Get Mystery Box with random crypto!

' ለአላህ ብላችሁ ተባበሩኝ እያለቀስኩ ነው…ልጄ ልትገደልብኝ ነው አስመጡልኝ ' - አረጋዊያኖቹ የ | 🇪🇹 ኢትዮ Students

" ለአላህ ብላችሁ ተባበሩኝ እያለቀስኩ ነው…ልጄ ልትገደልብኝ ነው አስመጡልኝ " - አረጋዊያኖቹ የለይላ  አባትና እናት

ከአሰሪዎቿ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ግጭት ተፈጥሮ በመካከል የአንድ ታዳጊ ሕይወት በማለፉ በሳዑዲ መንግሥት ሕግ መሠረት የሞት ፍርድ የተፈረደባት ኢትዮጵያዊት የሟች ቤተሰቦች የሞት ፍርዱ ወደ ካሳ እንዲቀየር ተስማምተዋል።

በዚህም የተጠየቀው 2 ሚሊዮን ሪያል ከወዳድ ዘመድ ተሰብስቧል። ይሁን እንጂ ገንዘቡ ቢሰበስብም የሚላከው በመንግሥት በኩል በመሆኑና ገና ስላልተላከ ፍርደኛዋ በሳዑዲ የሞት ፍርድ እየተጠባበቀች መሆኑን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከቤተሰቦቿ ገለጻ ተረድቷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገራቸው አረጋዊ የፍርደኛዋ አባት አቶ ኑርሰቦ፣ " ለአላህ ብላችሁ ተባበሩኝ #እያለቀስኩ ነው። እናቶች፣ አባቶች እባካችሁ ተባበሩኝ። የኢትዮጵያ ልጆች፣ የዓለም ልጆች ተባበሩኝ እባካችሁ ትመጣልኛለች እያልኩ 11 ዓመታት ሙሉ ጠበኳት እባካችሁ " ሲሉ እንባቸውን እያፈሰሱ ተማጽነዋል።

" ልጄን ልትገደልብኝ ነው አስመጡልኝ " ያሉት፣ የፍርደኛዋ አረጋዊት እናት ወ/ሮ ነፊሳ ሙሳ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከወዳጅ ዘመድ የተሰበሰበውን ገንዘብ በባንክ በኩል ወደ ሳዑዲ መንግሥት በፍጥነት በመላክ ልጃቸውን ከሞት እንዲታደግላቸው በአጽንኦት ጠይቀዋል።

የ21 ዓመቷ ለይላ ኑርሰቦ ሰርቸ እለወጣለሁ በሚል ተስፋ ከኢትዮጵያ ወደ ሳዑድ አረቢያ ከወጣች 11 ዓመታትን እንዳስቆጥረች ወላጆቿ አስረድተዋል። 

ይሁን እንጂ በሳዑዲ አረቢያ ከአሰሪዎቿ ጋ በተፈጠረ ግጭት የ11 ዓመት ታዳጊ በፀቡ ወቅት በመጎዳቱ  #ለአምስት_ወራት በሆስፒታል ሲረዳ ቢቆይም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም።

ይህን ተከትሎም 'የገደለ ይገደል' በሚል የሳዑዲ ሕግ ለይላ ነፍስ ማጥፋት ወንጀል ለ11 ዓመታት እስራትና የሞት ፍርድ እንደተፈረደባት ቤተሰቦቿ እንዲሁም የቲም ለይላ አስተባባሪዎች ገልጸዋል።

እንደ ገለጻው ከሆነ፣ የሟች ቤተሰቦች የሞት ፍርድ በካሳ ክፍያ እንዲቀየር ተስማምተዋል።

በዚህም 2 ሚሊዮን ሪያል፣ በኢትዮጵያ ብር ሲሰላ ደግሞ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፈላቸው ተብሎ በሳዑዲ መንግሥት ውሳኔ ተላልፎበታል።

ወዳጅ ዘመድ፣ በጎ አድራጊ ድርጆቶች ድጋፋ እንዲያደርጉ በማኀበራዊ ሚዲያ በተደረገ የ54 ቀናት ዘመቻ በቤተሰቦቿ በኢትዮጵያ በተከፈተ የባንክ አካውንት 30 ሚሊየን ብር፣ በሳውዲ በሟች ቤተሰቦችና በፍርደኛዋ በተከፈተ የባንክ አካውንት 230,000 ሪያል ተሰብስቧል።

መንግሥት የተሰባሰበውን ገንዘብ በፍጥነት ካልከ #ከ39 ቀናት በኋላ ለይላ የሞት ፍርዱ ሊፈጸምባት እንደሚችል በመግለጽ ቤተሰቦቿ እርዳታ እንዲደረግላቸው ተማጽነዋል።

በዛሬው ዕለት በሸራተን ሆቴል በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ የ'ለይላን እንታደጋት' የሶሻል ሚዲያ ንቅናቄ፣ "በሳዑዲ የሞት ፍርድ የተፈረደባት እህታችንን እንታደጋት" የሚል ጥሪ ተላልፏል።

ዘገባውን የላከው የአ/አ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ነው።

@ETHIOSTUDENTS
@ETHIOSTUDENTS