Get Mystery Box with random crypto!

ለውብ ለይል ቅዳሜ semir aklu The magic of thinking BIG!! | ፅሁፍ በፋኢዛ 🤗

ለውብ ለይል ቅዳሜ


semir aklu

The magic of thinking BIG!!!!


( ሂማ አታሳንሱ!!!!!!!)

@ መግቢያ፣ ሂማ በአረብኛ ይሆንልኛል ብለን የምናስበው፣ ራእይ፣ ምኞት፣ ሃሳብ
የምንፈጽምበት ትልቅ ወኔ ጭምር ማለት ነው።
ሰሞኑን The magic of thinking BIG!!!! በሚል ርእስ የተፃፈ አንድ የፈረንጅ ሃገር
መፅሃፍ እጄ ገባና ሳነበው ከረምኩ። አነቃቂና አደፋፋሪ መፅሃፍ ነው። በትልቁ እያሰቡ ፣
በትልቁ እያለሙ ፣በትልቁ እየሰሩ መኖር ለሰው የተሰጠው ፀጋ ነው፣ ለሰማይ ያሰቡት ጣራ ሳይነካ አይመለስም፣ ለተራራ ያለመ ኮረብታውን መነቅነቁ አይቀርም ይለናል። ከሰራነው
ታላቅ ታሪክ ይልቅ ገና የምንሰራው ታሪክ ይበልጣልና ዛሬ በዙሪያችን የተሰጠንን ትንሽ እድል በግዙፍ ራእይ አጅበን ትልቅ ታሪክ እንሰራበት ዘንድ አበክሮ ይመክራል። ፈጣሪ በውስጣችን ያስቀመጠው አቅም ተአምር ለመስራት አይገደውምና በምናየው ገደብ
ከመታሰር ይልቅ ተግዳሮቱ በውስጣችን ከተሸሸገው ቅምጥ አቅም ( potential) አንፃር ሲታይ ኢምንት ነውና በትልቁ እያለምን፣ በትልቁ እያሰብን ፣ ለትልቅ ታሪክ እንተጋ ዘንድ ወደፊት በሉለት ይለይለት እያለ ወደ ስኬት ዘመቻ ይመራናል።

በመፅሃፉ ውስጥ የተቀናበሩትን እሳቤዎች አብዝቼ ባሰብኳቸው ግዜ ከገዛ ዘመዶቼ ጓዳ ከዘመን በፊት ሲነገር የቆየ አንድ ትርክት ወደ ማእደ ትውስታዬ ተዘረጋልኝ። እንዲህ ነው ነገሩ። ባንድ ወቅት አንድ ከራማ ሞልቶ የሚፈስባቸው ትልቅ ሼክ ነበሩ እየተባለ ይነገራል።
ዱኣቸው ቅቡል የሆነ፣ ምርቃታቸው ገና ከአፋቸው ሳይወጣ የሚደርስ፣ በቱፍታቸው በሽታ የሚያሽሩ ነበሩ ተብሎ ይተረክላቸዋል። ብዙ ዘመን ሚስት ያገቡ ዘንድ ተለምነው ተለምነው " እምቢኝ ገና ነው የኔ ሰርግ" እያሉ ይመልሱ ነበር። ባንድ ወቅት የቤት ጉዳያቸውን የምታከናውን የቤት ሰራተኛ ( ካዳሚ) ወደ ቤታቸው አመጡላቸው። ጠንካራ፣ስራ ወዳድ፣ ተንከባካቢ ሴት ሆነችላቸው። እነ ሼህ ቅዳሜ ቅዳሜ ዱኣ አያልፋቸውም። ባንድ ቅዳሜ ቀጤማው ተነስንሶ፣ ሳሩ ተጎዝጉዞ፣ እረከቦቱ ተሰይሞ ሳለ
የነፍስያቸው መቃኛ የሆነውን የዱኣ ላይ እንጉርጉሮ በሸገነው ድምፃቸው ያወርዱት ጀመር። እንጉርጉሯቸው ለቀዬው ሰው ሁላ ማነቃቂያ፣ ለካዳሚዋ ሴት ደግሞ በየሳምንቱ እየተናፈቀ የሚመጣ በረካ ነው። ካዳሚዋ ሴት የእነ ሸህን እንጉርጉሮ በሰማች ግዜ ነፍሷ ጥፍት ይላል። ድምፃቸውን በሰማች ግዜ ልቧ ይሸፍታል። ስኒው ከእጇ ያመልጣል፣ ጀበናው ገንፍሎ ይኩረፈረፋል፣ ይህ ሁሉ ሲሆን እሷ ግን በአድናቆት ተመስጣ የነሸህን አይን አይናቸውን እያየች አለሙን ሁሉ ትረሳለች። ወደ ዃላ ላይ አድናቆት ወደፍቅር ከፍ ብሎ ተቸገረች። ፍቅር እንደለከፋት አይነውሃዋ ያሳብቅባታል። ይህንን እውነታ ሼሁ በዘወርዋራ
መንገድ አወቁት። ""።ይህች አቅሟን የማታውቅ ሴት እኔን መመኘቷ አሳቀኝም፣
አሳቀቀኝም"" እያሉ ከራሳቸው ጋር ሲያወጉ ከረሙ። ታዲያ አንድ ቅዳሜ የዱኣው ሃድራ በሞቀበት፣ ካዳሚዋ ሴት ቡና እያፈላች ሳለ እነ ሸህ ማንጎራጎር ጀመሩ። በቅኔ ተስፋሊያስቆርጧት ፈልገው ኖሮ እንዲህ ሲሉ ተቀኙ።


