Get Mystery Box with random crypto!

​​ጾመ ሐዋርያት/የሰኔ ጾም ጾመ ሐዋርያት ሐዋርያት በጽራሐ ጽዮን መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ | Ethiopian orthodox mezemur

​​ጾመ ሐዋርያት/የሰኔ ጾም

ጾመ ሐዋርያት ሐዋርያት በጽራሐ ጽዮን መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ወደ አገልግሎት ከመግባታቸውና ወደ ሀገረ ስብከታቸው ከመበተናቸው በፊት የጾሙት ጾም ነው፡፡ የጾሙበትም ምክንያት በማርቆስ ፪፥፳ እና በማቴወስ ፱፥፲፬ ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ይኸውም የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው እኛና ፈሪሳዊያን ብዙ ጊዜ የምንጾመው ደቀመዛሙርትህ ግን የማይጾሙት ስለ ምንድን ነው? አሉት፡፡ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፡-ሚዜወች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን ? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል ያን ጊዜ ይጾማሉ፡፡››ብሎ እንደመለሰላቸው፡፡

በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር ሙሽራ የተባለው ካባ በመደረብ ፈንታ ዕርቃኑን ሆኖ በአክሊል ፈንታ የእሾህ አክሊል ደፍቶ በሚዜወቹ ፈንታ በጠላት ተከቦ በመዝሙርና በደስታ ፈንታ በልቅሶና በዋይታ ታጂቦ በክብር ዙፋን መቀመጥ ፈንታ በመስቀል ተሰቅሎ በጭንካር ተወጥሮ በቀራንይዎ አደባባይ ስለ እኛ የተሞሸረው/የተሰቀለው/ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሚዜዎቹ የተባሉት ደግሞ ምንም እንኳን በሰርጉ እለት ከአንዱ በቀር (ከወንጌላዊ ዮሐንስ/ ከጎኑ ባይገኙም ኋላ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው በሕይወትም በሞትም ሙሽራውን/ኢየሱስ ክርስቶስን/ የመሰሉ ሐዋርያት ናቸው፡፡

ይወሰዳል መባሉም እርገቱን ለመናገር ሲሆን ከዚያ በኋላ ይጾማሉ መባላቸው ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ሲያርግ መንፈስ ቅዱስ ይመጣልና፡፡ በዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን ጉዳይ ጾም በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበረ በሐዲስ ኪዳንም የቀጠለ ሥርዓት መሆኑን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበረ ስለመሆኑ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት እና አይሁድ ብዙ ጊዜ ይጾሙ እንደነበረ ተጽፏል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት"እናንተና አይሀድ የጾማችሁት ባለማወቅ ወይም በስህተት ስለሆነ ደቀ መዛሙርቴ አይጾሙም" አላለም፡፡ ነገር ግን ለጊዜው ከእኔ ጋር ናቸው ደስ ሊላቸው ይገባል፡፡ ከሄድኩ በኋላ ግን ይጾማሉ ብሏል፡፡ ይኸውም ጾም ከአዳም ጀምሮ እስከ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እና ደቀ መዛሙርቱ ከዚያም በክርስቶስ ታድሶና ተቀድሶ ለደቀ መዛሙርቱ የተሰጠ ከዚያም ለእኛ ለተከታይዮቻቸው የተላለፈ ሥርዓት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

ለጊዜው ሐዋርያት ሊጾሙበት ያልቻሉበት ምክንት ሊቃውንት ሲያብራሩ ፡-አንደኛ ጾም ሐዘን ነውና ሐዘኑም ኃላፊነትን ከመሸከም ጋር ተያያዥነት ያለው ነውና፡፡ ምክናያቱም መጾም አላማው ንስሐ እንደመሆኑ እንደ ቅዱስ ዳዊት ለግል ኃጢያት አሊያም እንደነነዌ ሰዎች ስለሀገር ጥፋት የሚያለቅሱበት የሚያዝኑበት ሁኔታ አለው፡፡ ክርስቶስ ደግሞ በስጋው ወራት ከአምላክነቱና ከሁሉ አባትነቱ ባሻገር ለሐዋርይት እንደ ሥጋ አባትም ወንድምም በመሆን የእነርሱን ኃላፊነት ተሸክሞላቸዋልና እርሱ በአካለ ሥጋ በአጠገባቸው እስካለ ድረስ ማዘን አልተገባቸውም፡፡

በሁለተኛነት ደግሞ ጾም ኃላፊነት ነው፡፡ኃላፊነቱን ለመሸከም ደግሞ ኃይል የሚሆናቸው መንፈስ ቅዱስ ያስፈልጋቸው ነበርና መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ እንዲጾሙ ጊዜ ሰጣቸው፡፡ ሦስተኛው ምክነያት አይሁድ ይጾሙት የነበረው በብሉይ ኪዳን ስርዓት ውስጥ ሆነው ነበር፡፡ ሐዋርያት ደግሞ የሐዲስ ኪዳን ልጆች ስለሆኑ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው አሊያም አዲሱ ሰው በተባለው በክርስቶስ ደም ተጽናንተውና ሥጋውንና ደሙን ተቀብለው አዲሱን ሰው ለብሰው በአዲስ መንፈስና ኃይል በአዲስ ስርዓት መጾም ስለነበረባቸው በጊዜው አልጾሙም ነበር፡፡/ማቴ ፱፥፲፮-፲፯/

ይቀጥላል
ለወዳጅዎ ሼር ያድርጉ!
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur