልግለቶች በመመልከት የከፈሉት ታክስ ለተገቢው አላማ መዋል አለመዋሉን መመልከት ይችላሉ፡፡
የንብረት ታክስ ጠቀሜታዎችበአጠቃላይ የንብረት ታክስ የታችኛው የአስተዳድር እርክን የሚያስፈልጉትን ወጪዎች ለመሸፈን የሚያገለግል ሲሆን የአብዛኛዎቹ አገራት ከተማ መስተዳድራት አብዛኛው ገቢያቸውን ከዚህ የታክስ አይነት ያገኛሉ፡፡ የዚህ ታክስ ገቢ ሽፋን ድርሻ በአደጉት አገራት እስከ 100% የሚደርስ ሲሆን ይህ የታክስ አይነት በታዳጊ አገራት ትኩረት ካለማግኘቱ ጋር ተያይዞ በከተማ መስተዳድሮች ያለው ድርሻ አነስተኛ ነው ፡፡

የንብረት ታክስ ከገጠር አካባቢዎች ይልቅ በከተሞች ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡ የዚህ ታክስ አይነት ተቀሜታ በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ የሆነበት ዋነኛ ምክንያቶች በከተሞች አካባቢ ካለው ከፍተኛ የመሬት ዋጋ እና በእነዚሁ አካባቢዎች ካለው የህንጻዎች ብዛት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የንብረት ታክስ በከተሞች የሚጣል የታክስ አይነት እነደሆነ ተደርጎ ይታሰባል፡፡

የንብረት ታክስ በአንድ በኩል የመስተዳድሮችን ራስን ማስተዳደርን ሲያጎለብት በሌላ በኩል መስተዳድሮች ለነዋሪዎቻቸው ያላቸውን ተጠያቂነት ያሳድጋል፡፡ ከንብረት ታክስ የሚሰበሰበው ገንዘብ መስተዳድሮቹ ለሚያቀርቧቸው አገልግሎቶች የሚውል በመሆኑ ከዚሁ ታክስ የሚሰበሰበው ገንዘብ መስተዳድሮቹ ለሚያቀርቡት አገልግሎት በቂ በሆነ ግዜ መስተዳድሮቹ በማዕከላዊ መንግስት ያላቸውን ጥገኝነት ይቀንሳል፡፡

ከንብረት ታክስ የሚሰበሰበው ገንዘብ ጠቅም ላይ የሚውልበት ሁኔታ በታክሱ ከፋዎች በቀላሉ በእየታ ውስጥ የሚገባ በመሆኑ መስተዳድሮች ለነዋሪዎቻቸው ያላቸውን ተጠያቂነት ይጎለብታል፡፡ የመስተዳድሮቹ ተጠያቂነት በሚያድግበት ግዜም ባለስልጣናት እንደሙስና ወደመሳሰሉ ህገወጥ ተግባራት አንዳይገቡ ያደርጋል፡፡

የንብረት ታክስ ጠቀሜታ ፍትሀዊ እና ውጤታማ የመሬት አስተዳደርን ከማስፈን አንጻርም ሊታይ ይችላል፡፡የመሬት አጠቃቀምን አስመልክቶ ሊከሰቱ ከሚችሉ አላስፈላጊ ነገሮች ወይም ተግባራት ውስጥ አንዱ የመሬት ዋጋ መጨመርን መጠባበቅ (land speculation) ነው፡፡ የመሬትን ዋጋ መጨመርን መጠባበቅ የሚከሰተው የመሬት ባለይዞታዎች በያዙት መሬት ላይ በቂ የሆነ ግንባታወይም ኢንቨስትመንት ሳያደርጉ በግዜ ቆይታ በያዙት መሬት ላይ የሚከሰተውን የመሬት ዋጋ ጭማሪ ለማግኘት በማሰብ መሬት ሲይዙ ነው፡፡ ይህንን ችግር ከመቅረፍ አኳያ የንብረት ታክስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

የንብረት ታክስ በተለይም በመሬት ላይ የሚጣል የንብረት ታክስ በሚኖርበት ግዜ መሬትን ሳያለሙ ዋጋው ይጨምራል በሚል እሳቤ መሬትን የመያዝ ሁኔታ (land speculation) ይቀንሳል፡፡ ይህም የሚሆነው የመሬት ባለይዞታዎች የያዙትን መሬት ሳያለሙ እና ከመሬቱ ጥቅም ሳያገኙ በመሬቱ ላይ ታክስ ብቻ እየከፈሉ ለመቆየት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ስለማይኖራቸው ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ መሬትን በአግባቡ የሚያለሙ ሰዎች ብቻ የመሬት ባለይዞታ የሚሆኑበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህም ውጤታማ የመሬት አስተዳደር እንዲኖር ያደርጋል፡፡

መሬትን በአግባቡ የሚያለሙ ሰዎች ብቻ የመሬት ባለይዞታ በሚሆኑበት ግዜ ፍትሀዊ የመሬት ባለቤትነት ይፈጠራል፡፡የመሬት ዋጋ መጨመርን መጠባበቅ (land speculation) በሚስፋፋበት ግዜ የመሬት ዋጋ በእጅጉ ይንራል፡፡ ይህ የመሬት ዋጋ መጨመር በትክክለኛ ወይም ጤናም በሆነ ሁኔታ የሚመጣ ባለመሆኑ በኢኮኖሚ ውስጥ ኢ-ፍተሀዊነትን ይፈጠራል፡፡ በመሬት ላይ የሚጣል የንብረት ታክስ በሚኖርበት ግዜ መሬትን ለመያዝ ያለው ፍላጎት (demand) ስለሚቀንስ የመሬት ዋጋ ተመጣጣኝ ይሆናል፡፡ ይህም አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የመሬት ባለይዞታ እንዲሆን ስለሚያደርግ በመሬት ይዞታ ዙሪያ ፍተሀዊነትን ይፈጥራል፡፡


የንብረት ታክስ እና ጠቅላላ የታክስ መርሆች

ማንኛውም አይነት ታክስ በሚጣልበት ግዜ ሊከተላቸው የሚገቡ ጠቅላላ የታክስ መርሆች አሉ፡፡ አዳም ስሚዝ የተባለ ሊቅ wealth of nations በተባለ መጽፉ ላይ እንዳሰፈረው ውጤታማነት (efficiency)፣ ፍትሀዊነት (equitablity)፣ ቀላልነት (simplicity) እና አመቺነት (convenience) ዋነኛ የታክስ መርሆች ናቸው፡፡ አንደማንኛውም የታክስ አይነት የንብረት ታክስ አጣጣልን ከእነዚህ መርሆች አንጻር ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ከእነዚህም መርሆች ውስጥ ፍተሀዊነት እና ውጤታማነት በዚህ ጽሁፍ የሚዳሰሱ ይሆናል፡፡