Get Mystery Box with random crypto!

አሜሪካ የአል ቃኢዳውን መሪ አይማን አል-ዛዋሂሪን መግደሏን አስታወቀች!! አሜሪካ የአል ቃኢዳውን | Fana Tv/Fbc ™

አሜሪካ የአል ቃኢዳውን መሪ አይማን አል-ዛዋሂሪን መግደሏን አስታወቀች!!

አሜሪካ የአል ቃኢዳውን መሪ አይማን አል-ዛዋሂሪን በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ውስጥ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት መግደሏን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስታወቁ።

የአሜሪካ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሲአይኤ ባለፈው ዕሁድ ካቡል ውስጥ ባካሄደው የፀረ-ሽብር ዘመቻ ላይ ነው ዛዋሂሪን መግደል የቻለው ተብሏል። ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግድያውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ አይማን አል-ዛዋሂሪ በአሜሪካ ዜጎች ላይ ግድያ እና ጥቃትን የቀረጸ ሰው ነው ያሉ ሲሆን “አሁን ፍትህ ተሰጥቷል ፤ ይህ የአሸባሪ ቡድን መሪ ከዚህ በኋላ በሕይወት የለም” ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ዛዋሂሪ በአንድ በጥብቅ በሚጠበቅ ቤት በረንዳ ላይ ተቀምጦ ባለበት ወቅት ነው የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ሁለት ሚሳኤሎችን ተኩሶ የገደለው። እንዲሁም በቤቱ ውስጥ የነበሩ ሌሎች የቤተሰብ አባላት ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው እና በጥቃቱ ዛዋሂሪ ብቻ ተነጥሎ መገደሉን መናገራቸውን ቢቢሲ አስነብቧል።

ዛዋሃሪ ከቀድሞው የአል-ቃኢዳ መሪ ቢን ላደን ጋር በመሆን ከ20 ዓመታት በፊት የተፈጸመውን የ9/11 ጥቃትን የመራ ሲሆን አሜሪካ ለረጅም ዓመታት ስታፈላልገው የቆየችው የሽብር ቡድኑ መሪ ነው። አይማን አል-ዛዋሂሪ የኦሳማ ቢን-ላደን ሕልፈትን ተከትሎም አል-ቃኢዳን ሲመራ ቆይቷል።