Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ሐምሌ 25/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ ገንዘብ ሚንስቴር ክልሎች ከሚሰበስቡት የንብረት | ኢ.ዜ.አ

ሰኞ ሐምሌ 25/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ ገንዘብ ሚንስቴር ክልሎች ከሚሰበስቡት የንብረት ታክስ ገቢ ውስጥ 25 በመቶውን ፌደራሉ መንግሥቱ እንዲወስድ የሚያዝ ረቂቅ ሕግ ለፌደሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች መምራቱን ገለፀ። ሆኖም ሕጉ ከመጽደቁ በፊት፣ ፌደሬሽን ምክር ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክልሎች የንብረት ቀረጥ ገቢ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ክሎች እና ፌደራል መንግሥቱ የሚጋሩት የጋራ ገቢ ስለመሆን አለመሆኑ በቅድሚያ መወሰን አለባቸው። ክልሎች በዋናነት የንብረት ቀረጥ ገቢ የሚሰበስቡት ከከመሬት መጠቀሚያ፣ ከሕንጻዎች እና ሌሎች የግል ንብረቶች ነው።

2፤ በደቡብ ክልል የስልጤ ዞን ምክር ቤት ዞኑ ከደቡብ ክልል ተነጥሎ ከሌሎች መሰል የአስተዳደር መዋቅሮች ጋር አዲስ ክልል ለመመስረት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን አስታውቋል። የዞኑ ምክር ቤት ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ከሀዲያ፣ ከምባታ ጠምባሮ እና ሀላባ ዞኖች እና ከየም ልዩ ወረዳ ጋር በሕዝበ ውሳኔ በሚመሰረት አዲስ ክልል ስር ለመዋቀር ነው። የጉራጌ ዞን ምክር ቤትም ተመሳሳይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። ሌሎቹ የአስተዳደር መዋቅሮች በአዲስ ክልል ስር ለመዋቀር ውሳኔ ያሳለፉት ትናንት ነው።

3፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተወካዮች ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ርዕስቱ ይርዳው ጋር በዚህ ሳምንት ሊወያዩ መሆኑን ገለፀ። የመወያያ አጀንዳው በክልሉ ውስጥ በርካታ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ያነሱት የክልልነት አደረጃጀት ጥያቄ እንደሚሆኑ ምንጮች መናገራቸውን ዘገባው ጠቁሟል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በርካታ የክልሉ አስተዳደራዊ መዋቅሮች በሁለት አዲስ ክልሎች ለመዋቀር ያሳለፉት ውሳኔ ተግባራዊ ከሆነ፣ የደቡብ ክልል ሕልውና ያከትማል።

4፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብዙኀን መገናኛ የሳተላይት ሥርጭቱን መጀመሩን የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ አስታውቋል። ብዙኅን መገናኛው በሬዲዮ በአምስት ቋንቋዎች እንዲሁም በቴሌቪዥን በሰባት ቋንቋዎች ፕሮግራሞቹን እንደሚያሰራጭ ተገልጧል። የክልሉ መንግሥት በሳተላይት ለሚሰራጨው ጣቢያ ግንባታ 200 ሚሊዮን ብር ማውጣቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን ተናግረዋል። ቤንሻንጉል ጉሙዝ ሜዲያ በሚል ስያሜ ሥርጭት ለሚጀምረው ጣቢያ፣፣ የክልሉ ምክር ቤት የአዋጅ ማሻሻያ አድርጓል።

5፤ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ አን ዌበር ወደ መቀሌ ሊጓዙ መሆኑን በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ጽፈዋል። ልዩ መልዕክተኛ ዌበር ወደ መቀሌ የሚጓዙት፣ አፍሪካ ኅብረት የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ እንደሆነ አስታውቀዋል። ሆኖም ዌበር መቼ ወደ መቀሌ እንደሚጓዙ፣ ስንት ቀናት እንደሚቆዩና በቆይታቸው ወቅት ምን ዓይነት መርሃ ግብሮች እንደያዙ አላብራሩም።

6፤ በኢትዮጵያ በቴሌኮም አገልግሎት የተሠማራው ሳፋሪኮም ኩባንያን ከፍተኛ የማኔጅመንት ሃላፊነቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ኬንያዊያን መቆጣጠራቸውን ደይሊ ኔሽን ዘግቧል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬንያዊ ሲሆኑ፣ የቦርዱ ሰብሳቢዎች ግን ከጅምሩ ጀምሮ የውጭ ዜጎች ነበሩ። ሆኖም ቦርዱ በቅዳሜለት ጉባዔው፣ አንድን ኬንያዊ ሊቀመንበሩ አድርጎ መርጧል። ሳፋሪኮም ስረ መሠረቱ የኬንያ ኩባንያ ሲሆን፣ የብሪታኒያው ቮዳፎም እና የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮን ግን ከፍተኛ ድርሻ አላቸው።

@Ethiopianewsagency (ኢዜአ)