Get Mystery Box with random crypto!

ረቡዕ ሐምሌ 27/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አራት | ኢ.ዜ.አ

ረቡዕ ሐምሌ 27/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አራት ዋና ከተሞች እንዲኖሩት ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ አስታውቋል። በብዝሃ ዋና ከተሞች ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ፣ ቦንጋ፣ ተርጫ፣ ሚዛን አማን፣ ቴፒ ከተሞች እኩል የክልሉ መቀመጫ እንዲሆኑ ተደንግጓል። በረቂቅ አዋጁ መሠረት፣ ቦንጋ የክልሉ የፖለቲካና የርዕሰ መስተዳድሩ ጽሕፈት ቤት፣ ተርጫ የክልሉ ምክር ቤት፣ ሚዛን አማን የዳኝነት አካሉ እንዲሁም ቴፒ የብሄረሰቦች ምክር ቤት መቀመጫዎች ይሆናሉ።

2፤ በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ካንድ ወር ወዲህ በተቀሰቀሰ ግጭት ከ8 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ሰምተናል። አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ከኦሮሚያው ባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ በአምስት ቀበሌዎች መጠለላቸውን ዘገባው አመልክቷል። የግጭቱ ምክንያት የመሬት ሽሚያ፣ ወሰን ዘለል እርሻ እና የኢንቨስትመንት መስፋፋት የፈጥፕረው የመሬት እጥረት ናቸው ተብሏል። በአካባቢው ግጭቱ እና መፈናቀሉ ብዙ ዓመታት ያስቆጠረ ነው። ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት፣ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ተፈናቃዮች ተናግረዋል።

3፤ በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት እየተደረገ ስላለው ጥረት ነገ ለኅብረቱ ሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ማብራሪያ እንደሚሰጡ ከኅብረቱ የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል። ኦባሳንጆ ባለፉት ሁለት ወራት ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሃት ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ዙሪያ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያደርጋሉ። በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢጋድ ተወካዮች መግለጫ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኦባሳንጆ ለምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻውን ማብራሪያ የሰጡት በየካቲት ወር ነበር።

4፤ በተመድ የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ዛሬ በአፍሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ይጀምራሉ። ግሪንፊልድ በአራት ቀናት የአፍሪካ ቆይታቸው፣ ኡጋንዳን፣ ጋናን እና ኬፕቨርድን እንደሚጎበኙ ተናግረዋል። ግሪንፊልድ ጉብኝታቸው የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በቅርቡ በአፍሪካ ያደረጉትን ጉብኝት ዒላማ ያደረገ እንዳልሆነ ተናግረዋል። አፍሪካዊያን ከአሜሪካና ከሩሲያ አንዱን እንዲመርጡ አንገፋፋም በማለት ትናንት የተናገሩት ግሪንፊልድ፣ ሆኖም ሩሲያ ስለ ዩክሬኑ ጦርነት የምትነዛውን የሐሰት ትርክት እንዲያምኑ አንፈልግም ብለዋል።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 52 ብር ከ1698 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 53 ብር ከ2132 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 60 ብር ከ9973 ሳንቲም፣ መሸጫው 62 ብር ከ2172 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ53 ብር ከ4688 ሳንቲም ሲገዛ እና በ54 ብር ከ5382 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል።

@Ethiopianewsagency (ኢዜአ)