Get Mystery Box with random crypto!

የልብ ነገር ክፍል ስምንት (ፉአድ ሙና) *** የእኔ ያልነውን ያፈቀርነውን፣ የህይወት ማገር፣ | ጣፋጭ ታሪኮችና ወጎች

የልብ ነገር
ክፍል ስምንት
(ፉአድ ሙና)
***

የእኔ ያልነውን
ያፈቀርነውን፣ የህይወት ማገር፣
ተቀየርንበት
እንዴት ይገርማል፣ የልብ ነገር።

ያጣመደንን
የፍቅር አምሳል፣ ቀርፆ አሳምሮ፣
ጥለነው ስንሄድ
ጆሮ ነሳነው፣ ለልቡ ‘ሮሮ።

***
የህይወት ከባድ ድሎት እምነት ነው። ፈጣሪን ማመን ... አለምን ማመን ... ራስን ማመን .... እግራችን የሚያርፍበትን እያንዳንዱን መሬት ማመን .... ከላያችን ያጠለለንን ሰማይ ማመን .... ቤተሰባችንን ማመን .... ፍቅራችንን ማመን ... ማመን ... ማመን! የሰው ልጅ ማመን ባይችል መኖር የሚችል አይመስለኝም። ያብዳል! ለዚህም ይመስለኛል መከዳት ትልቅ ህመም የሚፈጥርበት .... ህይወቱን ኦና የሚያደርግበት! መከዳት ያማል .... ያስቀመጡት ከጠበቁት ቦታ ሲንሸራተት ማየት ልብ ላይ የተሰካ አንዳች ነገር በኃይል ሲነቀል የሚሰማውን አይነት ህመም ያማል። ሰው ደግሞ ይከዳል! መክዳት ተፈጥሮው ነው። የዚህችን አለም እውነተኛ ገፅ የምንመለከተው የተከዳን ቀን ይመስለኛል። መክዳት ደግሞ መጀመሪያ ይከብዳል  .... ከዚያ ይለመዳል .... ሲልም ይወደዳል። ፈጣሪን መክዳት .... ሰውን መክዳት .... ራስን መክዳት!

ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢክራም ጋር የተነካካንበትን ቀን ሳስበው ልቤ ላይ የነበረው ፍርሀት .... ፀፀት .... ቁጭት ያስገርመኛል። በሂደት እንዲህ ሊጠፋ .... እንዲህ ልንላመድ .... ከሚስቴ በላይ ልዋሀዳት .... ይገርማል! መጀመሪያ አካሌ ብቻ ነበር ፈሪሀን የከዳው! አሁን ግን ልቤም እየተከተለው ነው። ልብ ሲከዳ መጥፎ ነው። ትናንትን ያስረሳል። አሁን የፈሪሀ ውበት በኢክራም ተውጦብኛል። በብዙ ነገር ከእሷ እንደምትሻል አሳይታኛለች። ፈሪሀን በከዳሁት ልክ ፈጣሪዬንም የከዳሁ ይመስለኛል። ቀስ እያልኩ የተንሸራተትኩ ... በወንጀሌ የተመፃደቅኩ .... ከክብር ዙፋኔ የወደቅኩ .... ብዙ በጣም ብዙ አይነት መክዳትን የከዳሁ ይመስለኛል። ፈሪሀ ልትመለስ አንድ ወር ብቻ ቀርቷታል። የቤቴ ንግስት .... የምወዳት እና የምትወደኝ ሴት .... የማፈቅራት የከዳኋት ውብ .... የምትናፍቀኝ የማልናፍቃት ፈሪሀ .... ልትመለስ ነው። በየደቂቃው ትደውላለች .... ልብስ ለመግዛት ታስመርጠኛለች .... ስሟን ስልኬ ላይ ባየሁ ቁጥር እበረግጋለሁ። የፍርሀት መበርገግ አይመስለኝም .... የጭንቀት ነው። ሳላስበው ነገሮች ከቁጥጥሬ እንዳይወጡ እፈራለሁ። ስለቤተሰቦቼ .... ስለቤተሰቦቿ እያሰብኩ እጠበባለሁ። ፈሪሀ ላይ ማገጥኩ ብል በምን አይናቸው ያዩኛል? እኔንጃ! ብፀፀት እንኳን ይቅር አይሉኝም። እነሱ ፈጣሪን አይደሉም።

ቁምጣዬን እንደለበስኩ ተጋድሜ የዋና ገንዳው ውስጥ የሚሆነውን ትዕይንት እመለከታለሁ። ኢክሩ ለሙስሊም ሴቶች የተዘጋጀ ሂጃብ እና ሱሪ ያለው የመዋኛ ልብስ ለብሳ ገንዳው ውስጥ ትንሳፈፋለች። ሰሚሬ ከተረኛ «ሚስቱ» ጋር ገንዳው ውስጥ ይሳሳቃሉ። የእርሱ እጅ ላይ ሆና ለመዋኘት ትሞክራለች። አንዳንድ ሰዎችን እውነት ....  ሌሎችን ክህደት ያዛምዳቸዋል። ምንም ከድሮም ብንተዋወቅም የእኔና የሰሚር ግንኙነት ከአህመድ ጋር ካገኘሁት ወዲያ እጅጉን ጨምሯል። የጋራ ወንጀላችን ያዛመደን ይመስለኛል። በዚህ ሰዓት ፈታ ብሎ የሚያፍታታኝ እንጂ እየጨቀጨቀ ጭንቀት የሚጨምርብኝ አይነት ሰው ማግኘት አልፈልግም። ባለኝ ትርፍ ሰዓት ሁሉ አገኘዋለሁ። ኢክራምም ተጫዋችነቱ ደስ ይላታል። ሰሚር ስጨናነቅ ሲያየኝ ከከተማ ካልወጣን ብሎኝ፤ ሀዋሳ ነን። ሀዋሳ ካሉት ውድ ሪዞርቶች በአንዱ!

ሰሚሬ ከውጪ ሆኜ ስብሰለሰል ተመልክቶኝ ይመስለኛል .... ሴቶቹን ትቶ ወደኔ መጣ። ከጎኔ ያለው አልጋ ላይ እየተጋደመ በፎጣ ራሱን ያደራርቃል።

«አለሽ? ወይስ UK ነሽ?»
«UK ነኝ!» ሳቅኩኝ።
ከሰሚር ጋር ለመግባባት ብዙ ማውራት አያስፈልግም። የሚፈጥራቸው አጫጭር ኮዶች አሉ። ልፋት ያቀላሉ።

«ስማማ ሰሚሬ ፈሪሀ እኮ አንድ ወር ብቻ ነው የቀራት ለመምጣት!»
«እና ቦታ መያዝ ያለበት ነገር አለ?»
«አዎ!»
«ሰራተኛችንን ምን እንደማደርግ ግራ ገብቶኛል። ከፈሪሀ ጋር ይቀራረባሉ። ከመጣች ምንም ብትጠይቃት አትደብቃትም። የኢክራምን ጉዳይ ደግሞ ነገሩ ሲሆን በአይኗ አትይ እንጂ በደንብ ታውቃለች። ባባራት ለመናገር ጥሩ ሰበብ ይሆንላታል ብዬ ፈራሁ!»
ሰሚሬ እግሩን ወደ መሬት አውርዶ ወደ እኔ ዞሮ ተቀመጠ።
«ፉዬ ... »
አይኔን ከፍ አደረግኩ!
«ልብህ ማንን መርጧል?»
«ማለት?»
«የእውነት ፈሪሀን ትፈልጋታለህ ወይስ ክህደት መሆኑ ነው የደበረህ?»
«እኔንጃ .... » ጭንቅ አለኝ።
«እሺ አሁን ፈሪሀ ሚስትህ አይደለችም ብለን እናስብ! ዛሬ እያየሀቸው ቢሆን .... ማንን ትመርጣለህ?»
«ኢክራምን ይመስለኛል!»
«ለምን?»
«ሴት ናት! የምር ሚስት ናት! ዓለሟ በእኔ ዙሪያ ነው። ሌላ አለም አትፈልግም! እንደዛ አይነት ሴት እወዳለሁ። የምትዋረድልኝ .... ወደሷ የምቀርባት ሳትሆን ወደ እኔ የምትቀርብልኝ ሴት!»
«በቃ በቃ ..... ያለቀለት ነው ይኼማ!»
«ስትል?»
«በቃ ፈሪሀን ፍታት እና ኢክራምን አግባ!»
«እንዲህ ቀላል ነው?»
«ኪሳራው ፈሪሀን ማጣት ነው። ፈሪሀን ደግሞ አንተ ቀድመህ ለማጣት ወስነሀል። ስለዚህ ኪሳራ የለውም። ልጅም የለህም፤ ስለዚህ አያስጨንቅም!»
«ሰው መሆን የምትችል አይመስለኝም ፌሪ!»
«አንተ አትፈታትም እኮ በራሷ ፍታኝ እንድትል እናደርጋለን። ስለዚህ ጥፋቱ የሷ ይሆናል።»
«ይኼ ደግሞ ምን የሚሉት አስማት ነው?»
«ፈሪሀ ዘመነኛ ነን እንደሚሉት አይነት ናት አይደል? ዲነኛ አይደለችማ?»
«አዎ .... ማን ገደለውና ኢማኔን?»
«አየህ እንደዛ ከሆነ ሁለተኛ ሚስት አግብቻለሁ ትላታለህ። ለኢክራም እንነግራታለን። ኢክሩ የአራዳ ልጅ ናት ትተውናለች። ያኔ ፈሪሀ ፍታኝ ትልሀለች። አለቀ! ከኢክራም ጋር ተጋብተህ ትኖራለህ።»
«ምን አይነት ጨካኝ ነህ ግን ሰሚሮ?»
«ምናባህ?»
«ፌሪ እኮ ስንት አመት አቅፌያት የተኛኋት ሚስቴ ናት!»
«እና ማንአባህ ማግጥባት አለህ? ሰሚር ማግጥባት አለህ?»
«ብቻዬን ይኼ ሁሉ አመት?»
«ማግጠሀል! አለቀ።»
«ወይም ሌላ ምርጫ ልስጥህ?»
«ምን?»
«የፈጅር ሚስት ታውቃለህ?»
«አላውቅም!»
«ኢክሩን የሆነ ቤት ተከራይተህ ታስቀምጣታለህ! ከዛ ፈጅር መስጂድ ብለህ ትወጣለህ! ሁሌ ደሞ ቂርዓት አለ ከፈጅር በኋላ!»
«የምን ቂርዓት?»
«ኢክራም ናት ኡስታዛዋ! ሁሌ ፈጅር ሰግደህ እሷ ጋር ሄደህ ታረፋፍድና .... ስራ በዛው ትሄዳለህ።»
«ሳላገባት ኢክራምን?»
«በድብቅ አይድሩልህማ!»
«አዎ እሱማ! ግን የማላገባት ከሆነማ ምን ድራማ አሰራኝ? እኔ ነፃ የሆነ .... የማልማግጥበት ህይወት ነው የፈለግኩት! በቃ መስተካከል እንደድሮው መሆን እፈልጋለሁ።»
«ፈሪሀን ፍታት እና ኢክራምን አግባ አለቀ። ፈሪሀን ካገባህ ኢክራም ጋር መሄድህ አይቀርም!»
«እስኪ አስብበታለሁ።»
«ደሞ ቆፍጠን በል እንጂ! የውሳኔ ሰው ሁን የፈለገው ይምጣ!»

አንዳንዴ በገዛ እጃችን ወደ ህይወታችን የምናመጣቸው ወንጀሎች በፈለግነው ሰዓት የሚሰናበቱን አይደሉም። ወደ ወንጀል እንደመግባት መውጣቱ አይቀልልም። ትብታቡን በጣጥሶ ለማለፍ ጥንካሬ ይፈልጋል። አሁን ወደ ክብሬ ብመለስ ደስ ይለኛል። ወደ ዙፋኔ! ቁልቁል ወደ ተምዘገዘግኩበት ከፍታ! ይገራልኝ ዘንድ ምኞቴ ነው።