እሳት ነዶ ነዶ፣ ሰማዩን አይፈጅም፣
የማያገኙትን፣ መከጀል አይበጅም።


ይህን የሰማችው ካዳሚ እንዲህ መለሰችላቸው።

እሳት ምድር ነዶ፣ ሰማይ ላይ ነው ጭሱ፣
አምላክ ለሚያደርገው፣ ሂማ አታሳንሱ።

እነ ሸህ ይህንን መብረቅ የሆነ መልስ ሲሰሙ ተብረከረኩ። የልጅቱ ብርታትና የልብአፍቃሪነቷ አሸነፋቸው። ቡናው እየተቀዳ ሳለ እንግዲህ ሚስቴ አንችው ነሽ ብለው በወግ በማረግ ተዳሩ።
አያችሁ እነ ሼህ እንዴት የቤት ሰራተኛዬ ጌታዋን ልታገባ ሽቅብ ትመኛለች?? ብለውአሰቡ። ዋናው ምስጢር ያለው ልብ ላይ ነው። ሰው በልቡ እንዳሰበ እንደዚሁ ይሆናል።የቤት ሰራተኛ ተብላ ብትጠራም እሷ ግን ራስዋን እንደ እቴጌ ቆጥራ ነው የኖረችው። ሃገር መንደሩ እንደ ገረድ አድርጎ ቢጥላትም እሷ ግን የእነ ሼህ ማጀት ባለ ሙሉ ሹመኛ እመቤት አድርጋ ነበር ያሰበችው። ለትንሽ ስራ ተጠራች እሷ ግን በትልቁ አሰበች እናም ባለ ትልቅ ህልም ሆና ሃሳቧን አሳካች። ከዚህ ወዲያ The magic of thinking BIG!!!!
ይኖራል እንዴ???? የኛ ዘመዶች ከፈረንጆቹ በፊት አቅምና ጉልበት የሚሆን ሃገርኛ ፍልስፍናነበራቸው ማለት ይሆን????

#አንድ ታሪክ ደግሞ ከባህር ማዶ እንጨምር


ቦክሰኛው መሀመድ አሊ ቴሬልን ለመግጠም ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ቴሬል በድሮ ስሙ ካሲስ ክለይ እያለ ሲጠራው ለምን በባርነት የነጭ ስም ትጠራኛለህ በስሜ "መሀመድ" ለምን አትለኝም? ቢለውም ቴሬል "መሀመድ" ላለማለት "ክለይ" እያለ እምቢ በማለቱ ግብግብ ተፈጠረ። በ ቦክሱ ግጥሚያ ቀን መሀመድ አሊ ከሰባተኛው ዙር በኋላ እየቀጠቀጠው "ስሜ ማን ነው" (What is my name) እያለ ይጮህ ነበር። መሀመድ አሊ በቦክስ አለም እንዲህ ሲናደድ ታይቶ አይታወቅም። መጨረሻ ላይ ምን እንደተፈጠረ HBO በዚህ ጉዳይ documantary ሰርቶበታል በአጭሩ ግን ይህንን ተመልከቱ። ራስህን ሁን ራስህን አስከብር አትሽለጥለጥ።
**
ሸንበ
ቆ ቢረዝም ቅል አያንጠለጥልም
ሂማ የሌለው ሰው ቢታገል አይጥልም


እውነትም ሂማ አታሳንሱ!!!!!!!!!!